
ከ 6 ሰአት በፊት
“ዳይ! ጫማችሁን አውልቁ!፣ እጅ ለእጅ ተያያዙ!” የሚል ጊዜ የማይሰጥ ትዕዛዝ ወረደ።
ጨለማው፣ ጉዞው፣ ጭንቀቱ እና ረሃቡ አክስሏቸዋል። አብዛኛዎቹ ተጠርጣሪዎች በእጃቸው ያንጠለጠሉት ምንም ነገር የለም።
ያደረጉትን ጫማ በፍጥነት እያወለቁ ወረወሩ።
በእንቅልፍ እጦት በተጨናበሰው ዐይናቸው ያሉበትን አካባቢ ለመረዳት እንኳ ፋታ አላገኙም።
በባዶ እግራቸው በጠጠሩ እና በአሸዋ ላይ እንደምንም እየተራመዱ ወደ ግቢው ዘለቁ።
በብሎኬት ወደተሠራ አዳራሽ መሯቸው።
በውስጡ ምንም ዓይነት ፍራሽም ሆነ ምንጣፍ አሊያም ወንበር የለም።
“ያመናጭቁን፣ ያጥላሉን ነበር። በአካባቢው ካለው ኦናነት በላይ ጩኸታቸው ያስበረግግ ነበር” ይላል።
የሚላስም ሆነ የሚቀመስ የለም። በባዶው ክፍል ያለምንም የመኝታ ቦታ፣ ያለምንም አልባሳት እንዲተኙ ታዘዙ።
ወለሉ ላይ ተቀመጡ። ነገ ምን እንደሚጠብቃቸው አያውቁም እና በተቀመጡበት ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈው ዓይናቸውን ከደኑ።
ለሰብዓዊ መብት አብዝቶ የሚቆረቆረው የዞን ዘጠኙ ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ መስከረም 22/2009 ዓ.ም. በኢሬቻ በዓል ላይ ከደረሰው እልቂት በኋላ በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ነበር በቁጥጥር ሥር የዋለው።
የሆነው እንዲህ ነበር።
ኅዳር 2009 ዓ.ም. ማለዳ 12፡30።
ወቅቱ ደግሞ በ2009 ዓ.ም. በኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ በተከሰተው እልቂት የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበት።
የበፍቃዱ ቤት በር ተንኳኳ። በሩን ሲከፍት ፊት ለፊት ሲቪል ከለበሱ የፀጥታ ኃይሎች ጋር ተገጣጠመ።
“ለጥያቄ ስለምንፈልግህ ወደ ጣቢያ ልንወስድህ ነው!” የፀጥታ ኃይሎቹ ቆፍጠን ያለ ጥያቄ አቀረቡ።
“ፖሊስ መሆናችሁን እንዴት ማወቅ እችላለሁ?” ሲፈራ ሲቸር የሰነዘረው ጥያቄ ነበር።
አንደኛው ፖሊስ መታወቂያውን አውጥቶ ካሳየው በኋላ በአቅራቢያው ወደ ሚገኘው የፈረንሳይ ለጋሲዎን ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱት። ቀደም ብሎም የመንግሥት ዒላማ ስለነበር በፖሊስ መያዙ በፍቃዱን አላስበረገገውም።
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እና ማለዳው ተደማምሮ አካባቢውን ፀጥ ረጭ አድርጎታል።
በፍቃዱ ከለበሰው ሹራብ እና ቱታ፣ ካደረገው ነጠላ ጫማ ውጪ በእጁ ያንጠለጠለው አንዳች ነገር የለም።
