የደቡብ አፍሪካ ተጫዋቾች

ከ 5 ሰአት በፊት

የዘንድሮ የአፍሪካ ዋንጫ የአሸናፊነት ግምት የተሰጣቸው አገራት ብዙ ትኩረት ባልተሰጣቸው አገራት መሸነፋቸውን ቀጥለዋል።

ትልቅ የዋንጫ ግምት የተሰጣት ሞሮኮ በደቡብ አፍሪካ 2 ለ 0 ተሸንፋ ከውድድሩ ተሰናብታለች።

በትናንት ምሽቱ ጨዋታ ባፋና ባፋናዎች በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው 2 ጎሎችን ሞሮኮን አሸንፈው ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል።

ከዚህ ጨዋታ በፊት ቀድሞ በተካሄደው ጨዋታ ማሊ እና ቡርኪና ፋሶ ተገኝተው የነበረ ሲሆን ማሊ ጨዋታውን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፋለች።

በመጀመሪያው አጋማሽ የቡርኪና ፋሶው ተከላካይ በራሱ ግብ ላይ ጎል አስቆጥሮ ማሊ 1ለ0 እየመራች እረፍት ወጥተዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ አጥቅታ ስትጫወት የነበረችው ማሊ በሲናዮኮ አማካይነት ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችላለች።

በማሊ የግብ ክልል ውስጥ ኳስ በእጅ በመነካቱ ቡርኪና ፋሶ ፍፁም ቅጣት ምት አግኝታ ትራኦሬ ወደ ጎል ቀይሮት ቡርኪና ፋሶ ወደ ጨዋታው ተመልሳ ነበር። ይሁን እንጂ ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር ባለመቻላቸው ጨዋታው 2ለ1 በሆነ ውጤት ተጠናቅቋል።

ማሊ በሩብ ፍፃሜው የፊታችን ቅዳሜ ከአስተናጋጇ አይቮሪ ኮስት ጋር ትገናኛለች።

ሳይጠበቅ ሞሮኮን 2 ለ 0 ያሸነፈችው ደቡብ አፍሪካ ደግሞ የፊታችን ቅዳሜ ከኬፕ ቨርድ ጋር የምትገናኝ ይሆናል።

ትናንት በነበረው ጨዋታ ሁሉም ቡድኖች ከእረፍት በፊት ግብ ማስቆጠር አልቻሉም ነበር።

አጥቂው ማክጎፓ በ57 ደቂቃ ደቡብ አፍሪካን ቀዳሚ ማድረግ ችሎ ነበር። ጨዋታ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ሞሮኮ ወደ ጨዋታው ልትመለስ የምትችልበትን ወርቃማ ዕድል ሳትጠቀምበት ቀርታለች።

ኳስ በእጅ መነካቱን ተከትሎ ሞሮኮ ፍጹም ቅጣት ምት ብታገኝም ተከላካዩ አሽራፍ ሃኪሚ ኳሷን ከግቡ አግዳሚ ጋር አጋጭቶ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

90ኛው ዲቀቃ የማንቸስተር ዩናይትድ ተጫዋቹ አምራባት በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቱ ደግሞ የሞሮኮን ፈተና የበለጠ ያወሳሰበ ሆኖ ነበር።

በጨዋታ ማብቂያው ላይ ቶቦሆ ሞኮኤና ከቅጣት ምት ድንቅ ጎል አስቆጥሮ የደቡብ አፍሪካን ድል አረጋግጧል።

በቀሪዎቹ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ናይጄሪያ ከአንጎላ ዓርብ ምሽት የሚገናኙ ሲሆን፤ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደግሞ ከጊኒ ጋር በተመሳሳይ ዓርብ ምሽት የሚጫወቱ ይሆናል።