
January 31, 2024

ንግድና ኢንዱስትሪውን ዘርፍ በመነጣጠል የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሄደበት ያለው መንገድ ሥጋት እንደፈጠረባቸው የቀድሞው የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤቶች ፕሬዚዳንቶች ገለጹ፡፡
በተለያዩ ወቅቶች የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤቶችን በፕሬዚዳንትነት የመሩት አንጋፋው የፋይናንስ ዘርፍ ባለሙያ አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ ኢንዱስትሪውና የንግድ ዘርፉን ነጣጥሎ በሁለት የተለያዩ አደረጃጀቶች እንዲዋቀሩ ማድረግ የንግድ ማኅበረሰቡን የሚወክል ጠንካራ የንግድ ምክር ቤት እንዳይኖር ሊያደርግ ይችላል ብለዋል፡፡
የታሰበው አደረጃጀት የንግድ ማኅበረሰቡን ለሁለት የሚከፍል፣ ይህም የንግድ ማኅበረሰቡ በጋራ ሆኖ ሊፈጥር የሚችለውን አቅም የሚያዳክም እንደሆነ አቶ ኢየሱስወርቅ ተናግረዋል። በተለይ ሥራ ላይ ያለው አዋጅ የፈጠራቸው ተፅዕኖዎችና በንግድ ምክር ቤቶች አካባቢ አሉ የሚባሉ ችግሮች ጎልተው በሚሰሙበት በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪውንና የንግድ ዘርፉን ነጣጥሎ ማደራጀት ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል የሚል ሥጋታቸውን አቶ ኢየሱስወርቅ አጋርተዋል። ከ20 ዓመት በፊት የወጣውና እስካሁን ድረስ ሥራ ላይ ያለው የንግድ ምክር ቤቶች አዋጅ ብዙ ችግሮች እንዳሉበት የሚገነዘቡት አቶ ኢየሱስወርቅ፣ በዚህ አዋጅ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማረም ሁሉንም ዘርፎች ያማከለ ማሻሻያ ማድረግ የተሻለ እንደሆነ ያምናሉ። በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ የሚገኘው የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ፖለቲከኞች እጃቸውን አስገብተውበት የተዘጋጀ መሆኑን በዚህም ምክንያት አዋጁን በተሟላ ለመልኩ ለመተግበር ፈተናዎች ሲያጋጥሙ እንደነበር አቶ ኢየሱስወርቅ አስታውሰዋል፡፡ ንግድና ዘርፍ በሚል ስያሜ የተዋቀሩት ንግድ ምክር ቤቶች በንግዱና በዘርፍ ማኅበራት መካከል መሳሳብ እንዲፈጠርና ንግድ ምክር ቤቶች በአግባቡ ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ ማደረጉን ገልጸዋል።
አሁን በሥራ ላይ ያሉትን ንግድ ምክር ቤቶች ንግድና ኢንዱስትሪ በማለት ለሁለት ከፍሎ ለየብቻ ለማቋቋም እየተደረገ ያለው ዝግጅት የንግድ ማኅበረሰቡን የሚወክል ጠንካራ ተቋም እንዳይፈጠር የሚያደርግ በመሆኑ ተጣድፎ ከመወሰን ይልቅ ሁኔታውን በደንብ መፈተሽ ይገባል ሲሉ መክረዋል፡፡
በተመሳሳይ የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤቶችን በፕሬዚዳንትነት በመምራት የሚታወቁት አቶ ክቡር ገናም ይህንን ሐሳብ ይጋራሉ። ‹‹አብሮ መሥራት የሚችሉ ተቋማትን ነጣጥሎ ማስቀመጥ የበለጠ ልዩነት ነው የሚፈጥረው›› የሚሉት አቶ ክቡር፣ በዚህ መንገድ አብሮ የመሥራትና አብሮ ችግርን የመፍታት ባህልን ማዳበር እንደማይቻል ጠቅሰዋል፡፡
ንግድና ኢንዱስትሪ የተያዙ መሆናቸውን በመጥቀስም ‹‹በአንድ በኩል ያመረትከውን ምርት ወደ ገበያ ማውጣት መቻል አለብህ፡፡ ገበያ ላይ አውጥተህ ደግሞ የምታገኛቸው መረጃዎች ለኢንዱስትሪው ይጠቅመዋል›› በማለት ተያያዥ ባህሪያቸው እንደሚያጎላ አስረድተዋል፡፡
ስለዚህ ሁለቱን ለያይቶ በማየት ለየብቻቸው እንዲቋቋሙ ማድረግ እንደማይጠቅም ይሞግታሉ።