ፖሊስ ጣቢያው እንደደረሱ ቃሉን ተቀብለውት ከሰዓታት በኋላ ወደ የካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወሰዱት።
እዚያም አንድ ቀን ካደረ በኋላ በነጋታው ‘መሪ’ የሚባል ፖሊስ ጣቢያ አስገቡት። እዚያ የነበሩ ሰባት እስረኞችን ተቀላቀለ። ሰባቱም እስረኞች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተያዙ ነበሩ።
ጣቢያው ከተከፈተ አዲስ ይመስላል።
“በተለምዶ ‘ደያስ’ የሚባለው በቅጡ የማይሠራው የምግብ አቅርቦት እንኳን አልነበረም” ይላል።
በዚህ አሰቃቂ ክፍል ውስጥ መቆየቱ በፍቃዱን አሳሰበው።
አንድ ቀን እስረኛ ለመጎብኘት የመጣ ኮማንደርን አግኝቶ “እባካችሁ ወደ ሌላ ቦታ አዛውሩኝ?” ሲል ተማጸነ። ያገኘው ምላሽ ‘የባሰ አለ አገርህን አትልቀቅ’ ዓይነት ነበር።
“ሌሎቹ ሙሉ ናቸው። ወደ ፈረንሳይ ብንወስድህ እዚያም ሙሉ ነው። ከመሙላቱ የተነሳ ታሳሪዎች የሚተኙት በፈረቃ ነው። እዚህ ይሻልሃል” የሚል። በዚህ ሁኔታ አምስት ቀናት አለፉ።
በስድስተኛው ቀን ቀድሞ የተያዘ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ስለነበረው ወደ የካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወሰዱት።
ወደነበረበት እንደሚመለስ ነበር ግምቱ። የታቀደው ግን ሌላ ነበር።
በአውቶብስ እንዲሳፈር ትዕዛዝ ተሰጠው። ወዴት ሊወሰዱት እንደሆነ ፍንጭ እንኳ አላገኘም። ተሳፈረ።
አውቶብሱ ከተማ ውስጥ መዟዟር ጀመረ። እስረኞችን ከያሉበት እየለቀመ ነበር። እኩለ ቀን ላይ ጀምረው በከተማው የሚገኙ ማቆያዎች እና እስር ቤቶች ውስጥ የነበሩ እስረኞች እነበፍቃዱን ተቀላቀሉ። አመሻሹ ላይ አውቶብሱ ጉዞ ጀመረ። ሁሉም በግራ መጋባት ስሜት ውስጥ ነበሩ።
የተሳፈሩበት አውቶብስ ወደ ቱሉ ዲምቱ አቅጣጫ አፍንጫውን ሲያዞር ልቡ አንድ ነገር ሹክ አለው። አዋሽ!
በፍቃዱ ቀደም ብሎ አዋሽ በሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ በእስር አሳልፈው የወጡ ግለሰቦችን አነጋግሮ ያውቃል። ለዚህም ነው ስለሚወሰዱበት ቦታ የገመተው።
- አዋሽ አርባ፡ በኢትዮጵያ ከጅምላ እስር ጋር ስሙ የሚነሳው ‘የበረሃው ጓንታናሞ’24 ጥር 2024
- አዋሽ አርባ ታስረው የነበሩ የምክር ቤት አባላት እና ጋዜጠኛ ወደ አዲስ አበባ ተዘዋወሩ29 ጥር 2024
- ‘ተዉኝ ልኑርበት!’. . . ዜጎች መረጃ ለመስጠት ያለባቸው ስጋት እና የመገናኛ ብዙኃን ፈተና26 ጥር 2024
ጉዞ ወደ አዋሽ
