spot_img

በብዛት የተነበቡ

አንጋፋው ፖለቲከኛና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አቶ ተመስገን ዘውዴ፣ ‹‹እኛ መንግሥትን የቀጠርነው ሳሙናና ስኳር እንዲቸረችር አይደለም፤›› ብለው በአንድ የፓርላማ ውይይት መድረክ ላይ ያደረጉት ንግግር በተደጋጋሚ ይጠቀሳል፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ሊኖረው የሚገባው ሚና በየፖለቲካ መድረኩ ተደጋግሞ የሚነሳ የመከራከሪያ አጀንዳ ነው፡፡መንግሥት ከሳሙና መቸርቸር ብቻ ሳይሆን ከፋይናንስና ከቴሌኮም ዘርፍም መውጣት አለበት የሚል ሙግት የሚያነሱ ወገኖች አሉ፡፡ መንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ወይም የኢኮኖሚ መጫወቻ ሜዳውን የሚወስኑ ሕጎችና አሠራሮችን ከማጣት፣ እንዲሁም ከማስፈጸም በዘለለ በኢኮኖሚው ውስጥ እጁን መክተት የለበትም የሚሉ ወገኖች በርካታ ናቸው፡፡እንደ ኢትዮጵያ ባለ የዳበረ የግል ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ባልተፈጠረበት አገር መንግሥት የኢኮኖሚ ሚናው ሰፊ ሊሆን ይገባል የሚል ሙግት በተቃራኒው የሚያነሱም አሉ፡፡ ይህን ሙግት ገዥ ያደረገው መንግሥትም ኢኮኖሚውን ለግል ዘርፍ ለቆ ይውጣ/አይውጣ የሚለው ክርክር በተፈጠረ ቁጥር የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን ለሚሰብኩ ወገኖች ‹‹የኒዮሊበራል ኃይሎች›› ተብለው ሲፈረጁ ባለፉት 30 ዓመታት መመልከት የተለመደ ነበር፡፡መንግሥት ራሱንም ሆነ የሚከተለውን የፖለቲካ ኢኮኖሚ ፖሊሲ በተመለከተ ‹‹ልማታዊ መንግሥት›› ነኝ ሲል በቆየባቸው ባለፉት 30 የኢሕአዴግ አስተዳደር ዓመታት፣ የኢኮኖሚ ነፃነትም ሆነ የመንግሥት የኢኮኖሚ ተዋናይነት አጀንዳ በተነሳ ቁጥር ፅንፍ የረገጡ ክርክሮችን ማድመጥ የተለመደ ነበር፡፡ትልቁ ጥያቄ ግን አሁንስ ይህ ተለወጠ ወይ የሚለው መሆኑን ብዙዎች ያነሱታል፡፡ ኢሕአዴግ ልማታዊ መንግሥት ነኝ በሚል በኢኮኖሚው ውስጥ የበዛ ጣልቃ ገብነት ሲያደርግ የቆየባቸው የሚባሉት ዓመታት ታልፈው የለውጡ መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታት በሥልጣኑ ላይ ተተክቷል፡፡ አዲሱ የብልፅግና መንግሥት የመንግሥትን የኢኮኖሚ ሚናም ሆነ የኢኮኖሚ ነፃነት ጉዳይን በተመለከተ እያራመደ ያለው አቋም ምንድነው የሚለው፣ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ካልሆነ ብዙም ለውይይት ሲቀርብ አይታይም፡፡የብልፅግና መንግሥት የሚከተለውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በተመለከተ ‹‹በአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ›› ወይም ‹‹ፍኖተ ብልፅግና›› ላይ መሠረታዊ የሚባሉ ነጥቦችን ማስቀመጡ ይታወቃል፡፡ ከ2013 ዓ.ም. እስከ 2022 ዓ.ም. እንደሚተገበር በተነገረለት በዚህ የልማት ዕቅድ ላይ የመንግሥት የኢኮኖሚ ምን መሆን እንዳለበት የሚጠቁሙ ነጥቦችን አሥፍሯል፡፡በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተጻፈው የዕቅዱ መቅድም ላይ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት አስመዝግባለች፡፡ ይህ ዕድገት በመንግሥት ከፍተኛ ወጪ በተስፋፋ የመሠረተ ልማት አማካይነት የተመዘገበ ነው፡፡ ይህም ለዓመታት የዋጋ ግሽበት የፈጠረ ሲሆን፣ ዘላቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል በተፈለገው መጠን በቋሚነት አልፈጠረም፡፡ ወጪው በከፍተኛ ብድርና ዕርዳታ የተሸፈነ ስለነበር ከፍተኛ የዕዳ ጫና ፈጥሯል፤›› የሚል ሐሳብ ተቀምጧል፡፡ ዕቅዱ የቀደመውን የኢሕአዴግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ በመተቸት ነው የሚጀምረው፡፡ይህን የኢሕአዴግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ እንደሚያስተካክልና ጉድለቱን እንደሚሞላ ቃል የሚገባው ‹ፍኖተ ብልፅግና› የግሉን ዘርፍ ሚና እንደሚያሳድግ በጉልህ ያወሳል፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) በመቅድማቸው፣ ‹‹በአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ዘመን የኢኮኖሚውን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት በማሳደግ የኢኮኖሚ ዕድገቱ በሒደት በግሉ ዘርፍ ወደሚመራበት ሁኔታ በማሸጋገር የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለማስቀጠል፣ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ምኅዳር ለመፍጠር፣ ድህነትን በሁሉም መገለጫ በተጨባጭ ለመቀነስ፣ ዘላቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራ ይሆናል፤›› በማለትም አክለዋል፡፡በዕቅዱ መግቢያም ቢሆን ይኼው ሐሳብ ደግሞ የተጠቀሰ ሲሆን፣ መንግሥት በቀረፀው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የግሉ ዘርፍ ‹‹ዋና የኢኮኖሚ ዕድገት መዘውር›› ተደርጎ መቀመጡን ይጠቁማል፡፡የልማት ዕቅዱ የሚከተለውን መስመር በተመለከተ ደግሞ፣ ‹‹የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ገበያ መር የኢኮኖሚ ሥርዓት (Pragmatic Market Based Economic System) ነው የምንከተለው፤›› በማለት ያስቀምጣል፡፡ የግሉን ዘርፍ ጉልህ ሚናና ተሳትፎ በማሳደግ የበለፀገች አገር መገንባት ዋና ግቡ እንደሆነም ዕቅዱ ያወሳል፡፡ይህንኑ ‹ፕራግማቲክ ካፒታሊዝም› በሚል የቀረበ የኢኮኖሚ ሥርዓት ጽንሰ ሐሳብም የመንግሥት ባለሥልጣናት በተለያዩ መድረኮች ሲያስተጋቡት ነበር፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት በተካሄደው ምርጫ ወቅት በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በተደረጉ የፓርቲዎች ክርክሮች፣ የብልፅግና ፓርቲ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ሲጠቅሱት ነበር፡፡ብልፅግናን ወክለው በጊዜው የተከራከሩት ነመራ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ በመንግሥት ሰፊ ኢንቨስትመንት ማድረጓን ገልጸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነትን በመፍጠር ረገድ ዕድገቱ ችግር አለበት ብለዋል፡፡ ሁሉንም ዜጎች በፍትሐዊነት በማሳተፍ ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ድል እናስመዘግባለን ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ፕራግማቲክ ካፒታሊዝምን የገዥው ፓርቲ ተከራካሪዎች ለኒዮሊበራሊዝም የተጠጋ የካፒታሊዝም ሥርዓት አድርገው ሲያቀርቡት ተሰምተዋል፡፡ የግል ዘርፉ ከፍተኛውን የማምረት፣ የመግዛት፣ የመሸጥ፣ የመቅጠር ሚና እንዲኖረው የሚያደርግ ሥርዓት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ስለዚሁ በምርጫ ክርክር ወቅት ስለተነሳው የፓርቲዎች የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሙግት በወቅቱ ሰፊ ሀተታ በፌስቡካቸው ጽፈው የነበሩት የኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ዋሲሁን በላይ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ አስተያየት ካላቸው በሪፖርተር ተጠይቀው ነበር፡፡‹‹በኢኮኖሚው ውስጥ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ወይ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አይደለም ወሳኙ፡፡ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ባለህ አቅምና ብቃት በተለይም በተቋማት የአፈጻጸም ጥንካሬ ነው የሚወሰነው፤›› የሚል አስተያየት የሚሰጡት አቶ ዋሲሁን፣ ለኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ኒዮሊበራል፣ ፕራግማቲክ ካፒታሊዝምና ሌላም ‹የዳቦ ስም› በመስጠት የሚፈጠር ለውጥ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡በኢኮኖሚክሱ ልክ የሚባል መላምት (ቲዮሪ) እንደሌለ የጠቀሱት አቶ ዋሲሁን፣ ‹‹ኮሙዩኒዝም ልክ አይደለም አይሠራም ቢባልም የተወሰኑ አገሮችን ግን በእጅጉ አራምዷል፤›› ሲሉ አስታውሰዋል፡፡ ሊበራሊዝም ወይም ኒዮሊበራሊዝም ብዙ አገሮች አሳድጓል ይላሉ፡፡ እነ ኩባ ወይም ሰሜን ኮሪያ በኢኮኖሚ የወደቁት በተቋም ደረጃ ስለወደቁ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም ‹‹የሚኮነነው ኮሙዩኒዝም እኮ በቻይና ተዓምር ሲሠራ እያየን ነው፤›› የሚሉት አቶ ዋሲሁን፣ ኢኮኖሚ በአመዛኙ በርዕዮተ ዓለም ሳይሆን በተጨባጭ መሬት ላይ በሚወርደው ሥራ እንደሚወሰን አመልክተዋል፡፡‹‹እኛ ሶሻሊዝምን በምንከተል ጊዜ ኬንያ ካፒታሊዝምን ትከተል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አንዱ ከሌላው ፍፁም የተለየ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አልደረሰም፡፡ ስለዚህ ክርክሩ የርዕዮተ ዓለም አይደለም፤›› ብለዋል፡፡የመንግሥት የኢኮኖሚ ጣልቃ ገብነትን ለማብራራት ዘ ግሬት ዲፕሬሽን ወቅት (በታላቁ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል) የተነሳውን የጆን ሜይነርድ ኬንስን ሐሳብ አንስተዋል፡፡ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት ዓለም በከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ በተመታ ጊዜ ኢኮኖሚውን ዳግም እንዲያንሰራራ ለማድረግ ብዙ መንግሥታት ተቸግረው በግራ መጋባት ውስት ወድቀው እንደነበር አቶ ዋሲሁን ይጠቅሳሉ፡፡ በዚያን ፈታኝ ወቅት ኬንስ የተባለው የእንግሊዝ ኢኮኖሚስት የሸማቾችን አቅም በማሳደግ ገበያን ማነቃቃት ይቻላል የሚል ሐሳብ አፈለቀ ይላሉ፡፡ ይህ ያልተለመደ ሐሳብ ቢሆንም ለሸማቾች ጥቂት ድጎማ መንግሥት በመስጠት ገበያ እንዲነቃቃ፣ ብሎም የብዙ አገሮች ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ መደረግ መቻሉን አቶ ዋሲሁን በምሳሌነት ያስታውሳሉ፡፡ይህንኑ ሐሳብ ታዋቂው የኖቤል ኢኮኖሚክስ ሽልማት አሸናፊውና የፕሬዚዳንት ክሊንተን የኢኮኖሚ አማካሪ ጆሴፍ ስቲግሊዝ በሰፊው በመጽሐፋቸው ከትበውታል፡፡ ስቲግሊዝ ‹‹People, Power, and Profits: Progressive Capitalism for an age of Discontent›› በሚለው መጽሐፋቸው፣ የግል ዘርፉና መንግሥት በቅንጅት መሥራታቸው ለኢኮኖሚ ያለውን ውጤታማነት በሰፊው አስነብበዋል፡፡‹‹Capitalist economies have thus always involved a blend of private market of government-the question is not markets or government, but to combine the two to best advantage.