January 30, 2024 

የዝምድና ታሪክ ፟ በዕውቀቱ ስዩም
በምስሉ ላይ ምኒልክና የሸዋ መኳንንት ይታያሉ ፤ በቀኝ በኩል ጫፍ ላይ ቆሞ የሚታየው ድቡልቡል ሰውየ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አያት ደጃዝማች ጉዲሣ ነው፡፡ የዚህን መስፍን ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ባጭሩ የዘገበው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የውጭ ጉዳይ ምኒስትር የነበረው ህሩይ ወልደሥላሴ ነው፡፡ የ”ህይወት ታሪክ“ በሚል ርእስ በ1914 ባሳመው መጽሐፉ፤ ”ወልደሚካኤል“ በሚል ርእስ ሥር እንዲህ ብሎ ይጀምራል፤ “ ደጃዝማች ወልደሚካኤል ፤አባ ጉራች፤ ጉዲሣ ወልደሚካኤል ፤ የንጉሥ ሳህለሥላሴ አማች፡፡ እሳቸውም የራስ መኮንን አባት ናቸው፤ ገጽ 86)ዝርዝሩ ይቀጥላል፡፡ ይህ መጽሀፍ ከተጻፈ ከአርባ አመት በኋላ የተጻፈው የብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል“ ቼ በለው” የቀኃሥን አያት ስም ዞር አድርጎ ”ወልደሚካኤል ጉዲሣ እንደሆነ ጽፏል፡፡

ስለሰውየው የተጻፉትን ነገሮች በግሌ መርምሬ ፤ ጉዲሣ ወልደሚካኤል የአንድ ሰው ስም መሆኑን ደርሸበታለሁ፡፡ ጉዲሣ የተወላጅነት ስም ሲሆን ወልደሚካኤል የጥምቀት ስም ነው፡፡

የምኒልክ አያት ንጉሥ ሣህለሥላሴ ልጃቸው ተናኘ ወርቅን ለጉዲሣ ድረዋል፡፡ ከሁለቱ ግኑኝነት የተፈሪ አባት መኮንን ከነሉሉ ዱብ ብሏል ማለት ነው፡፡

በሳህለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የሸዋን ቤተመንግሥት ለመጎብኘት የታደሉ የእንግሊዝና የፈረንሳይ ጸሐፊዎች ይህንን ጋብቻ በጉዞ ማስታወሻቸው መዝግበውት ይሆን ብየ ያቅሜን ገለጥ ገለጥ ማድረግ ጀምሬ ነበር፡፡Maurice Tamisier እና Edmond Combes የተባሉ የፈረንሳይ መንገደኞች ይቺን ነገር ጣል አርገው አልፈዋል፤
Le Lendemain de notre arrv ée à Ankober ,SahleSellassi ,qui avait promis l’une de ses filles en marriage à un Galla converti ,l’envoya chez son futur époux ,qui gouvernait une province à plusieurs journées de la capitale .
ትርጉም በስለሺ፤
“አንኮበር በገባን ማግስት ሳህለሥላሴ ከሴት ልጆቹ አንዲቱን ላንድ የተጠመቀ ኦሮሞ ለመዳር ቃል ገብቶ ኖሮ ከመዲናይቱ ብዙ ቀን መንገድ የሚርቅ አገር ወደ ሚገዛው እጮኛዋ ሸኛት ፤ ” ይሉና የነበረውን አጀብ በሰፊው ይዘግባሉ፡፡
የተጠመቀው ኦሮሞ የዶባው ገዥ ጉዲሳ ወልደሚካኤል ይሆን? ልጂቱስ ተናኘ ወርቅ ትሆን ?

ዋናው ጉዳይ ወዲህ ነው፤ በኢትዮጵያ የነበረው የባላባት ወግ ባውሮፓ ከነበረው ዘረኝነት ወግ በጣም የተለየ ነበር፡፡ በግለሰብነቱ ከተርታው የተለየ ብልጫ ያሳየ ሰው ለከፍተኛ ማእረግ ይመለመላል፤ የንጉሥ ልጅ ያገባል ፤ እድል ከቀናውም ንጉሥ ይወልዳል፡፡ ባህልን በጌቶች ባህል የማስገበር ዝንባሌ ቢኖርም“ ደምህ ከደሜ” እንዳይቀላቀል የሚያሰኝ የዘረኝነት ፖሊሲ አልነበረም፡፡
በመጨረሻም ! ብሄርብሄረሰቦች ሆይ ተጣበሱ ! ተካለሱ ! በጥላሁን ጠመኔ የተሠመረውን ድንበር አፍርሱ!
( የግርጌ ማስታወሻ ፤ ጥላሁን የስብሐት ገብረእግዚኣብሄር ”ሌቱም ኣይነጋልኝ ገጸ- ባህርይ ነው፡፡ ለመደባደብ ሲፈልግ በሱና ባባላጋራዎቹ መካከል ወለል ላይ የጠመኔ ድንበር ያሰምራል፡፡) ፟ በዕውቀቱ ስዩም