ሳሙኤል ቦጋለ

January 31, 2024

የቴክኖሎጂ አሶሼትስ ኃላፊዎች ስለድርጅታቸው መግለጫ ሲሰጡ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ማጭበርበርንና በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን (Money Laundering) የሚያስቀር ሲስተም ግዥ እየፈጸመ መሆኑ ታወቀ፡፡

ብሔራዊ ባንክ መቀመጫውን ኬንያ አድርጎ በዘጠኝ አገሮች (ስምንቱ በአፍሪካ) እየሠራ የሚገኘውን ቴክኖሎጂ አሶሼትስ (Technology Associates) የተሰኘውን ኩባንያ ሶፍትዌር በማሠራት ግዥ እየፈጸመ መሆኑ ታውቋል፡፡

ቴክኖሎጂ አሶሼትስ በፋይናንስ፣ በጤናና በኤሌክትሮኒክስ አስተዳደር ሥራዎችን የሚያከናውን ኩባንያ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፈቃድ አግኝቶ መሥራት ከጀመረ አንድ ዓመት ሆኖታል፡፡ ለግል ባንኮችና ለሌሎችም የቴክኖሎጂ አቅርቦት ያደርጋል፡፡

በግማሽ ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ሲስተሙን ከዘረጋ በኋላ ለሰባት ዓመታት ለሚቆይ አገልግሎት ከብሔራዊ ባንክ ጋር እንደሚፈራረሙ የገለጹት፣ የኩባንያው የኢትዮጵያ ካንትሪ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጃያንት ኩማር ናቸው፡፡ ሁለቱ ተቋማት ስምምነቱን የካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚፈራሙና ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ እንዲቆጣጠረው ሆኖ የሚሠራው ሶፍትዌር ገንዘብን ያማከለ ማጭበርበር የሚከታተል ሲሆን፣ የንግድ ባንኮችም ብሔራዊ ባንክ የሚሰጣቸውን አካሄድና ድንጋጌ በመከተል በሲስተሙ አማካይነት ይሠራሉ ተብሏል፡፡

ለሰባት ዓመታት የሚቆየው የብሔራዊ ባንክና የቴክኖሎጂ ኩባንያው ግንኙነት ለሶፈትዌሩ ፈቃድ በመስጠት፣ በማልማትና እየተከታተሉ ድጋፍ በማድረግ እንደሚሠራ ነው ጃያንት ያስረዱት፡፡ ባንኮች የሚያደርጉትን የገንዘብ ዝውውር በመከታተል ማጭበርበር እንደሚቀንስም ገልጸዋል፡፡

‹‹ብሔራዊ ባንክ የሶፍትዌሩ ባለቤት ይሆንና ባንኮች እየተጠቀሙበት በማዕከል ይቆጣጠራል፤›› ሲሉ አስረድተው፣ ይህም የመጀመሪያው እንደሆነና ብሔራዊ ባንክ በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አድርጎ የማቅረብን ወንጀል የሚቆጣጠርበት ቴክኖሎጂ ነው በማለት አክለዋል፡፡

ቴክኖሎጂ አሶሼትስ ኩባንያው ማክሰኞ ጥር 21 ቀን 2016 ዓ.ም. በራዲሰን ብሉ ሆቴል ከአጋር ኩባንያው ቲቶ ኢቭሪ (Tietoevry) ከተባለ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋር በጋራ ባካሄዱት የባንኪንግ ክፍያ አገልግሎት ውይይት ላይ ነው ኃላፊው ለለሪፖርተር ሥለ ድርጅታው ሥራዎቸ ማብራሪያ የሰጡት፡፡

ከተመሠረተ 28 ዓመታት ያስቆጠረው ቴክኖሎጂ አሶሼትስ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ 12 ዓመታት በፊት ነበር ለወጋገን ባንክ የቴክኖሎጂ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር፣ በተጨማሪም ለብርሃን ባንክ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንና ከሌሎች ባንኮች ጋርም ውይይት በማድረግ ላይ መሆኑን ጃያንት አስረድተዋል፡፡