ጆሞ ኬንያታ አየር ማረፊያ

ከ 6 ሰአት በፊት

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከወራት በፊት አገራቸው የአፍሪካ አገራት ዜጎች ቪዛ ሳያስፈልጋቸው ኬንያን መጎብኘት ይችላሉ በማለት ይፋ ካደረጉ በኋላ ብዙዎች አወድሰዋቸው ነበር።

የፕሬዝዳንቱ ‘ቪዛ አያስፈልግም’ አዋጅ ግን ‘ለቪዛ ክፍያ አንጠይቅም’ ማለት እንዳልሆነ አፍሪካውያን ተጓዦች የገባቸው ዘግይቶ ነው።

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የበርካታ የአፍሪካ አገራት ዜጎች ኬንያ ሲደርሱ ፓስፖርታቸው ላይ ምልክት ተደርጎላቸው ያለ ምንም ክፍያ እና ቪዛ በአገሪቱ እስከ ሦስት ወራት መቆየት ይችሉ ነበር።

በዚህ አሠራር ሲጠቀሙ የቆዩት ኢትዮጵያውያን እና ሌሎችም መጉላለት ሳይገጥማቸው ለሥራ ወይም ለጉብኝት ወደ ምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ሲገቡ እና ሲወጡ ቆይተዋል።

ፕሬዝዳንት ሩቶ ኬንያ ‘ከቪዛ ነጻ’ ትሆናለች ብለው ይፋ ያደረጉት አዋጅ ተፈጻሚ መሆን ሲጀምር ግን በርካቶች ለወጪ እና ለእንግልት እየተዳረጉ ነው።

በዚህ አዋጅ ቪዛ ቀርቷል ቢባልም ተጓዦች ኤሌክትሮኒክ የጉዞ ፍቃድ (ኤሌክትሮኒክ ትራቭል ኦተራዜሽኝ – ኢቲኤ) ከጉዟቸው ሦስት ቀናት ቀድመው ከኬንያ መንግሥት ባለሥልጣናት ማግኘት ይኖርባቸዋል።

ይህ አዲሱ አሰራር ቀድሞ ያልነበረ አዲስ ክፍያ ከመጠየቁም በላይ ተጓዦች ፎርም እንዲሞሉ ይገደዳሉ።

በተለይ ደግሞ የጉዞ ፍቃዱን ለማግኘት የሚጠየቀውን 30 ዶላር ለመክፍል ዓለም አቀፍ ክፍያ መፈጸሚያ ካርድ ማግኘት ከባድ በሆነባቸው እንደ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ያሉ አገራት ዜጎች ደግሞ ፍቃዱን የማግኘት የበለጠ ውስብስብ ያደርገዋል።

አዲኦ የተባለ በጀርመን ነዋሪ የሆነ የዚምባብዌ ዜጋ ወደ ኬንያ ለመብረር ሻንጣው ሸክፎ ከአየር ማረፊያ ሲደርስ መጉላላት ሊገጥመው እንደሚችል ፈጽሞ አልጠረጠረም።

አውሮፕላን ከመሳፈሩ በፊት ሻንጣ መላኪያ መስኮት ጋር ሲደርስ ከዚህ በፊት ባልገጠመው ሁኔታ ኬንያ ለመግባት ፍቃድ እንዳለው ጥያቄ ቀረበለት።

“ለጉዞ ፍቃድ አያስፈልገኝም ብዬ ተከራክሬ ነበር” ሲል የ33 ዓመቱ ተጓዥ ይናገራል።

እርሱ እንዳለው ከጥቂት ሳምንታት በፊት ዚምባብዌን ጨምሮ የ40 የአፍሪካ አገራት ዜጎች ቪዛ ሳያስፈልጋቸው ኬንያ መግባት ይችሉ ነበር።

“ያለ ቪቫ ማለት ያለ ክፍያ ማለት አይደለም”

ካልንበት የአውሮፓውያኑ 2024 ጀምሮ ኬንያ ከቪዛ ነጻ ትሆናለች ሲባል፣ የተረዳሁት ወደ አገሪቷ የሚደረገው ጉዞ ቀላል እንደሚሆን ነበር የዚምባብዌ ዜጋው አዲኦ።

“የጉዞ ፍቃዱን ዝርዝር ስመለከት ከቪዛ ነጻ የተባለው ከክፍያ ነጻ ማለት እንዳልሆነ ተረዳሁ” ይላል።

አዲኦ በጉዞ ወኪሎች ድጋፍ 160 ዶላር ወጪ አውጥቶ የሚጠበቅበትን ለሟሟላት ቢጥርም የጉዞ ፍቃዱ እስኪደርሰው ሰዓታት በማለፋቸው በረራው አምልጦታል።

በኬንያ አዲሱ የጉዞ ሕግ መሠረት ተጓዦች ወደ ኬንያ ከመጓዛቸው በፊት ኢቲኤ ማግኘት ይኖርባቸዋል።

ኢቲኤ 30 ዶላር የሚያስከፍል ሲሆን አንድ ተጓዥ በኬንያ ለ90 ቀናት እንዲቆይ ይፈቅዳል።

ይህንን ፈቃድ ለማግኘት ተጓዦች የጉዞ ትኬት ዝርዝር እና በኬንያ የሚቆይበት አድራሻን ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል።

