January 30, 2024 –

ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) ራሱን አጠፋ ወይስ ሰው ገደለው ?! (መላኩ ብርሃኑ )

ቀኑን ሙሉ ሲያወሩ ቢውሉ መስማት የማይሰለቹኝ አራት ሰዎች አሉ።ስብሃት ገብረእግዚአብሄር፣ ዘነበ ወላ ፣ አብዱ አሊሄጂራ እና ገነነ መኩሪያ።

ገነነ ከወሬው በላይ የሚያውቀው ነገር መብዛቱ ነው የሚደንቀኝ።እነዚያን በደቃቃ ፎንቶች ሊብሮ ላይ ይጽፋቸው የነበሩ መሶብ የሚሞሉ የኳስ ወሬዎችን ነፍሱን ይማረውና ታናሽ ወንድሜ በተመስጦ ሲያነባቸው ነበር የማያቸው።ኳስ አፍቃሪ ስላልሆንኩ የኳሱን ገነነን ብዙም ሳላነበውና ሳልሰማው ነው የኖርኩት።በኋላ ግን ገነነ መስማት በምወደው የድሮ ታሪኮች መጣ። ተከታታዩ ነበርኩ።

ከገነነ የሚገርመኝ ነገር…አወራሩ ነው! He was so engaging ካሜራ ፊት ሆኖ ሲናገር ፊቴ ቆሞ የሚያወራኝ ያህል ነበር ቀልቤን የሚይዘው። ቀንና ሰዓት ስምና ቦታ ሳይረሳ ሲናገር ይደንቀኝ ነበር። የትናንቱን ማስታወስ ለሚቸግረኝ እኔ ገነነ የረጅም ዘመን ታሪክን ሳያዛንፍ ወደኋላ ተመልሶ ሲያወራ ትንግርቴ ነው።

የሆነው ሆኖ ገነነ አሁን የለም።አፈሩ ይቅለለው። አሟሟቱ ግን በጣም እንቆቅልሽ ሆኖብኛል። በተለይ በቴዲ ተክለአረጋይ ጽሁፍ መነሻነት ኢትዮፒካል ሊንክ ላይ ከሰማሁት መረጃ ተነስቼ ፣ (ጥቂትም ቢሆን) የፖሊስ ወንጀል ምርመራ ሳይንስ እንደተማረ ሰው ሆኜ መረጃውን ሳብላላው ያልተመለሱልኝ ዋና ዋና ጥያቄዎች አንጎሌ ውስጥ ተጉላልተውብኛል።

ከዚያ በፊት ግን እከሌ አስነጠሰው ተብሎ ወሬ በሚሆንበት በዚህ ዘመን ገነነን ያህል ታላቅ ሰው መታመሙና እግሩ መቆረጡ ሲነገር አለመስማቴ (ሌሎች ሰምተው እንደሁ እንጃ እንጂ) ፣ ይባስ ብሎ እስኪቀበር ድረስ ሆቴል ክፍል ውስጥ ሞቶ መገኘቱ ሳይወራ ድብቅ ሆኖ መቆየቱ በራሱ በጣም ደንቆኛል።

ጊዜና አጋጣሚ እድል የፈጠረላቸው ሰዎች በሚገኑበት በዚህ ሃገር ብዙ ሰርተው አሻራቸውን ያኖሩ ባለውለታዎች እንዲህ ሲድበሰበሱ ሳይ ማህበረሰቡ ለህትመት እና ለብሮድካስት ጋዜጠኞች ያለውን ሚዛን ፣ ከብሮድካስትም ቴሌቪዠን መዝናኛ ላይ ለሚሰሩ ሰዎች የሚሰጣቸውን ‘ዕውቅና’ እያሰብኩ የጋዜጠኝነት ሙያና ማህበረሰቡ ሙያና ባለሙያውን የሚረዳበትን ክፍተት አስባለሁ።(በዚህ ጉዳይ ሌላ ቀን እጽፋለሁ) ።

ወደገነነ አሟሟት ልግባ። (ትንተናዬን ያንተራስኩት በኢትዮፒካል ሊንክ ላይ ከሰማሁት መረጃ ላይ ብቻ መሆኑን ልብ በሉልኝ።)