በፍቃዱ ወደ አካባቢው እስረኛ ሆኖ ሲሄድ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም በሥራው አጋጣሚ እዚያ በእስር አሳልፈው የነበሩ ሰዎች ምን ያህል የማሰቃየት ተግባር እንደተፈፀመባቸው ስለሚያውቅ ግፉን ከወዲሁ እያሰበው ያንገፈግፈው ጀመር።
ጉዞው የተንቀራፈፈ ነበር። ለምን እንደሚንቀራፈፍ አልገባውም።
ወደ ፈጣን መንገዱ የክፍያ ጣቢያ ሲቃረቡ አውቶብሱ ዳር ይዞ ቆመ። በዐይኑ ሲያማትር ሌሎች መሰል ሁለት አውቶቡሶች ቆመው ተመለከተ። ቀስ እያለ የአውቶብሶቹ ቁጥር አምስት ደረሰ።
እየተጠባበቁ ሁሉም በአንድ መስመር ጉዟቸውን ቀጠሉ።
በፍቃዱ በተሳፈረበት አውቶብስ ውስጥ ሴቶችም እንደነበሩ ያስታውሳል።
እየመሸ ሲመጣ ሁሉም መረበሽ ጀመሩ። ወዴት እንደሚወስዷቸው፣ ለምን እንደሆነ የሚወስዷቸው የነገራቸው የለም።
በፍቃዱ እንደሚለው እንኳንስ እነሱ አውቶብሶቹን የሚያሽከረክሩት ሹፌሮችም ወዴት እንደሚጓዙ የሚያውቁ አይመስሉም ነበር።
መንታ መንገዶች ላይ በደረሱ ቁጥር ወዴት እንደሚታጠፉ ከጠባቂ ፖሊሶች ጠይቀው ነበር የሚረዱት።
ፖሊሶቹ ደግሞ ከሚያዛቸው አካል በስልክ ይጠይቃሉ።
ይህ በበርካቶች ዘንድ ጭንቀትን ፈጥሮ ነበር።
“በቃ የሆነ ቦታ ወስደው ሊረሽኑን ነው የሚል የከፋ እሳቤ ጭምር ነበር” ይላል።
“የት ነው የምንሄደው?” ሲሏቸውም አይነግሯቸውም። አውቶብሶቹ እየተጠባበቁ ነበር የሚሄዱት። የተደገነ መትረየስ በተጫነባቸው ፒክ አፕ መኪኞች ታጅበዋል።
ድባቡ የሚያስፈራ ነበር። ይህንን ዝምታ እና ጭንቀት ለመስበር አንዳንዶች ቀልድ ቢጤ ጣል ያደርጉ ነበር። ቀልዱ ግን ብልጭ ብሎ ወዲያው ድርግም ይላል። ማንንም አያስፈግግም።
ወደ አዋሽ ወደሚወስደው መንገድ ከታጠፉ በኋላ “ወዴት እንግባ?” ሲሉ ሹፌሮች ጠየቁ። የሚመልስላቸው አልነበረም። አቅጣጫ ጠቋሚዎቹም ስልክ አያነሱም።
ሹፌሩም፣ ታሳሪውም ጠባቂዎቹም ግራ ተጋቡ። ለቅሶው ተጀመረ። “የት ወስደው ሊደፉን ነው?” በሚል ጭንቅ ሆነ።
ትንሽ ከተጉላሉ በኋላ አቅጣጫ ጠቋሚዎቹ ደወሉ።
እኩለ ሌሊት ገደማ አዋሽ ሰባት ደረሱ።
ገና ከአውቶብሱ እንደወረዱ ነበር ጫማቸውን አሽንቀንጥረው እንዲጥሉ የታዘዙት። ሌሊቱም ተደጋግፈው በተኙበት ተገባደደ።
የአዳራሹ በር ተንኳኳ። እስረኛ ጠባቂዎቹ ነበሩ።

ዕጩ ‘ኩንታኩንቴዎች’
ረፋድ ላይ ለእያንዳንዳቸው ምላጭ ተሰጣቸው። እርስ በእርስ ፀጉራችሁን ተለጫጩ ተባለ። በትዕዛዙ መሠረት ከጎኑ የነበረው ሰው ፀጉሩን ላጨው። እርሱም በተራው የተባለውን ፈፀመ።
ሲጨርሱ “ተነሱ! እጅ ለእጅ ተያያዙ!” የሚል ከወታደሮቹ አፍ የማይለይ ቃል በድንገት አምባረቀ።
የአዋሽ ፀሐይ ፀጉር አልባ ጭንቅላታቸውን መፈተን ያዘች።
በዚያ ሙቀት “ወታደሮቹ ሙሉ መለዮዋቸውን እንዴት መልበስ እንደቻሉ ያስደንቀኝ ነበር” ይላል በፍቃዱ የአካባቢውን ኃይለኛ ሙቀት ሲገልጽ።
የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ተቀብለው ተነስተው መራመድ እንደጀመሩ ባሉበት እንዲቆሙ ታዘዙ። ትዕዛዙ ወታደራዊ ነው። ውልፍት የለም።
በዚህ ቅጽበት በአሻጋሪ አንድ ነገር ዐይኑን ሳበው።
ከወደታች እጅ ለእጅ ተያይዘው፣ በአንድ እጃቸው ቢጫ ጀሪካን ይዘው የሚያልፉ በርካታ ወጣቶች።
ከሃሳቡ ያነጠበው “‘ኩንታኩንቴዎች’ አይመስሉም?” የሚለው አጠገቡ የነበረ እስረኛ ንግግር ነበር።
አመድ መስለዋል። የለበሱት ካናቴራ ላያቸው ላይ አድፎ ተቦጫጭቋል። በባዶ እግራቸው ናቸው። እግራቸው ስንጥቅጥቅ ብሏል። ራሳቸው መላጣ ነው። አሮጌ መላጣ። አቧራ፣ ነፋስ እና ሙቀት የተፈራረቀበት የወየበ መላጣ።
ኩንታኩንቴ፣ ‘ሩትስ’ በሚል ፊልም ላይ ያለ ገጸ ባህርይ ስም ሲሆን በባሪያ ፈንጋይ ወደ አሜሪካ የተወሰደ አፍሪካዊ ነው። ኩንታኩንቴ በገበያ መሐል ጥርሳቸውን እያሳዩ፣ ታፋቸው እየተመተረ፣ ባታቸው እየተጨመቀ፣ ትከሻቸው እየተለካ፣ በአደባባይ፣ በጨረታ የተሸጡ ጥቁር አፍሪካዊያን ታሪክን የሚያሳይ ገጸ ባህርይ ነው።
ኩንታኩንቴ የጥቁሮችን መከራ እና ስቃይ ፍንትው አድርጎ አሳይቷል።
በፍቃዱ አሻግሮ ያያቸው ወጣቶች እነዚህን በባሪያ ፈንጋይ የተሸጡ ኩንታኩንቴዎች ነበር የሚመስሉት።
በቆይታ እንደተረዳው ወጣቶቹ ከእነርሱ በፊት 40 ቀናትን በካምፑ ያሳለፉ ናቸው። በእጃቸው ቢጫ ጀሪካን ይዘዋል። ጀሪካኖቹ ውሃ ቀድተው የሚያስገቡባቸው ናቸው።
እነ በፍቃዱ ራሳቸውን በእነርሱ ቦታ አድርገው ሳሉት። ዕጩ ኩንታኩንቴዎች!
ወጣቶቹ አልፈው ሲጨርሱ እነ በፍቃዱን በባዶ እግራቸው በኮረኮንች እና በአሸዋ ላይ ‘እንጠጥ፣ እንጠጥ’ እያሉ እጅ ለእጅ እንደተያያዙ ወደ ጫካ ወሰዷቸው።
ወገባቸውን እንዲፈትሹ [እንዲፀዳዱ] ነበር ወደ ጫካው የመሯቸው።
ረሃብ እና የተፈጥሮ ጥሪ
“ ጎን ለጎን ተደርድራችሁ ተፀዳዱ”
ቦይ ነው። ቁልቁል የተቆፈረ። ሽታው አያስጠጋም። ግን የተፈጥሮ ግዴታ ከሽታው ይልቃል። መቀመጫችሁን ወደ ቦዩ አዙራችሁ ጎን ለጎን ተቀምጣችሁ ተፀዳዱ የሚል ትዕዛዝ ወረደ።
ይህንን ድፍረት ያገኘ አልነበረም። ያሳፍርም፤ ያስደነግጥም ነበር። ለመፀዳዳት የተቀመጠ አልነበረም። “ጭቃ ሽንቱን ትተን፣ እዚያው ጎን ለጎን ሆነን ውሃ ሽንታችንን አፈሰስን” ይላል።
የመጀመሪያ ቀን ስለሆነ፣ የጎረሱትም ስላልነበር ማስታገስን ምርጫቸው አደረጉ። ለነገው ይህ የሚደገም አይሆንም።
እንደዚያው እጅ ለእጅ እንደተያያዙ ወደ ቧንቧ ወስደዋቸው ከታጠቡ በኋላ እንደተሰለፉ ወደ ባዶው አዳራሽ አስገቧቸው – ለዳቦ ቀለባ ።
“ዳቦ መቅለብ”
የቁርስ ሰዓት ነው። አንድ ዳቦ ከግማሽ ኩባያ ሻይ ጋር ነበር ቁርሳቸው።
