ኢሰመጉ በአማራና ትግራይ ክልሎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ወደቀያቸው ባለመመለሳቸው ለሞት፣ ለከፍተኛ ርሃብ እና የተለያዩ ሰብዓዊ ቀውሶች ተጋልጠዋል ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ገልጧል።
ኢሰመጉ፣ በትግራይ ክልል በሽረ፣ አክሱም፣ አቢአዲ፣ መቀሌ እና አዲግራት ከተሞች የሚገኙ ተፈናቃዮች፣ የረድዔት ድርጅቶች የምግብ ዕርዳታ በመቋረጡና የፌደራሉና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በቂ ሰብዓዊ ድጋፍ ባለማቅረባቸው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በርሃብ ለሞት እንደተዳረጉ አረጋግጫለኹ ብሏል።
በአማራ ክልልም በማዕከላዊ ጎንደር፣ በደቡብ ወሎ፣ በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን፣ በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞንና በሰሜን ጎንደር ዞን የጃናሞራና ጠለምት አካባቢዎች፣ ከባድ ድርቅ እንደተከሰተ ኢሰመጉ አስታውቋል።
በድርቁ ሳቢያ በርካታ ሰዎችና እንስሳት እየሞቱ ነው ያለው ኢሰመጉ፣ ባካባቢዎቹ ባለው የጸጥታ ኹኔታ ሳቢያ በቂ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ እንዳልተቻለ መረዳቱንም ኢሰመጉ ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በትግራይና በአማራ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅና ድርቁ የደረሰውን ሰብዓዊ ጉዳት አስመልከቶ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ በትግራይ ማዕከላዊ ዞን 351 ሰዎች በምግብ እጥረት ሲሞቱ፣ 15 ሺሕ 565 ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ገልጧል። በርካታ ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታቸው ውጪ መኾናቸውን ተቋሙ አስታውቋል።
በአማራ ክልልም፣ በድርቅ ከ325 ሺህ በላይ መሬት ከምርት ውጪ መኾኑ፣ በዘጠኝ ዞኖች ከ 1 ሚሊዮን 800 ሺሕ በላይ ዜጎች ለከፋ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ እንደተዳረጉና ከ26 ሺህ በላይ ሰዎች በወባና ኮሌራ በሽታዎች መጠቃታቸውን ጠቅሷል። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙና በቂ የሆነ ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳልኾነም ገልጧል።