በዊልቼየር ላይ ነበር የተባለው ገነነ ለስራ ከገባበት ጊዮን ሆቴል በወደቤቱ ሳይመለስ ቀረ።ሁለት ቀን ሙሉ ሲጠፋ ከቤተሰቡ ‘የት ገባ’ ብሎ ተጨንቆ የፈለገው ሰው አለመኖሩን ነው የተረዳሁት። ገነነ “ስልኩን አጠፋ” ተብሎ ብቻ ሊታለፍ የሚገባው ሰው ነው ? ….ዘመዶቹ…ወዳጆቹ..ባለቤቱም ጭምር ምን ያህል ..የት ርቀት ድረስ ሄደው ፈለጉት? ይህን ያህል ታዋቂ የሆነ ሰው ሲጠፋ በተገኘው መንገድ ሁሉ ‘ፈልጉልኝ’ አይባልም?…ወድቆ ቀርቶስ ቢሆን? ለያውም በዊልቼየር ያለ ሰው…ቢያንስ የተጠለለበት የ ‘ዋአካን ሆቴል’ ሰዎች እኮ ያውቁታል። ጠፋ የሚል ወሬ ቢሰሙ እኛጋ ነው ፣ ኑና ውሰዱት ማለታቸው አይቀርም ነበር።

እዚህ ላይ መረጃው ገነነ ከቤተሰብ በተለይ ከባለቤቱ ጋር የሆነ አለመግባባት አንደነበረው እንዳስብ አድርጎኛል።በተለይም ከሁለት ቀን በኋላ “እዚህ ነኝ ያለሁት” ያለው ሰይድ ኪያርን ከሆነ ለባለቤቱ መንገር ያልፈለገበት ምክንያት ነበረው ማለት ነው። ወደቤቱ መመለስ አልፈለገም ማለት ነው። ባለቤቱም ‘የጠፋው’ ባሏ ተገኝቶ ስኳሩ ወርዷል ስትባል ሚሪንዳ አዝዛለት ብቻ አለ የተባለበት ሆቴል ሳትሄድ ቀረች መባሉም የሁለቱ ግንኙነት ቅሬታ ውስጥ መሆኑን ያረጋግጣል። ይህ እንግዲህ የቤተሰባዊ ግንኙነት ጉዳይ እንጂ ወንጀል አይደለም።ገነነ ባይሞት ኖሮ ይህ ጉዳይ ከቤተሰቡ ውጪ የሚመለከተው ማንም የለም። የቤተሰቡ ጉዳይ ብቻ ስለሆነ ከአማሟቱ ጋር እስካልተገናኘ ድረስ ወደኋላ ዳና የሚፈተሽበት ጉዳይ አይሆንም። ከመጨረሻው መጀመሪያ ስንነሳ ግን “ገነነ በሩን ዘግቶ ሲንኳኳ አልከፍት አለ” ተባለ አይደል?

መጀመሪያ ይህ ክፍሉ ውስጥ ያለው ሰው ደህና ስለመሆኑና በህይወት ስለመኖሩ በሚቻለው መንገድ ሁሉ ማረጋገጥ የማንም ሰው ቀዳሚ ተግባር ነውና የሆቴሉ አስተናጋጅም ሆነ ተጠርተው የመጡት የገነነ ባለቤትና ጓደኛው ሰይድ ኪያር በሩን ደጋግመው ማንኳኳታቸው …አልከፍት ሲላቸውም በብርሃን ማስገቢያ መስኮቱ በኩል ሰብረው ወደውስጥ መመልክታቸው ተገቢ ነበር ። ምናልባት እርዳታ በሚያስፈልገው ደረጃ ላይ ሊሆን ስለሚችል ጊዜ ላለመውሰድና ያለበትን ሁኔታ ለማየት የማንንም ህጋዊ አካል ፍቃድ መጠበቅ አይገባም። የነፍስ ማዳን ስራ ስለሆነ በህግም ድጋፍ አለው።

እኔን ያላሳመነኝና ከባድ ጥፋት ነው ብዬ የምሞግተው ተግባር ፣ ምናልባትም ዛሬ በይሆናል እንድንነጋገርና አሟሟቱ እንቆቅልሽ እንዲሆንብን ምክንያት የሆነው ድርጊትም ከዚህ በኋላ የተፈጸመው ነው። በግሌ ይህ ድርጊት “ከባድ ቸልተኝነት እና ጥፋት ነው” እላለሁ።ፈጻሚዎቹ ራሳቸውም ለጥርጣሬ እንዲዳረጉ ያደረጋቸው፣ ለገነነ ሞት ምክንያትም ጥርት ያለ መረጃ እንዳይወጣ ምክንያት የሆነው ይኸው ጥፋት ነውና ስለሱ ልናገር።

በተሰበረው ብርሃን ማስገቢያ በኩል ሲያዩት ገነነ ግማሽ አካሉ መሬት ግማሹ ዊልቼየር ላይ ሆኖ ታያቸው። በሌላ አነጋገር የሚያዩት ሰው ‘በድን’ ነበር። የሆነ ችግር ተፈጥሯል ማለት ነው። የገነነ በህይወት መኖር በራሱ አጠራጣሪ ሆኗል ማለት ነው።ደግሞም ከምሽቱ 3 ሰዓት ሆኗል። ስለዚህ ሁሉም ሰዎች እዚህ ላይ መቆም ነበረባቸው። የገነነ ባለቤት፣ ሰዒድ ኪያርም ይሁን የሆቴሉ ሰዎች በቀዳዳ ወድቆ ‘በድን ሆኖ’ ያዩትን ሰው ለማውጣት በሩን መስበር አይገባቸውም ነበር። በሩን በመጥረቢያ ሰብረው በመግባታቸውና ይህንን ጥፋት በመፈጸማቸው ግን “በሩ የተቆለፈው ከውስጥ ነበር ወይስ ከውጭ” የሚለውን ወሳኝ ማስረጃ አጥፍተውታል።

ፖሊስ በሩን ሰብሮ ገብቶ፣ ገነነም ሞቶ አግኝቶት ቢሆን ኖሮ የመጀመሪያ ተግባሩ የክፍሉ በር የተቆለፈው ከውስጥ መሆንና አለመሆኑን ማረጋገጥ፣ ከዚያም የክፍሉ መስኮትም (መስኮት ካለው) ከውስጥ የተዘጋ መሆኑን ማረጋገጥ ነው። ይህ ከተደረገ ገነነ ራሱን አጥፍቶ ሊሆን እንደሚችል ወይም በሰው ተገድሎ ሊሆን እንደሚችል ምርመራውን ፈር የሚያስይዝ ዋና የቴክኒክ መረጃ ተገኘ ማለት ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ከበሩ እጀታዎች ላይ የሚወሰድ አሻራ እና ከቁልፉ ላይ የሚወሰድ አሻራም አለ። ይህ አሻራ ከገነነ አሻራ ጋር ‘ማች’ ይሰራል። ውጤቱ ወንጀል መኖርና አለመኖሩን የሚጠቁም ሁለተኛው ወሳኝ የቴክኒክ ማስረጃ ነው። ገነነ ባለበት አካባቢ በልዩ መሳሪያ የዱካ አሻራም ይፈለጋል።አልጋው ይፈተሻል። ክፍሉ ውስጥ ያለ ምንም አይነት ፈሳሽ መጠጥ ይዘቱን ለማረጋገጥ ለፎረንሲክ ምርመራ ይያዛል።ሌሎችም በርካታና እዚህ ቢነገሩ የማይጠቅሙ ምስጢራዊ የቴክኒክ ምርመራዎች ይካሄዳሉ። ማስረጃዎች ይሰበሰባሉ። በዚህ የተነሳ ፖሊስ ነገሩ ግድያ ወይም የተፈጥሮ ሞት አለያም ራስን ማጥፋት ስለመሆኑ ፈር የሚያሲዝ መረጃ ይኖረው ነበር።

ሁለተኛው ከባድ ጥፋት ደግሞ ይኼ ነው! …የገነነ ሚስትም ሆነ ሰዒድ ኪያር ክፍሉ ሲገቡ ገነነ መሞቱን ካረጋገጡ ምንም ሳይነካኩ ፖሊስ መጥራት ነበረባቸው። ማንም አመዛዛኝ ሰው እንኳን በሆቴል ክፍል ቀርቶ በገዛ ቤቱ ውስጥ ሳይታሰብ ሞቶ ከሆነ ወይም መሞቱ ጥርጣሬ ካሳደረ ተከትሎት ከሚመጣው አሉባልታም ይሁን ህጋዊ ጥያቄ ለመዳን አካባቢው ላይ ድርሽ አይልም።ምንም ነገር አይነካም። ዱካም ይሁን አሻራ እንዳይቀላቀል ፣ ማስረጃ እንዳይጠፋ አካባቢውን አስጠብቆ ለፖሊስ ያሳውቃል። ይሄ ማንም ሲያደርገው የኖረ የደመነፍስ እውቀት ነው። መማርና መመራመር አያስፈልገውም።

