ኢላን መስክ

ከ 5 ሰአት በፊት

የቢሊየነሩ የቴክኖሎጂ ሰው ኢላን መስክ፤ ኒውራሊንክ የተባለው ኩባንያው ሰዎች አንጎል ውስጥ የሚገጠም ገመድ አልባ ቺፕ መሥራቱን ይፋ አድርጓል።

መስክ እንዳለው ይህ ቺፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰው ላይ መኩራ ተደርጎበታል።

የመጀመሪያ ዙር ውጤቶች እንደሚያሳዩት የኒውሮን መጠንን እና የነርቭ ‘ኢምፐልስ’ ከፍ ማለት የተስተዋለ ሲሆን ታካሚው እያገገመ ይገኛል።

የኩባንያው ዓላማ የሰው ልጅን አእምሮ ከኮምፒውተር ማስተሳሰር ነው።

ይህን በማድረግ ውስብስብ የሆኑ ከነርቭ ጋር የተያየዙ (ኒውሮሎጂካል) የጤና ችግሮችን ለመፍታት ያስባል።

ሌሎች ተመሳሳይ ምርት የሚያመርቱ ድርጅቶችም ይህን ቺፕ የሰው ልጆች አንጎል ውስጥ መግጠም ጀምረዋል።

ቢቢሲ ከኒውራሊንክ እና ከአሜሪካው የምግብ እና መድኃኒት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት ምላሽ ለማግኘት ሞክሯል።

የምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን (ኤፍዲኤ) ኢላን መስክ ቴክኖሎጂውን ሰዎች ላይ እንዲሞክር ይሁንታ የሰጠው ባለፈው ግንቦት ነው።

ከዚያ ቀደም ሌሎች ኩባንያዎች ይህን ፈቃድ ለማግኘት ብዙ ቢጥሩም አልተሳካላቸውም ነበር።

ኒውራሊንክ እንደሚለው ፈቃዱን ተከትሎ ስድስት ዓመታት የሚፈጅ ጥናት ጀምሯል።

ለዚህ ሥራ የተመደበው ሮቦት 64 ከፀጉር ዘለላ የቀጠኑ ገመዶችን ጭንቅላት ውስጥ በመግጠም “የእንቅስቃሴ ሂደትን” መቀጣጠር ይጀምራል።

ኩባንያው እንደሚለው እኒህ ቀጫጭን ዘለላዎች ቻርጅ የሚደረጉት ገመድ አልባ በሆነ ቴክኖሎጂ ነው።

64ቱ ዘለላዎች ምንም ገመድ ሳይጠቀሙ የአእምሮ የሚገኙ መረጃዎችን (ሲግናል) ወደ አንድ መተግበሪያ ይልካሉ። መተግበሪያው ደግሞ አንድ ሰው ምን ዓይነት እንቅስቃሴ ለማድረግ እንዳሰበ መረዳት ይችላል።

በቀድሞው ስሙ ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ገፁ ላይ መልዕክት ያሰፈረው ኢላን መስክ፣ አዲሱ ቴክኖሎጂ መጠሪያው ቴሌፓቲ ነው ብሏል።

ቴሌፓቲ የተሰኘው ስም የተሰጠው ቴክኖሎጂ “ስልካችሁን አሊያም ኮምፒውተራችሁን ይቆጣጠራል፤ ከዚያ በማሰብ ብቻ የትኛውንም ነገር ማድረግ ትችላላችሁ” ይላል መስክ።

“መጀመሪያ ይህን ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚችሉት እጅግ እና እግራቸውን ያጡ ሰዎች ናቸው” ሲል አክሏል ቢሊየነሩ።

የሞተር ኒውሮን በሽታ የነበረው ሟቹ ሳይንቲስትን ጠቅሶ “ስቴፈን ሆውኪንግ ከትይባ ፍጥነት በላይ ማውራት ቢችል ብላችሁ አስቡት። በቃ ዓላማው እሱ ነው” ይላል።

ምንም እንኳ የኢላን መስክ ኒውራሊንክ ነገሮችን በፍጥነት ማስኬድ ቢችልም በዘርፉ ከሁለት አስርታት በላይ ሲመራመሩ የቆዩ ኩባንያዎች አሉ።

በአሜሪካዋ ዩታህ የሚገኘው ብላክሮክ ኒውሮቴክ ለመጀመሪያ ጊዜ አንጎል ውስጥ ቺፕ የገጠመው በአውሮፓውያኑ 2004 ነበር።

የኒውራሊንክ ተባባሪ ፈጣሪ በሆነው ግለሰብ የተመሠረተው ፕሪሲሽን ኒውሮሳይንስ ሌላኛው መንቀሳቀስ የማይችሉ ሰዎች ለማገዝ የተቋቋም ኩባንያ ነው።

በቅርቡ አሜሪካ ውስጥ የተደረጉ ምርምሮች እንደሚያሳዩት የሰዎች ጭንቅላት ውስጥ የሚገጠሙ ቴክኖሎጂዎች ሰዎች ማውራት የፈለጉትን ነገር ቀድመው ማወቅ ችለዋል።