
31 ጥር 2024, 15:44 EAT
በምሥራቃዊ ኬንያ ውስጥ ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት ነው የተባለው ጉድ ኒውስ ኢንተርናሽናል ሚኒስትሪስ የተባለው ‘ቸርች’ የተደራጀ ወንጀለኛ ቡድን ተባለ።
የኬንያ የአገር ውስጥ ጉዳይ እና ብሔራዊ አስተዳደር ካቢኔ ሚኒስትር ናቸው ቤተ-ክርስቲያኑ የወንጀለኞች ቡድን በማለት በይፋ አውጀው የሰየሙት።
ሚኒስትሩ ኪቱሬ ኪንዲኪ ረቡዕ ጥር 22/2016 ዓ.ም. በወጣ ጋዜጣ እንዳወጁት የሰባኪው ፖል ማኬንዚ ቤተ-ክርስቲያን የተደራጀ የወንጀለኞች ቡድን ነው።
በዚህም መሠረት “የተደራጁ ወንጀለኞችን ለመከላከል በወጣው ሕግ አንቀፅ 22 ቁጥር 1 መሠረት ጉድ ኒውስ ኢንተርናሽናል ሚኒስትሪስ የተደራጀ ወንጀለኛ ቡድን ተብሎ እንዲፈረጅ ወስነናል” ሲል ከሚኒስቴሩ የወጣው መግለጫ አመልክቷል።
የቤተክርስቲያኑ መሪ እና ሰባኪው ማኬንዚ እና 94 ተከታዮቹ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በጅምላ ግድያ ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ነው የሚገኙት።
ተጠርጣሪዎቹ ኪሊፊ በተባለችው የኬንያ ግዛት ውስጥ ሻካሆላ ጫካ ከ400 በላይ የእምነቱ ተከታዮች በረሃብ እና በተለያዩ ምክንያቶች እንዲሞቱ ሰበብ ሆነዋል ተብለው ነው የተከሰሱት።
ሰባኪው ለተከታዮቹ “እየሱስን መቀላቀል ከፈለጋችሁ እስክትሞቱ ድረስ ተራቡ” ሲል ነግሯቸዋል ተብሎ ተከሷል።
- የጎዳና ላይ ነጋዴ የነበረው ፓስተር ተከታዮቹን እንዴት በረሃብ እንዲሞቱ ማሳመን ቻለ?2 ግንቦት 2023
- ከረሃብ የተረፉት ኬንያውያን ራስን በማጥፋት ወንጀል ክስ ቀረበባቸው13 ሰኔ 2023
- አነጋጋሪ በሆነው የኬንያ የእምነት ቡድን በርካታ ህጻናት በረሃብ እንዲሞቱ መደረጋቸው ተነገረ14 ግንቦት 2023
ተጠርጣሪዎቹ ለስምንት ወራት ያክል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከቆዩ በኋላ ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ተከሳሾቹ በተደራጀ የወንጀል ተግባር፣ በፅንፈኝነት፣ የሽብርተኝነት ተግባር በማመቻቸት እና በሌሎችም ወንጀለኞች ቢጠረጠሩም ይህን ያስተባብላሉ።
የኬንያ ዐቃቤ ሕግ፤ ተጠርጣሪዎቹ ይህን ተግባር የፈፀሙት በአውሮፓውያኑ ከ2020 እስከ 2023 ባለው ጊዜ ነው ሲል ለችሎቱ ተናግሯል።
በኬንያው ሻካሆላ ጫካ እና በአቅራቢያው ባሉ አካባቢዎች ነው 429 የቤተክርስቲያኑ አባላት ራሳቸውን በረሃብ በመቅጣት ሞተው የተገኙት።
ሰባኪው ማኬንዚና ሮዳ ማዌን ጨምሮ 95ቱ ተጠርጣሪዎች “ፅንፍ የረገጠ የእምነት ሥርዓት በመዘርጋት ሰዎች ራሳቸውን በረሃብ እንዲቀጡ በማድረግ እምነት አስፋፍተዋል” የሚል ክስ ይቀርብባቸዋል።
ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው ሰባኪው ማኬንዚ የእምነቱን ተከታዮች ወደ ሻካሆላ ጫካ እና ማሊንዲ ከተማ በመውሰድ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥሏል፤ ይህ ደግሞ የሽብርተኝነት ድርጊትን ማመቻቸት ነው ብሏል።
አክሎ ሰባኪው ሌሎች ሁለት ሰዎች በርካታ ሲዲዎች፣ ዲቪዎች፣ መጻፍት እና በራሪ ወረቀቶችን ተጠቅመው የእምነቱ ተከታዮች ሕይወት አደጋ ላይ ጥለዋል ይላል።
ራሱን ፓስተር ብሎ የሚጠራው ፖል ማኬንዚ ካለፈው ሚያዚያ ጀምሮ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ነው የሚገኘው።