ፖሊስ በዚያ ወቅት ተጠርቶ ቢሆን ኖሮ ቢያንስ ይህንን ያደርጋል። ከገነነ አስከሬን ላይ አሻራ ይወስዳል። ገነነ አካሉ ላይ ያለ በአይን የሚታይ ጉዳት ካለ መላ ሰውነቱን ይፈትሻል።ተተኩሶበት ከሆነ መሳሪያው ከነአቀማመጡ፣ ታንቆ ከሆነም ገመዱ ከመነካካቱ በፊት ፎቶ ተነስቶ ለማስረጃ ይወሰዳል።ይህ አሻራ ከበሩ እጀታና ከቁልፉ አሻራ ጋር ‘ማች’ ስለሚደረግ አስፈላጊ ነው። በክፍሉ ውስጥ ሌላ ገነነ ህይወቱን አጥፍቶበታል፣ ወይም ህይወቱ ጠፍቶበታል ተብሎ የሚጠረጠር ምንም ነገር ካለ ለማስረጃ ይያዛል። ማስረጃዎች ሲሰበሰቡ ከዚያ ስለመገኘታቸው መርማሪው እዚያው ሆነው ሂደቱን ሲያዩ የነበሩ አንድ ሁለት ሰዎችን የታዛቢ (የደረጃ ምስክር) ቃል ይቀበላል። ይህ ባለመሆኑ ግን የገነነ አሟሟት ምርመራ ወሳኝ ምዕራፎች እንዲደበዝዙና እንዲታጠፉ ምክንያት ሆኗል።

ሶስተኛው ጥፋት ደግም ይኼ ነው። የገነነ ባለቤትም ይሁን ጓደኛው ሰይድ ኪያር ወይም የሆቴሉ ሰዎች ፍጹም ማድረግ ያልነበረባቸው ነገር የገነነን አስከሬን ወደቤት መውሰድ ነው። ይህ በፍጹም መደረግ ያልነበረበት ጥፋት ነው።እንዴት የፈለገ ቢደነግጡ፣ የፈለገ ቢዋከቡ ይህ ይጠፋቸዋል። የሰው ልጅ እንኳን ሞቶ ተገኝቶ ቀርቶ መኪና ገጭቶት ሞቶ ከሆነ እንኳን አስከሬኑ ወደሆስፒታል እንጂ ወደቤት አይወሰድም። አሟሟቱ የሚታወቅ ቢሆንም ተመርምሮ በህጋዊ አካል መረጋገጥና መመዝገብ አለበት። ይህ ህግ የሚያዘው ሰዎች የፈለገ ሟች ዘመዳቸውን ቢወድዱት ሊያስቀሩት የማይችል ሂደት ነው። አስከሬን ማንገላታት አይገባም እያሉ ፖሊስ ሳይመረምረው የቀበሩ ሰዎች እኮ ታስረው አስከሬኑም ተቆፍሮ ወጥቶ ተመርምሮ ያውቃል። ምክንያቱም ነገ ከሚከሰት ችግር ዛሬ የሚፈጠር መጉላላት ይቀልላል። ይህ ጥፋት በመፈጸሙ ግን ገነነ ታንቆ ሞተ ወይስ ሰው አንቆ ገደለው ወይስ በሌላ ምክንያት ሞተ የሚለውን መረጃ አዛብቶታል።

ፖሊስ አስከሬኑን አንስቶት ቢሆን ኖሮ በጥንቃቄ ጭኖ ወደሆስፒታል ለፎረንሲክ ፓቶሎጂ ምርመራ ይወስድና ያስረክብ ነበር። በዚህ መሃል የወሰደውን የገነነን አሻራ ሳምፕል ከበር እጀታና ቁልፍ ላይ ካገኘው አሻራ ጋር ‘ማች’ አድርጎ ትክክል ከመጣለት ገነነ በሰው ተገደለ የሚል እሳቤውን ትቶ የምርመራ ስኮፑን በማጥበብ ‘ራሱን አጥፍቷል’ በሚል ማጠቃለያ መዝገቡን ለመዝጋት ሆስፒታል የላከውን የገነነን አስከሬን የምርመራ ሪፖርት ይጠብቅ ነበር። ከዚያም ወዳጅ ዘመድም አዝኖ፣ የሚታማም የሚያማም ሳይኖር እውነቱ ፍርጥርጥ ብሎ ማንም የጎሪጥ ሳይተያይ ለሟች ሃዘን መቀመጥና ነፍስ ይማር ማለት በተቻለ ነበር።

