January 30, 2024 – Konjit Sitotaw 

በኦሮሚያ ክልል ለኹለተኛ ዙር የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጠርቶታል በተባለው የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ አድማ ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰኑ ቀናት ተግባራዊ መኾን መጀመሩን ዋዜማ ካሰባሰበቻቸው መረጃዎች መረዳት ችላለች።

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ነቀምት ከተማ የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ጨምሮ እስከ ዛሬ እኩለ ቀን ድረስ ባንኮች፣ ንግድ ቤቶች፣ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ዝግ መኾናቸውን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች።

በምዕራብ ወለጋ ዞን ደምቢዶሎ ከተማ እንዲኹም መነሲቡ እና ቆንዳላ ወረዳዎች፣ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሻምቡ ከተማ እና የተለያዩ ወረዳዎች፣ በምዕራብ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች የተለያዩ ወረዳዎች እንዲኹም በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ከጭሮ ከተማ ወደ ድሬዳዋ መሉ ለሙሉ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴዎች መቆሙን ለማወቅ ተችሏል።

በምሥራቅ ሸዋ ዞን ከአምቦ ከተማም፣ የሚወጣም ኾነ የሚገባ ተሽከርካሪ እንደሌለ ዋዜማ ባደረገችው ማጣራት የተረዳች ሲኾን፣ ወደ አዳማ እና አዲስ አበባ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ብዛትም በአንጻራዊነት መቀነሱን ምንጮች ገልጸዋል።

በተጠቀሱት አካባቢዎች የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት በመሄድ ባለንብረቶች ተሽከርካሪዎቻቸውን እንዲያወጡና የንግድ ቤቶችን እንዲከፍቱ ጫና እያደርጉ እንደኾነ ዋዜማ ተረድታለች።