January 30, 2024 – Konjit Sitotaw

በራያ የሚገኙ ስድስት ወረዳዎች ሕዝበ ውሳኔ ተደርጎ የማንነት ጥያቄያቸው ባለመፈታቱ ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን የኮረም ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ገብረ እግዚዓብሔር ደረጀ ለዋዜማ ተናግረዋል።

ባለፈው ነሐሴ በቅርቡ ሕዝብ ውሳኔ ይደረጋል በሚል ከመከላከያ ሠራዊት አመራሮች ጋር ውይይት ተደርጎ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው፣ ከዚያ በኋላ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳልተደረገ ተናግረዋል።

የፌደራል መንግሥቱ ከጦርነቱ በኋላ ለትግራይ ክልል የተለያዩ ድጎማዎችን ሲያደርግ ራያን ለይቶ ትቶታል ያሉት ኃላፊው፣ ባኹኑ ወቅት የአካባቢው አስተዳደር የሚንቀሳቀሰው የአማራ ክልላዊ መንግሥት በሚያደርግለት ውስን ድጎማ ነው ብለዋል።

በበጀት እጥረት ምክንያት የጤና ተቋማት የተሟላ አገልግሎት እንደማይሰጡ፣ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት መኖሩን እንዱኹም የወደሙ የትምህርት ቤቶች አለመጠገናቸውንና የመንገድና ሌሎች መሠረት ልማት ማስፋፊያዎች አለመኖራቸውን ኃላፊው ገልጸዋል።

ሕዝብ ውሳኔ እንዲደረግላቸው የሚጠየቁት፣ በዋግኽምራ ዞን ሥር የኮረም ከተማ አስተዳደር፣ ወፍላ እና ዛታ ወረዳዎች እንዲኹም በሰሜን ውሎ ዞን አላማጣ ከተማና ራያ አላማጣ እና ራያ ባላ ወረዳዎች መኾናቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።