ኢምራን ካሃን ከባለቤታቸው ቡሽራ ቢቢ ጋር
የምስሉ መግለጫ,ኢምራን ካሃን ከባለቤታቸው ቡሽራ ቢቢ ጋር

ከ 2 ሰአት በፊት

የቀድሞው የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካሃን ከባለቤታቸው ጋር የ14 ዓመት እስር ተፈረደባቸው።

ካሃን ይህ ፍርድ የተላለፈባቸው በሌላ ወንጀል 10 ዓመት ከፈረደባቸው ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

እአአ 2022 በተቃዋሚዎቻቸው ከሥልጣን የተነሱት ኢምራን ከሃን በአሁኑ ወቅት በሙስና ወንጀል 3 ዓመት ተፈርዶባቸው በእስር ላይ ይገኛሉ።

ማክሰኞ ዕለት የአገር ምሥጢር በማውጣት 10 ዓመት ከተፈረደባቸው በኋላ ዛሬ ረቡዕ ደግሞ በሙስና ወንጀል 14 ዓመት ተፈርዶባቸዋል። የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የተላለፈባቸውን የእስር ቅጣቶች በተመሳሳይ ጊዜ የሚፈጸሙ ይሆናሉ።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ግን እነዚህ ክሶች ፖለቲካዊ ናቸው ይላሉ።

ካህን እነዚህ ቅጣቶች የተላለፉባቸው አገራቸው ፓኪስታን አገራዊ ምርጫ ለማድረግ አንድ ሳምንት ብቻ ሲቀራት ነው። ካህን በዚህ ምርጫ እንዳይሳተፉ የተጋዱ ሲሆን፣ ፓርቲያቸው ፓኪስታን ቴህሬክ-ኢ-ኢንሳፍ የተለያዩ የምርጫ ቅስቀሳ ገደቦች ተጥለውበታል።

ዛሬ የተላለፈውን ፍርድ ተከትሎ የኢምራን ካሃን ባለቤት ቡሽራ ቢቢ ባለቤታቸው ታስረው በሚገኙበት እስር ቤት ተገኝተው እጅ ሰጥተዋል።

ኢምራን ካሃን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እያገለገሉ ባሉበት ወቅት ጥንዶቹ የተሰጧቸውን ስጦታዎች ሽጠዋል በሚል የቀረቡባቸውን ክሶች አጣጥለዋል።

ካህን እና ባለቤታቸወ ከተላለፋባቸው የእስር ቅጣቶች በተጨማሪ 5.3 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ ተፈርዶባቸዋል።

የኢምራን ካሃን ፓርቲ ፓኪስታን ቴህሬክ-ኢ-ኢንሳፍ ፍርዱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ለ10 ዓመታት በምርጫ እንዳይሳተፉ የሚያደርግ ነው ብሏል።

የፓርቲው ቃል አቀባይ “በፍትሕ ሥርዓታችን ውስጥ አሳዛኙ ቀን” ሲሉ የፍርድ ውሳኔውን ገልጸውታል።

ኢምራን ካሃን አገራዊ ምሥጢር አውጥተው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን አሻክረዋል ተብለው የተላለፈባቸውን ፍርድ አጥብቀው ተችተዋል።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ፓርቲያቸው የቀረቡትን ክሶች “ሐሰተኛ” እንዲሁም ውሳኔውን ያስተላለፈባቸው ፍርድ ቤት የቡድኖችን ፍላጎት እንዲያስፈጸም የተቋቋመ ችሎት ነው ብለውታል።

ቀድሞ ታዋቂ የክሪኬት ስፖርት ተጫዋች የነበሩት ካህን፣ ደጋፊዎቻቸው ከሳምንት በኋላ በሚደረገው ምርጫ ሰላማዊ መንገድን በመጠቀም ለእያንዳንዱ ኢ-ፍትሐዊ አሰራር ድምጽ በመከልከል እንዲበቀሉ ጠይቀዋል።