ሻዩ ለምን በኩባያው ግማሽ ተደርጎ እንደተሰፈረ ግልጽ አይደለም። በግማሽ ኩባያ ሻይ አንዱን ደረቅ ዳቦ ለመጨረስ ግብ ግብ መግጠም የግድ ነው።
ግማሽ ኩባያ ሻይ የቅጣቱ አንድ አካል ይመስላል።
በፍቃዱ ይህን የተረዳው እየቆዩ ሲሄዱ የሻዩ መጠን እየጨመረ ስለመጣ ነው።
በአዳራሹ ውስጥ ሥራ ፈትተው ጥግ ላይ የተከመሩ ጠረጴዛ እና ወንበሮች ቢኖሩም አዳራሹ ውስጥ ለማረፊያ የሚሆን ጠፍጣፋ ድንጋይ እንኳን የለም።
እንደ ሕጻን ልጅ ወለሉ ላይ ዝርፍጥ ብለው ተቀምጠው ነበር የሚመገቡት።
እንደ ኳስ የተወረወረላቸውን ዳቦ ቀልበው፣ ከወደቀም አራግፈው ባዶ ወለል ላይ ተቀምጠው በጉሮሯቸው ለማወራረድ ይታገላሉ።
“የዚህ ዓላማው ማንኳሰስ እና ማዋረድ ነው” ይላል በፍቃዱ።
ረፋዱ ላይ ከአዳራሹ አስወጧቸው። ወበቃማው የአዋሽ አየር ይጋረፋል። መሬት ላይ ተደርድረው ተቀመጡ።
ስማቸው አንድ ባንድ እየተጠራ ከሌሎች ጋር ተሰባጥረው በቡድን ተዋቀሩ።
በቡድን የተዋቀሩት ወደ አንድ አንድ ክፍል ገቡ። በፍቃዱ እንደሚያስታውሰው የቡድኖቹ ስያሜዎች የወንዝ ስም ይበዛባቸው ነበር። ከእነዚህ መካከል ‘አባይ ኃይል’ አንዱ ነው።
የተሰጣቸው ክፍሎች ተደራራቢ አልጋ የነበራቸው ናቸው። ፍራሽ ግን የላቸውም – ኮምፐርሳቶ ብቻ! የሚደረብም ሆነ የሚነጠፍ በሌለበት ኮምፐርሳቶ ላይ ጎንን ማመቻቸት እንዴት ይቻል ይሆን?
በእርግጥ ይህ ሌሊቱን ካሳለፉበት ሁኔታ አንጻር እጅጉን የተሻለ ነው። እንደ ዶሮ ቁጭ ብሎ ከማደር ጎናቸውን ለማሳረፍ ያስችላቸዋል። ሌላ ምርጫም አልነበረም።

“ ቤተሰቦቼ የት እንዳለሁ አያውቁም ነበር”
እንደ በፍቃዱ በድንገት ከቤታቸው ወጥተው የቀሩት ከለበሷት ልብስ ጋር ከመስማማት ውጪ ምርጫ አልነበራቸውም።
በፍቃዱ ልብስ ሳይቀይር ቀናት ተቆጥረዋል። ሲጠናበት የነተበ የውስጥ ሱሪውን አውልቆ ጥሎ በሱሪው ብቻ ሆነ።
በኋላ ላይ አንድ ፖሊስ በድብቅ ገዝቶ አቀበለው።
በፍቃዱ እንደሚለው በካምፑ ውስጥ 33 ቀናትን ሲያሳልፍ አንድ ልብስ ብቻ ነበር የለበሰው።
በእነዚህ ጊዜያት ገላውን የታጠበውም ሁለት ጊዜ ብቻ ነው። ራሱን ‘ኩንታኩንቴ’ ሆኖ አገኘው። ያኔ በግቢው ውስጥ አሻግሮ ካያቸው ‘ኩንታኩንቴዎች’ ጋር ተመሳሰለ።
በዚህ ሁሉ ውስጥ ማንም የሚጠይቃቸው የቤተሰብ አካል አልነበረም።
በአስቸኳይ ጊዜም ይሁን ያለ አስቸኳይ ጊዜ የተያዙ ተጠርጣሪዎች ጠበቃም ሆነ ቤተሰብ የማግኘት ሰብዓዊ መብት ቢኖራቸውም ቤተሰባቸውንም ሆነ ጠበቃ አግኝተው አያውቁም።
በምን እንደተከሰሱ፣ ለምን ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ የሚያውቁት ነገር የለም።
“ማስጨነቅ ማስጠበብ፣ እርባና ቢስ እንዲሆኑ እንዲያስቡ ማድረግ ዓላማው ነው” ይላል በፍቃዱ።
