የኢራቅ ሚሊሻ አባላት

ከ 4 ሰአት በፊት

በዮርዳኖስ ሦስት የአሜሪካ ወታደሮች የተገደሉበትን ጥቃት እንደፈጸመ የተጠረጠረ በኢራቅ የሚገኝ ታጣቂ ቡድን አሜሪካ ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት ማቆሙን አስታወቀ።

ካታይብ ሄዝቦላህ የተባለው እና ከኢራን ጋር ግንኙነት ያለው ታጣቂ ቡድን ለዚህ ውሳኔው ምክንያቱን ሲገልጽ “የኢራቅ መንግሥት ሊደርስበት የሚችለውን አሳፋሪ ምላሽ ለመከላከል ነው” ብሏል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ዕሁድ በዮርዳኖስ የሚገኘው የአሜሪካ የጦር ሰፈር ላይ ለተፈጸመው እና ለሦስት ወታደሮች ሞት ምክንያት ለሆነው ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ የሚሰጥበትን መንገድ መወሰናቸውን ገልጸዋል። ሆኖም አጸፋው በምን መልኩ ይሆናል የሚለውን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

አሜሪካ በተደጋጋሚ የአጸፋ ምላሹ ወታደራዊ ጥቃት ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ሰጥታለች።

ከእሁዱ ጥቃት ጀርባ ነበርኩ ያለው ካታይብ ሄዝቦላህ የጸጥታ ዘርፍ ዋና ጸሀፊ አቡ ሁሴን አል ሃሚዳዊ ባወጣው መግለጫ “በኢራቅ መንግሥት ላይ የሚደርሰውን አሳፋሪ ምላሽ ለመከላከል በሚል ወራሪ ኃይሎች ላይ የምንወስደውን እርምጃ ብናቋርጥም በጋዛ ህዝባችንን መከላከል እንቀጥላለን” ብሏል።

ባለፈው ዕሁድ በዮርዳኖስ እና ሶሪያ ድንበር አከባቢ የተፈጸመው ጥቃት በኢራን ሰራሽ ድሮን እንደሆነ ተዘግቧል።

በዚህ ጥቃት ሶስት ወታደሮች ከመገደላቸው በተጨማሪ በርካታ የአሜሪካ ወታደሮችም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

አሜሪካ ይህንን ጥቃት የፈጸሙት በኢራን የሚደገፉ ኃይሎች ናቸው ብትልም ካታይብ ሄዝቦላህ የጥቃቱ ፈጻሚ ነው ብላ አልደመደመችም።

ታጣቂ ቡድኑ አሜሪካ ላይ ጥቃት መሰንዘሬን አቁሜያለሁ ማለቱን ተከትሎ የፔንታገን ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ “ድርጊት ከቃል በላይ ይናገራል” ሲሉ ተደምጠዋል።

ቃል አቀባዩ ፓት ራይደር አክለውም ድርጊቱ ከባድ መዘዝ እንደሚያስከትልም አክለዋል።

በሌላ ዜና አሜሪካ ጥቃት የደረሰበት እና በዮርዳኖስ በሚገኘውን የጦር ሰፈር ጥበቃ እያጠናከረች ትገኛለች። ሰፈሩ የአሜሪካ የኢስላሚክ ስቴት ጥቃትን ለመከላክል ነበር የተቋቋመው።

የድሮኖችን ጉዞ የሚያጨናግፉ ዘዴ ጨምሮ ተጨማሪ የመከላከያ ወደ ስፍራው መላኩን የቢቢሲ ምንጮች ገልጸዋል።

የአሜሪካ ምክር ቤት የደኅንነት ኮሚቴ ሊቀ መንበር ማይክ ተርነር የዮርዳኖሱን ጥቃት ጨምሮ ሁቲ በቀይ ባህር መርከቦች ላይ እየፈጸመ ለሚገኘው ጥቃት “ያለጥርጥር ኃላፊነቱን የሚወስደውን አካል የሚጠቁሙት መንገዶች በሙሉ ወደ ኢራን የሚወስዱ ናቸው” ብለዋል።

ጨምረውም “በሚገባቸው መንገድ ምላሽ መሰጠት አለበት፣ ተከላካይ ብቻ ሆነን አንቀጥልም” ሲሉ ገልጸዋል።

በተጨማሪም አሜሪካ የምትወስደው እርምጃ እና እየተካሄደ ያለው ግጭት የኢራን በር ጋር የሚደርስ እንደሆነ እንድትረዳው የሚያደርግ ነውም ብለዋል።

አሜሪካ በኢራን የሚደገፉ ታጣቂ ቡድኖች ላይ ደብደባ በመፈጸም ወታደሮቿን ለገደለው ጥቃት የአጸፋ ምላሽ ልትሰጥ ትችላለች።

አልያም በኢራቅ ወይም ሶሪያ የሚገኙ የኢራን እስላማዊ አብዮት ዘብ ከፍተኛ መሪዎችን ኢላማ ልታደርግ እንደምትችልም ተገምቷል።

ወይም ከፍተኛ ውጥረት ሊያስከት የሚችለውን እርምጃ በኢራን ደንበር ውስጥ ልትወስድ እንደምትችልም ተዘግቧል።