›› በሚል ጆሴፍ ስቲግሊዝ የከተቡት ሲሆን፣ ይህም የመንግሥትና የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ውጤታማ ቅንጅት በጉልህ የሚያንፀባርቅ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል መሆኑ ይወሳል፡፡ይህንን አቶ ዋሲሁን የመንግሥት ጣልቃ ገብነትን በኢኮኖሚው በተመጠነ ደረጃ አስፈላጊ መሆኑን እንደሚቀበሉት ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት ፕሮግሬሲቭ፣ የተገደበ፣ ልማታዊ ወይም ሌላ ዓይነት ካፒታሊዝም እከተላለሁ ቢልም የአገሪቱ የማስፈጸም አቅምና የተቋማት ጥንካሬ በስተመጨረሻ ወሳኙ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡የፕራግማቲክ ካፒታሊዝምን ምንነትን በተመለከተ ርዕዮተ ዓለም፣ ሥልት፣ ዘይቤ ወይስ ዕቅድ ነው የሚሉ ጉዳዮች ጥያቄ ማስነሳቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ከሰሞኑ ለብልፅግና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ገለጻ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ ‹‹ከኢኮኖሚ አንፃር ተራማጅ የገበያ ኢኮኖሚ ነው የምንከተለው፡፡ ጠንካራ ተዋንያን ያሉት ቢሆን ዕሳቤ ብቻ ያልታጠረ መሆን አለበት፡፡ ገበያ ፍላጎትና አቅርቦትን ማስተካከል ላይ የሚሠራ ነው፡፡ እዚህ ውስጥ የግልና የመንግሥት ትብብር ወሳኝ ነው፡፡ በግል ወይም በመንግሥት ብቻ የሚከወን ነገር የለም፡፡ የተዋንያንን ቅንጅት ለማምጣት ጠንካራ ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ ከተናጠላዊ ወደ ምሉዕ ዕይታ፣ ከነጠላ ወደ ብዝኃ ተዋንያን፣ ከነጠላ ወደ ብዝኃ ዘርፍ፣ ተለዋዋጭነት ከሌለው ወደ ዕውቀት መርነት ያለው የኢኮኖሚ ሥርዓት መሸጋገር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ተራማጅ (Pragmatic) የካፒታሊዝም ሥርዓት ነው፤›› በማለት ገለጻ አድርገው ነበር፡፡ዓብይ (ዶ/ር) ይህን ቢሉም የጠቀሱት ፅንሰ ሐሳብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ (ፖለቲካል ኢኮኖሚክ ቲዮሪ) ነው የሚለውን ጉዳይ ግን በርካቶች ጥያቄ እያስነሱበት ነው፡፡ፕራግማቲክ ካፒታሊዝምን እንዲሁም የመንግሥትን የኢኮኖሚ ሚና በተመለከተ ማብራሪያ የተጠየቁት አንድ የቀድሞ የመንግሥት ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ በዚህ ስም ወይም መንገድ የሚታወቅ አንዳችም የኢኮኖሚ ሀልዮት አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ የቃላት ለውጥ በማድረግ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ፖሊሲ በሚመለከት ለማምታታት የመሞከር ጥረት አዲስ ነገር አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡‹‹አገር በቀል ኢኮኖሚ ሲሉ እሰማለሁ፣ አገር በቀል የቀዶ ጥገና ሥራ አለ ወይ? ቀዶ ጥገና የትም ቀዶ ጥገና ነው፡፡ በዓለም ላይ አንድ ዓይነት ፊዚክስ እንዳለ ሁሉ ኢኮኖሚም አንድ ነው፡፡ ካፒታሊዝም አለ፡፡ ከዚያ ለየት ያለ ደግሞ ሶሻል