

ዜና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት አገልግሎቶችን በጊዜያዊነት ማገዱ ተገለጸ
ቀን: January 31, 2024
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሥሩ ለሚገኙ ተቋማት ሠራተኞች የባህሪና የቴክኒክ ፈተና ከሰጠ በኋላ፣ ከተገኘው ውጤት ጋር በተያያዘ፣ ለተገልጋዮች የሚሰጡ የመሬት አገልግሎቶችን በጊዜያዊነት አገደ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ማክሰኞ ጥር 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ለ11 ክፍላተ ከተሞችና ለሦስት ቢሮ ኃላፊዎች እንዳሳወቀው፣ የሠራተኞች ድልድል እንደ አዲስ ተካሂዶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ‹‹ማናቸውም ዓይነት የመሬት አገልግሎቶች›› ለአጭር ጊዜያት ታግደዋል፡፡
በርካታ የከተማ አስተዳደሩ ሠራተኞች ከታኅሳስ ወር ጀምሮ ለፈተና እየተቀመጡ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ፈተናውን ማለፋቸው የተገለጸው ግን በቁጥር አነስተኛ ናቸው፡፡
የመጨረሻ ፈተና ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ወስደው የነበሩት የአስተዳደሩ የመሬት ይዞታ ቢሮ፣ የመሬት ልማት አስተዳደር ቢኖና በከንቲባ ጽሕፈት ቤት ሥር የሚገኙ ሦስት ተቋማት በአጠቃላይ 3,861 ሠራተኞች ነበሩ፡፡
የእነዚህ ሠራተኞች ውጤት ሰኞ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ሲደረግ፣ ፈተናውን ወስደው ከነበሩት ውስጥ ያለፉት 1,680 ብቻ ነበሩ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተሰጥቶ የነበረውን ፈተና ማለፍ የቻሉት 44 በመቶ ብቻ ናቸው ተብሏል፡፡
አብዛኞቹ ከመሬት ጋር የተያያዘ ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሠራተኞች ሲሆኑ፣ አስተዳደሩ የፈተናው ውጤት በወጣ በቀጣዩ ቀን ነበር የመሬት አገልግሎቶችን በጊዜያዊነት ያገደው፡፡
ከዚህ ተቋም ፈተና ከተቀመጡ 4,213 በአመራር ደረጃ ከነበሩት ኃላፊዎች 1,422 ፈተና ሲያልፉ፣ ከ10,257 ባለሙያና ሠራተኛ ተፈታኞች ውስጥ ያለፉት 5,095 እንደነበሩ መገለጹ አይዘነጋም፡፡