በነገራችን ላይ የአስከሬን ምርመራ (ፎረንሲክ ፓቶሎጂ) የሚካሄደው በሁለት ደረጃ ነው። ቀዳሚውና የመጀመሪያ ደረጃ የሚባለው በአይን የሚታይ የአካል ክፍል ላይ የደረሰ ጉዳት ሲሆን ቀጣዩና የመጨረሻ ደረጃው በውስጥ አካል ብልት ላይ የደረሰ ጉዳት በምርመራ ሲረጋገጥ ሁለቱ ተጣምሮ የሚመጣው ውጤት ነው የአሟሟት ሁኔታን የሚወስነው። አቤት ሆስፒታል የሰጠው መረጃ ‘የሟች አንገት አካባቢ የገመድ ክርክር መታየቱን የሚገልጸው በእይታ እና አካል ፍተሻ የተገኘ የመጀመሪያ ደረጃ’ ሪፖርት ነው። ክርክሩና ቁስሉ ገነነ በገመድ ታንቆ ነበር የሚለውን እንጂ ራሱን አነቀ ወይም ታንቆ ሞተ የሚለውን አያረጋግጥም። ይህ ቢሆንማ ማንም ወንጀለኛ ሰው ገድሎ ‘ታንቆ ሞተ’ ለማስባል አንገቱ ላይ ገመድ አጥብቆ በማሰር ከፍትህ ዓይን መሰወር ይችል ነበር።

ገነነ ዊልቼየር ላይ ሆኖ ሳለ እንዴት በገመድ ታንቆ ሞተ ይባላል የሚል አስተያየትም አይቻለሁ። ታንቆ ለመሞት የግድ ኮርኒስ ላይ መንጠልጠል ግድ አይደለም። በራስ እጅ ራስን አንቆ መግደል ይቻላል ወይ የሚለው ላይ ከደመነፍስ መንፈራገጥ እና ከሞት በፊት ባለ ራስን መሳት ምክንያት ውጤቱ ሙሉ ሞትን ስለማምጣቱ ጥርጣሬ ቢኖረኝም
ገመድ ሸሽቀቆ ሳይሰሩ ሰዎች ራሳቸውን የሚያጠፉበትና ፖሊስም የሚያውቃቸው እዚህ ላይ መጥቀስ የማያስፈልጉ ዘዴዎች (Modes Operandi) አሉ። እሱ ይለፈን። ነገር ግን ገነነ ብዙ ነገር አዋቂ ስለሆነ በርግጥም በገመድ ራሱን አንቆ ከገደለ የሚፈጽምበት ዘዴ ከነዚያ መካከል አንዱ ነው።

ወደ ፓቶሎጂው ስመለስ …አንድ ሰው ሲታነቅ በአየር እጥረት ሳቢያ አንጎልን ጨምሮ ጉዳት የሚደርስባቸው የውስጥ አካል ብልቶች አሉት። አስከሬኑ ተከፍቶ ጉዳት የደረሰበት ብልት ተለይቶ የሚመረመረው ለዚያ ነው። አቤት ሆስፒታል በመጀመሪያ ደረጃ የእይታና አካል ፍተሻ ምርመራ ብቻ የገነነን ሞት አረጋግጦ ለፖሊስ ማረጋገጫ ሪፖርት ይጽፋል የሚል ዕምነት የለኝም። የገነነ አስከሬን ተከፍቶ ተመርምሯል የሚል ተስፋ ልያዝና የዚያ ምርመራ ውጤት ነው የመጀመሪያ ደረጃ ግምትን እውነትነት ወይም ስህተት መሆን የሚያረጋግጠው።

