የጋዛ ውድመት

ከ 4 ሰአት በፊት

እስራኤል መስከረም 26 ጥቃት ከተፈጸመባት በኋላ በጋዛ እየፈጸመች ባለችው ወታደራዊ ዘመቻ ቢያንስ ግማሽ የሚሆነው የጋዛ ሕንጻዎችን ማውደሟን የቢቢሲ ምርመራ አመለከተ።

ከጦርነቱ በፊት የተነሱ ምስሎች አሁን ካለው ጋር ሲነጻጸሩ በደቡባዊ እና መካከለኛው ጋዛ የደረሰውን ከፍተኛ ውድመት ያሳያሉ።

የጋዛ ነዋሪዎች የመኖሪያ መንደሮች ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል። ብዙዎች የሚገበያዩባቸው ቦታዎች እንዳልነበሩ ሆነዋል። የዩኒቨርሲቲ ሕንጻዎች ሙሉ በሙሉ ወድመው ጋዛ ከላስቲክ በተሰሩ መጠለያዎች ተሸፍናለች።

በዚህ ጦርነት አብዛኛዎቹ ሕጻናት እና ሴቶች የሆኑ ከ26ሺህ ያላነሱ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከአጠቃላይ የጋዛ ነዋሪ 80 በመቶ የሚሆነው 1.7 ሚሊዮን ሕዝብ ከመኖሪያው ተፈናቅሏል።

በዚህ ሁሉ ውድመት ውስጥ ግን የእስራኤል ጦር እያደረገ ባለው ጥቃት ዒላማ እያደረገ ያለው ሐማስን እና የሐማስ መሠረተ ልማቶችን ብቻ መሆኑን ይገልጻል።

ቢቢሲ የሳተላይት ምስሎችን ተመልክቶ በሰራው ትንተና ከ114ሺህ እስከ 175ሺህ የሚሆኑ የተለያየ መጠን ያላቸው ሕንጻዎች በእስራኤል የቦምብ ድብደባ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይተረዋል።

ይህ አሃዝ ታዲያ ከ50-61 በመቶ የሚሆነው የጋዛ ሕንጻ መውደሙን ያመለክታል።

በቅርብ ወራት ደግሞ በደቡባ ጋዛ የምትገኘው ኻን ዩኒስ ከፍተኛ ውድመት ካጋጠማቸው አካባቢዎች አንዷ ነች። ከ38ሺህ በላይ ሕንጻዎች ውድመት አጋጥሟቸዋል። በኻን ዮኒስ ባለ 16 ፎቁ ረዥሙ ሕንጻ አል-ፋራ ታዎር አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ በቦታው የለም።

በጋዛ ተዋቂ የነበረው ሳናበል ሸዋርማ ምግብ ቤት ሕንጻ አሁን እንዳልነበር ሆኗል።

“የእስራኤል ወታደሮች በኻን ዩኒስ መሃል ከተማ መኖሪያ ሕንጻዎችን ዒላማ ሲያደርጉ ነበር” በማለት ከመኖሪያዋ ተፈናቅላ የምትገኘው የ20 ዓመቷ የጋዛ ነዋሪው ራዋን ቃዳህ ለቢቢሲ ተናግረዋለቸ።

የእስራኤል ጦር በተደጋጋሚ የሐማስ ታጣቂዎች በሰላማዊ ሰዎች መገኛ ቦታዎች እራሳቸውን እየሸሸጉ ነው ከማለቱ በተጨማሪ ሐማስ መሠረተ ልማቶቹን የገነባው እንደ ሆስፒታል እና ትምህርት ቤት ሥር ባሉ ዋሸዎች ውስጥ ነው ሲል ቆይቷል።

በእስራኤል ጦር ውድመት ያጋጠማቸው ግንባታዎች ብቻ ሳይሆኑ የእርሻ መሬቶችንም ወድመዋል፤ አስፓልት መንገዶችም ተቆፍረዋል።

ለቢቢሲ አረብኛ ቃላቸውን የሰጡ ሰዒድ የተባሉ አርሶ አደር እንደ ሎሚ እና ብርቱኳን ያሉ ምርቶችን የሚምርቱበት የእርሻ መሬታቸው በእስራኤል ጦር ሙሉ በሙሉ እንዲወድም በመደረጉ ከመላ ቤተሰባቸው ጋር ቀያቸውን ጥለው ለመሰደድ መገደዳቸውን ገልጸዋል።

ቢቢሲ ከገለልተኛ ወገን ባያረጋግጥም የእስራኤል ጦር ሆነ ብሎ በቡልዶዘር የእርሻ መሬቶችን እና መንገዶችን ቆፍሯል።

ይህ ክስ እውነት ሊሆን የሚያመላክት የሚችል ቃል መጠይቅ በእስራኤል ጦር ከሁለት ወራት በፊት ተለቆ ነበር።

በዛ ቪዲዮ ላይ የእስራኤል ጦር ከፍተኛ አመራር የሆኑት ኮለኔል ዮጌቭ ባር-ሼሽተ ቃለ መጠይቅ ሲሰጡ፤ “ወዲህ የሚመለስ ካለ፤ የተቆፈረ መሬት ነው የሚያገኘው። መኖሪያ ቤት የሌለበት፣ የእርሻ መሬት የሌለበት፣ ምንም የሌለበት ነው የሚያገኙት። በዚህም ምንም ሕይወት አይኖራቸውም” ሲሉ ተደምጠዋል።