January 30, 2024 – Konjit Sitotaw

በአሜሪካ ሕግ መምሪያ የእንደራሲዎች ምክር ቤት አባል ትውልደ ሱማሊያዊቷ ኢልሃን ኦማር፣ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ተፈጻሚ ሊኾን አይችልም በማለት መናገራቸውን የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል።

ኢልሃን ኦማር ሚኖሶታ ግዛት ውስጥ ለሱማሊያዊያንና ትውልደ ሱማሊያዊያን በሱማሊኛ ቋንቋ ባደረጉት ንግግር፣ እኔ የአሜሪካ ኮንግሬስ ውስጥ ተቀምጩ የሱማሊያን መሬት ማንም ፈጽሞ ሊወስደው አይችልም በማለት መዛታቸውን ዘገባዎቹ አመልክተዋል።

ሱማሊያ ድሮ የተወሰዱባት ግዛቶች አሉ ያሉት ኦማር፣ አንድ ቀን ግዛቶቻችን እናስመልሳለን በማለት መዛታቸውንም ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል።

የኦማር ዛቻ፣ የኢትዮጵያው ኦጋዴንና የሰሜናዊ ኬንያ አካባቢዎች የታላቋ ሱማሊያ አካል ናቸው የሚለውን የተስፋፊውንና ወራሪውን የቀድሞው የሱማሊያ ወታደራዊ መሪ ጀኔራል ዚያድ ባሬን ፖሊሲ የሚያራምድ ነው በሚል በርካታ ትችት እየተሰነዘረባቸው ይገኛል።