ስለዚህ ከላይ ያልነው ሁለተኛ ደረጃ ምርመራ ነው አሟሟቱን በደንብ የሚነግረን ።ፓቶሎጂስቶቹም ‘ገመዱን ፈልጉ’ ያሉት ምናልባት ምርመራው በመታነቅ መሞትን ካረጋገጠ ፖሊስ ማስረጃ እንዲኖረው ብለው እንጂ ለነሱ ስራ ምንም አያደርግላቸውም። ፖሊስ ግን ሰዎቹ በፈጸሙት ስህተት ጉዳዩ ወደወንጀል አምርቶ ተጠርጣሪ ቢይዝ እንኳን ህግ አራት ማዕዘን ሳጥን ነውና የተከሳሽ ጠበቆች ለሚያነሱት ክርክር ማርከሻ የሚሆን የዐቃቢ ህግ መከራከሪያ የሆነ ወሳኝ ማስረጃ አጥቷል።

ነገሩን ስንጠቀልለው ገነነን ሰው ገደለው ወይስ ራሱን ገደለ የሚለውን ለመደምደም ብቸኛው እድል የፎረንሲክ ፓቶሎጂው ሁለተኛና የመጨረሻ ምርመራ ሪፖርት ነው። እንደኔ ግምት በተሰራው ጥፋት የተነሳ ከፓቶሎጂ ውጤት ባሻገር ፖሊስ የቴክኒክ ምርመራ በማጠናቀር ወደአሟሟቱ ምስጢር የሚወስደውንና አባሪ ማረጋገጫ የሚሆነውን ማስረጃ በእጁ መያዝ የሚችልበት እድል አምልጧል ።ከሰዎች የሚገኝ የታክቲክ ማስረጃ ደግሞ ጉዳዩ ሽፍን ስለሆነ ለምርመራው ብዙም የሚደግፈው አይሆንም።

እንግዲህ የፓቶሎጂስቶቹ ሪፖርት ፖሊስ እጅ ሲገባ የሚያመለክተው አቅጣጫ ሰሞኑን ግልጽ የሚሆን ይመስለኛል። አሁን አንድ ምኒልክ ሆስፒታል ብቻ የነበረው ምርመራ ብዙ ቦታ ስላለ እንደድሮው ጊዜ አይፈጅም። ከዚያ በኋላ ነው ዋናውን እውነት የምናውቀው።

እስከዚያው ድረስ በቅን ልቡና በመነሳሳት ወይም ባለማወቅ ወይም በግዴለሽነት ወይም በሌላ ምክንያት የተሰራው ጥፋት እንዳለ ሆኖ ማንንም ከማማትና በጥርጣሬ የቤተሰብን ሃዘን ከመበረዝ ተጠብቀን የገነነን አሟሟት ለመደምደም የፖሊስ መግለጫን መጠበቅ የተሻለ ይመስለኛል።አዲስ አበባ ፖሊስ የገነነ ጉዳይ የብዙ ሰዎች ‘ኮንሰርን’ መሆኑን ስለሚገነዘብ ብዠታዎችን ለማጥራት በዚህ ጉዳይ ላይ መግለጫ ይሰጣል ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ።በዚያውም በቸልተኝነት ወይም በቅን ልቡና በሚደረግ ተግባር ወንጀል ተድበስብሶ ሊቀር የሚችልበት እድል ስለሚሰፋ ለሌሎች ትምህርት የሚሆን ነገር ይናገራል ብዬ አምናለሁ።

የፖሊስ ምርመራ ሁለት አላማ አለው። አንድም ንጽህናን ሌላም ጥፋተኝነትን ማረጋገጥ ነው። የገነነ ባለቤትና እነሰኢድ አሁን ሶሻል ሚዲያ ላይ ከሚነሳው ስማቸው ነጻ የሚወጡት በዚህ ምርመራ ውጤት ብቻ ነው። አስቀድመው ተጠንቅቀው ቢሆን ንጽህናቸውን በራሳቸው ማረጋገጥ ፣ሃዘናቸውንም በቅጡ መወጣት በቻሉ ነበር።

ሁሉን ነገር ሲያውቅ የራሱን ጉዳይ ግን ‘ሆድ ይፍጀው’ ብሎ የቤት ስራ ሰጥቶ የተሰናበተን አንጋፋው ጋዜጠኛና ታሪክ አዋቂ ገኔ ግን እግዚአብሄር በሰማይ ነፍሱን ይማርልን።የ40 ዓመት ጋዜጠኝነት ህይወቱ ስሙን ሁሌም ከመቃብር በላይ ያውለዋል።

ገኔ ! በሰላም እረፍ!!

(መላኩ ብርሃኑ )