ማኅበራዊየከፍተኛ ትምህርት ምሩቃን የወጪ መጋራት ክፍያ በአግባቡ እንደማይፈጸም ተጠቆበጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን:

የተማሪዎችን የወጪ መጋራት ክፍያን በወቅቱ የሚያስፈጽሙ ተቋማት ቢኖሩም፣ በርካታ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በተዘረጋው የአሠራር ሥርዓት መሠረት ክፍያውን ተከታትለው እንደማያስፈጽሙ የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች የወጪ መጋራት ክፍያን መክፈል በሚገባቸው ወቅት አለመክፈላቸው፣ የመንግሥትን ተጨማሪ የኢንቨስትመንት አቅም እንደሚገድብም በሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የአስተዳደር ጉዳዮች ዴስክ ኃላፊ አቶ አብዶ ናስር ገልጸዋል፡፡ተማሪዎች የተጋሩትን ወጪ በሚጠበቅባቸው ወቅት አለመክፈላቸው ለተጨማሪ ወለድና ተሰብሳቢ ዕዳ እንደሚያጋልጣቸውም አክለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ወጪ መጋራት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የመከረ ሲሆን፣ እርስ በርስ የመናበብና የመቀናጀት ክፍተት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች የወጪ መጋራት ክፍያ በአግባቡ እንዳይሰበሰብ ማድረጉንም በሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የአስተዳደርና መሠረተ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሰለሞን አብርሃ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡የመንግሥት ገንዘብ በአግባቡ ተሰብስቦ ለተመሳሳይ ዓላማ ጥቅም ላይ እንዲውል ተቋማትና ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሠሩም ሚኒስቴሩ  ጥሪ ማቅረቡን በሚኒስቴሩ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ሰፍሯል፡፡በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የወጪ መጋራት (ኮስት ሼሪንግ) መመርያ መሠረት፣ ወደ መንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተቀላቀሉ አዳዲስ ተማሪዎች፣ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ተመርቀው እስኪወጡ ድረስ፣ መንግሥት ለምግብና ለመኝታ ያወጣውን ወጪ በሚገቡት ውል መሠረት ከምርቃት በኋላ ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተደንግጓል፡፡ከ1996 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ጀምሮ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገቡ አዳዲስ ተማሪዎች፣ ወጪ መጋራት የሚመለከታቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