“ለእንደ እኔ ዓይነት ሰዎች አዲሱ ሕግ ነገሮችን ቀላል አያደርግም። ከዚህ ቀደም ወደ ኬንያ ለመምጣት ምንም ነገር አይጠበቅብንም ነበር” ይላል አዲኦ።

ኬንያዊው የኢሚግሬሽን ጠበቃ የሆኑት ዴቪስ ኛጋህ የኬንያ መንግሥት ያስተዋወቀው ኢቲኤ “በስም እንጂ ከቪዛ በምንም አይለየም” ይላሉ።

“ከሕግ አንጻር በኢቲኤ እና በቪዛ መካከል ምንም ልዩነት የለም። ልዩነቱ በፓስፖርት ላይ የሚለጠፈው የቪዛ ፈቃድ መቅረቱ ብቻ ነው” ይላሉ።

ምናልባት የኬንያ መንግሥት ይህን አዲስ ሕግ ያስተዋወቀው ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ሊሆን ይችላል።

አሁን ላይ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ከሚባሉት ዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ ውጪ ያለ የየትኛው አገር ጎብኚ ወደ አገሪቱ በገባ ቁጥር 30 ዶላር ይከፍላል።

ከዚህ ቀደም የነበረው አሠራር የተወሰኑ አገራት ዜጎች 50 ዶላር ከፍለው ለበርካታ ጊዜያት እንዲገቡ እና እንዲወጡ የሚያስችል ፍቃድ ያስገኝላቸዋል።

የኬንያ መንግሥት ገቢ ለመጨመር ያረቀቀው ሕግ ግን ጎብኚዎችን በማሸሽ ዋጋ ሊያስከፍለው እንደሚችል ተንታኞች ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

ፓስፖርት

ለምሳሌ ሩዋንዳ ሁሉም የአፍሪካ አገራት ዜጎች ያለ ምንም ክፍያ ካለ ቪዛ ወደ አገሯ እንዲገቡ ማድረጓ የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምርላት ማድረጉን አስታውቃ ነበር።

በሩዋንዳ ለአፍሪካውያን ካለ ቪዛ ወደ አገሯ እንዲገቡ ከተፈቀደ በኋላ የአፍሪካውያን ጎብኚዎች ቁጥር በ14 በመቶ መጨመሩን ትገልጻለች።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አንቶኒ ማብያንጌ “ጎብኚዎችን እና ንግድን ለማበረታታት የተቀላጠፈ የጉዞ አማራጭ እጅግ ወሳኝ ናቸው” ይላሉ።

ባለሙያው ተጓዦች የጉዞ ፍቃድ እንዲያገኙ መጠየቃቸው የኬንያን ምጣኔ ሃብት በአጭር እና በመካከለኛ ጊዜ ውስጥ ሊጎዳው እንደሚችል ይገምታሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ ከፍተኛ የኬንያ መንግሥት ባለሥልጣን ለጉዞ ፍቃዱ ክፍያ የሚጠየቀው የአገሪቱን ደኅንነት ለማረጋገጥ ከሚወሰዱ እርምጃዎች መካከል አንዱ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኬንያ መንግሥት ፕሬስ ሴክሬታሪ የሆኑት ሳሊም ሳዋሌህ “ሽብርተኛነት በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ ስጋት ነው። ስለዚህ ወደ ኬንያ የሚመጣው በሙሉ ለአገሪቱ ደኅንነት ስጋት አለመሆኑን የምናረጋግጥበት መንገድ ያስፈልጋል” ብለዋል።

ኃላፊ ጨምረውም አዲሱ ሕግ እየተለመደ ሲመጣ ለተጓዦች ቀላል እንደሚሆን እና በረዥም ጊዜ የጎብኚዎች ቁጥርን ከፍ እንደሚያደርግ የኬንያ መንግሥት ትንበያዎች ማሳየታቸውን ገልጸዋል።

የኬንያ መንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት አይዛክ ማኢጉአ በበኩላቸው ምንም እንኳ ኢቲኤ “ጊዜያዊ የሆኑ ችግሮች” ቢያጋጥሙት በሂደት ነገሮች የተቀላጠፉ ይሆናሉ ይላሉ።

ባለፉት 30 ቀናት ከ60 ሺህ በላይ የጉዞ ፍቃዶች መሰጠታቸውን የገለጹት ቃል አቀባዩ፤ የኬንያ መንግሥት የዘረጋው ሥርዓት በቀን የ5000 ሰዎች ጥያቄን የማስተናገድ አቅም እንዳለው ተናግረዋል።

በአፍሪካውያን አገራት የሚተገበሩ ጠንካራ የቪዛ መስፈርቶች አፍሪካውያን የአፍሪካ አገራትን እንዳይጎበኙ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው።

ሊቢያ፣ ሱዳን፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን እና ግብፅ ጥብቅ የቪዛ መስፈርቶች ያሏቸው አገራት ናቸው።