በፍቃዱ ከበርካታ ቀናት በኋላ የት እንዳለ ለቤተሰቦቹ ያስነገረው የውስጥ ሱሪ ገዝቶ ለማምጣት በተባበረው ፖሊስ አማካኝነት ነበር።
አንዳንድ ጊዜ ኮማንድ ፖስቱ ለጉብኝት የሚልካቸው አባላት አንዳንዶቹን በትብብር ሲያስደውሏቸው ታዝቧል። ከዚያ ውጪ ግን ከቤተሰብ ጋር የመገናኛ አማራጭ መንገድ አልነበረም። አይጎበኙም።
አዋሽ ሰባት አካባቢ ሱቅ ስለመኖሩ፣ ምግብ ቤት ስለመኖሩ፣ ቤተክርስትያን አልያም መስጊድ ስለመኖሩ የሚያውቁት ነገር የለም።
ትዝ የሚለው ካሉበት ካምፕ በስተጀርባ ያለው ያላለቀው የባቡር ሐዲድ እና የሚንቀለቀለውን በረሃ አቋርጦ የሚመጣው የኮንስትራክሽን ሠራተኞችና የሚጓጓዙ ሐዲዶች ድምጽ ብቻ ነበር።
‘አይደገምም!’
“የገባ ሁሉ ይጠመቃል” ይላል በፈቃዱ። ጠመቃ የሚለው ‘የተሃሶድ ሥልጠና’ የሚባለውን ነው። ለዚሁ ተብለው የተዘጋጁ የሥርዓቱ ድርሳኖች ይነበቡላቸዋል። አሠልጣኞቹ የፌደራል ፖሊሶች ናቸው። ሥልጠናውን አለመውሰድ አይቻልም።
የመጀመሪያው የሥልጠና ማንዋል ‘አይደገምም’ የሚል ርዕስ የነበረው ነው። ሌሎችም ማንዋሎች ነበሩ። ኢትዮጵያ ስላስመዘገበችው የኢኮኖሚ እድገት የሚያትቱ፣ ‘የውጭ ኃይሎችን’ የሚከሱ፣ ከጥንታዊው ጀምሮ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያወሱ፣ ስለኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እንዲሁም ስለኢትዮጵያ የወደፊት ሕዳሴ የሚሰብኩ ነበሩ።
እነዚህ የሥልጠና ማንዋሎች በወቅቱ የነበረውን መንግሥት የሚያወድሱ እና የራሱን ትርክት የሚተነትኑ ነበሩ።
“አስተዳደሩ ያፈራቸውን ትውልዶች የሚያወድስ እና በተቃራኒው ያንኑ ትውልድ የሚወቅስ እርስ በእርሱ የተጣረሰ ሃሳብም ያለበት ነበር” ይላል በፍቃዱ።
በእነዚህ ሥልጠናዎች ወቅት ‘በአገሪቷ ተቃውሞዎች ለምን ተበራከቱ?’ የሚለውን ለማወቅ ጥያቄ ይጠይቋቸው እንደነበር የሚያስታውሰው በፍቃዱ፣ በኋላ ላይ ግን እሱን ጨምሮ አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች ላይ “የአሠልጣኞችን ሃሳብ ለማስቀየር እየሠራችሁ ነው” በሚል ማስፈራሪያ እና ዛቻ ይደርስባቸው እንደነበር ይናገራል።
በፍቃዱ እንደሚለው ከዚህ ተግባራቸው የማይቆጠቡ ከሆነ እርምጃ እንደሚወስዱባቸውም አስጠንቅቀዋቸው ነበር።
ከዚያ በኋላ የሚሉትን ከመስማት ውጪ የሚመላለሱት ነገርም አልነበረም።
በበፍቃዱ አገላለጽ ‘ጠመቃው’ ፖለቲካን ለሚያውቁት ባይሰራም ተቃውሞ ላይ ተሳትፈው ለማያውቁ፣ ወሬ ለመስማት ወጥተው ታፍሰው ለገቡ፣ እንዲሁም ላልተማሩት ሊሰራ እንደሚችል ይገምታል።
በዚህ ወቅት ፀጉራቸው አድጓል። ሥልጠናውን እያጠናቀቁ እንደሆነ ሲገባቸውም ጥለውት ወደ መጡት ሕይወታቸው እንደሚመለሱ ተስፋ ሰንቀዋል። በተጎሳቆለው ፊታቸው ላይ ተስፋ ብልጭ ብልጭ ማለት ጀምሯል።