ካፒታሊዝም አለ፡፡ ሁለተኛ ፕራግማቲክ ማለት ተጨባጫዊነትን አመላካች ነው፡፡ የምንሠራው ነገር እንዲሁ ከተጨባጩ ሁኔታ ጋር የሚሄድ ነው ለማለት ካልሆነ በስተቀር፣ በዓለም ላይ ፕራግማቲክ ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ብሎ ነገር የለም፤›› በማለት ነው ማብራሪያ የሰጡት፡፡በወቅቱ ያለውን የመንግሥትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የበዛ ጣልቃ ገብነት ሲሉ የገለጹት እኚሁ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ፣ ፕራግማቲክም ሆነ ልማታዊ የሚል ተቀፅላ ሳያወጡ ጣልቃ መግባት ይቻላል ይላሉ፡፡ የመንግሥት በኢኮኖሚ ጣልቃ የመግባት ሁኔታ በኃጢያትነት ሊታይ እንደማይችል ገልጸዋል፡፡ ‹‹አፄ ኃይለ ሥላሴ እኮ ዘውዳዊ ሥርዓት እየተከተሉ ለግል ኢንቨስትመንት ብዙ ፈቃድ ይሰጡ ነበር፡፡ መንግሥታቸውም የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ያለማ ነበር፤›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ይህኛው መንግሥትም ቢሆን ጠቃሚና አገር ቀያሪ በሆኑ ጉዳዮች ቢገባ ኃጢያት የለውም ሲሉ አስረድተዋል፡፡ፕራግማቲክ ካፒታሊዝም የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ቅንጅት የኢኮኖሚ ዕድገት ለማነቃቃት በሚል ያደገ ጽንሰ ሐሳብ ነው የሚሉት ደግሞ፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርኼ ተስፉ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ‹‹ነገርዬው ርዕዮተ ዓለም ሳይሆን የካፒታሊስቶች ዘይቤ ነው ቢባል የተሻለ ነው፤›› ይላሉ፡፡አሁን ባለው የዓለም ኢኮኖሚ ሁኔታ ዕውቀት ፈጣሪዎች ጥቂት መሆናቸውን ያመለከቱት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፣ ተጠቃሚዎቹ ግን ያን ዕውቀት ለውጠው ሥራ ፈጠራ ላይ የሚያውሉት ብዙኃኑ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡‹‹የእነ ቻይና፣ ቬትናምና የደቡብ እስያ አገሮች ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የመንግሥት የኢኮኖሚ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊነትን አጉልቶታል፡፡ ካፒታሊዝም 300 ዓመታት ሕዝቡን ከድህነት ለማውጣት ሲፈጅበት እነ ቻይና ግን በ30 ዓመታት ዕድገት አንድ ቢሊዮን ሕዝብ ከድህነት አውጥተዋል፡፡ ይህ የመንግሥት የኢኮኖሚ ጣልቃ ገብነት እጅግ አስፈላጊ ነው ቢያስብልም፣ ነገር ግን መልሶ እነ ቻይናም ቅልጥ ያለ ካፒታሊዝም ሲከተሉ ነው የታየው፤›› በማለት፣ አሁን ባለው ዓለም ድብልቅ የኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም መመልከት የተለመደ መሆኑን አውስተዋል፡፡ እነ ቻይናና ቬትናም ኮሙዩኒስት አገሮች ናቸው ቢባልም፣ እንዲያውም ‹‹ሌዘ ፌር›› የሚባል ዓይነት የካፒታሊስት ሥርዓት ሲከተሉ ነው የታየው ይላሉ፡፡አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የፖሊሲ አቅጣጫን እንዲገልጹ የተጠየቁት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፣ ለጊዜው በቀውስ ኢኮኖሚ ውስጥ እንጂ ፕራግማቲክ፣ ልማታዊም ሆነ ሌላ ተብሎ የሚቀመጥ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መስመር አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