January 31, 2024 – Konjit Sitotaw
” የነቀዘ ፣ የተበላሸና መጥፎ ጠረን ያለው የአርዳታ ዱቄት እየተሰጠን ነው ” – ተፈናቃዮች
” ጉዳዩን ደርሼበት የታደለው የተበላሸ ዱቄት እንዲሰበሰብ የሚያስጠነቅቅ ደብዳቤ ፅፊያለሁ ” – የእንዳስላሰ ሽረ ከተማ አስተዳደር
በትግራይ ክልል፣ ሰሜን ምዕራብ ዞን እንዳስላሰ ሽረ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለድምፂ ወያነ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃል ፤ የተበላሸ ፣መጥፎ ጠረን ያለው እና የነቀዘ ዱቄት ከለጋሽ ደርጅቶች መታደላቸውን ገልጸዋል።
ላለፉት 13 ወራት የረባ ሰብአዊ እርዳታ ባለማግኘታቸው በከባድ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ የገለፁት ተፈናቃዮቹ ፤ ከረጅም ጊዚያት በኃላ ጥር 20/2016 ዓ.ም መሰጠት የተጀመረው ዱቄት ጥራት የሌለው ፣ የተበላሽ ፣ የነቀዘና መጥፎ ጥረን ያለው መሆኑ በማስረጃ አስደግፈው አቅርበዋል።
የቴሌቪዥን ጣቢያ ” ለተፈናቃዮቹ የተሰጠው ዱቄት ለምግብነት ቢያውሉት ለጤናቸው ጠንቅ እንደሚሆን የምግብ ባለሙያዎች አረጋግጠውልኛል ” ብሏል።
ዱቄቱ በእርዳታ ያከፋፈሉ ለጋሽ ድርጅቶች ‘ተበላሸ’ ስለተባለው እህል ምላሽ እንዲሰጡ የተደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።
ጉዳዩ በጥብቅ እየተከታተለው መሆኑ የገለፀው የእንዳስላሰ ሽረ መንግስታዊ አገልግሎት ፅህፈት ቤት ፤ ዱቄቱ ያከፋፈሉ ለጋሽ ድርጅቶች ያደሉት እንዲሰበስቡና ማደል እንዲያቆሙ የሚጠይቅ ደብዳቤ መፃፉን አስታውቋል።
ፅህፈት ቤቱ ለለጋሽ ድርጅቶች በፃፈው ደብዳቤ በመጋዝን የተከማቸውና ለተፈናቃዮች የታደለው ዱቄት ተዘዋውሮ መመልከቱንና የተበላሸ መሆኑ ማረጋገጡ ገልጿል።
ስለሆነም ዱቄቱ በላፕራቶሪ ተጨማሪ ምርመራ እስኪደረግለት ድረስ Lot No. 1 MFD March 2023 & Exp. /Best Before February 2024 በሚል የሚታወቅ የተከማቸና ወደ ተፈናቃዮች የደረሰ ዱቄት እንዲሰበሰብና እንዲከለከል በፃፈው ደብዳቤ ማስጠንቀቁን የድምፂ ወያነ ቴሌቪዥን ዋቢ በማድረግ የመቐለው የቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባል መረጀውን አጋርቷል።