‘ጠመቃው’ ተጠናቀቀ። ለምረቃቸው ‘አይደገምም!’ የሚል ጽሑፍ የሰፈረበት ቲሸርት ታደላቸው።
ንጹህ ስለነበር ስለ ጽሑፉ ደንታ አልነበረውም። ተቀብሎ ወዲያው አጠለቀው። ከአንድ ወር በኋላ ገላው ከአዲስ ልብስ ጋር ተዋወቀ።
በምረቃ ማግስት አዋሽ ሰባትን ለመሰናበት በተዘጋጀላቸው አውቶብሶች ላይ ተሳፈሩ። አውቶብሶቹ ፊታቸውን ወደ አዲስ አበባ መስመር አዞሩ።
***
በ2009 ዓ.ም በአዋሽ ሰባት የእስረኛ ማቆያ ያሳለፈውን ያጋራን በፍቃዱ ኃይሉ ከዞን ዘጠኝ ጦማርያን መካከል አንዱ ነበር።
በፍቃዱ ውይይት የተሰኘ መጽሔት ከጓደኞቹ ጋር ያዘጋጅ እና ያሳትም ነበር። ከዞን ዘጠኝ ባልደረቦቹ ጋር በጋራ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም ሽልማት አግኝቷል።
ችልድረን ኦፍ ዜር ፓሬንትስ (የወላጆቻቸው ልጆች) የሚል ልቦለድም ለንባብ አብቅቷል። በዚህም የአፍሪካ የሥነ ጽሑፍ ሽልማት ውድድር ተሸላሚ ሆኗል።
በፍቃዱ ከአራት ዓመታት በፊት የተቋቋመው የመብቶች እና ዴሞክራሲ የእድገት ማከል (CARD) የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅትን ከመሠረቱት መካከልም አንዱ ነው።
በፍቃዱ በሚጽፋቸው ጽሑፎች ለሰብዓዊ መብት መከበር በሚያደርገው ሙግት በተደጋጋሚ ለእስር የተዳረገ ሲሆን፣ ሚያዝያ 2006 ዓ.ም. ከዞን ዘጠኝ ጦማሪያን እና ሦስት ጋዜጠኞች ጋር በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ ከተያዘ በኋላ ክሱ አመጽ ማነሳሳት በሚል ተቀይሮ ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር የእስር ቆይታ በኋላ ተፈትቷል።
መስከረም 22/2009 ዓ.ም. በኢሬቻ በዓል ላይ የደረሰውን እልቂት ተከትሎ በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታስሮ ወደ አዋሽ ሰባት የተወሰደውም ከእስር ከተፈታ ብዙም ሳይቆይ ነበር።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት ጥር 2010 ዓ.ም. ላይ ባወጣው ሪፖርት በወቅቱ በካምፑ የታሰሩ ከ1 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች ነበሩ።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የጅምላ እስሮች የተፈፀሙ ሲሆን፣ እስረኞቹ ክስ ሳይመሰረትባቸው፣ በቂ ምግብ፣ ውሃ እና የመፀዳጃ ሥፍራ በሌለበት ማቆያ በጅምላ እንዲቆዩ መዳረጋቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።