በብዙ አገሮች ሁለቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፎች አንድ ላይ በማጣመር ማደረጃት የተለመደ መሆኑን በመጥቀስ በኢትዮጵያ ይህንን አደረጃጀት ከማስቀጠል ይልቅ ለመለያየት የተጀመረውን ዝግጅት እንደማይስማሙበት ገልጸዋል። ነገር ግን የኢንዱስትሪ ዘርፉ በአብዛኛው ምርትን በአገር ውስጥ በማምረት ለገበያ የሚያቀርብ ስለሆነ ከውጭ የሚመጡ ተወዳዳሪ ምርቶችን የመከላከል ፍላጎት መኖሩን የጠቀሱት አቶ ክቡር፣ የአገር ውስጥ አምራቾች ምርቶታቸውን በአግባቡ እንዲሸጡ በማድረግ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለመደገፍ በሚል ዕሳቤ የተያዘ ውጥን ሊሆን እንደሚችል ይጠቅሳሉ።ይህንን አስመልክቶ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ በኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ ተዋንያን በአገር ውስጥ ኢንደስትሪዎች የሚመረቱ ምርቶችን ከውጭ በማስገባት ለአገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርቡ መሆኑ በሁለቱ መካከል መገፋፋት ወይም የሚያቃርኗቸው ጉዳዮች በመኖራቸው ሁለቱን ዘርፎች ለያይቶ የማቋቋም ዕርምጃ መውሰድ ኢንዱስትሪውን ሊደግፉ እንደሚችል አስረድተዋል።ሁለቱ ዘርፎች ከላይ ከተገለጸው አንፃር ሲታዩ ተቃርኖ ያላቸው መስለው ቢታዩም፣ አብሮ እንዲሠሩ ማድረግ ግን ኢንዱስትሪውንም ሆነ የንግዱን ዘርፍ ለማሳደግ እንደሚጠቅም አቶ ክቡር ገና ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ሁለቱን ዘርፎች መለያየት የተሻለ ውጤት ያመጣል የሚል እምነት እንደሌላቸው አስገንዝበዋል፡፡ አቶ ኢየሱስወርቅም ንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጁ ሁሉንም የቢዝነስ ዘርፎች ይዞ ቢቋቋም የተሻለ ነው ብለዋል፡፡ የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጁን መሻሻል የሚኖርበትም ጠንካራ የንግድ ምክር ቤቶች ለመፍጠር እስከሆነ ድረስ በዚያ ልክ ሊታሰብበትና ሊሠራበት እንደሚገባ ያምናሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ንግድ ምክር ቤቶች የተቋቋሙለት ዓላማ እያሳኩ አይደለም የሚል እምነት ያላቸው አቶ ኢየሱስወርቅ፣ አንዱ ችግር ሥራ ላይ ያለው የማቋቋሚያ አዋጅ ቢሆንም ንግድ ምክር ቤቶችን የሚመሩ አካላትም ጠንካራ መሪዎች እንደሌላቸው ተናግረዋል። የንግድ ምክር ቤቶች አመራሮች የንግድ ማኅበረሰቡን ጥያቄዎችና ፍላጎቶች ተረድተው መብቱን ከማስጠበቅ ይልቅ የግል ጥቅማቸውን የሚያራምዱ ናቸው ተብሎ የሚሰነዘሩ ወቀሳዎችን እርሳቸውም እንደሚጋሯቸው ገልጸዋል። በአብዛኛው በውጭ ጉዞዎች የተጠመዱ መሆናቸውን ጭምር በመጥቀስ እንዲህ ያለው ክፍተት ለመድፈንም ጠንካራ የኩባንያ መሪዎች ወደ አመራር እንዲመጡ በማድረግ እስካልተቻለ አዋጁን ማሻሻል ብቻ የተሻለ ነገር ሊመጣ ይችላል ብለው አያምኑም፡፡ ስለዚህ የማቋቋሚያ አዋጁ ሁሉንም ያቀፈ ሆኖ እንዲወጣ ማድረግ እንደተጠበቀ ሆኖ ጠንካራ ተቋምና አመራር መፍጠር ለመንግሥትም የሚጠቅመው በመሆኑ የአዋጅ ማሻሻያው ሥራው ብዙ ነገሮችን ያገናዘበ ቢሆን ንግድ ምክር ቤቶች የሚቋቋሙለት ዓላማ በተገቢው መንገድ እንዲያሳኩ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ የንግድ ኅብረተሰቡ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ሚና ወሳኝ የመሆኑን ያህል ሊደገፍ ከሚቻልባቸው ነገሮች አንዱ ከመነሻው አደረጃጀታቸውን የሚመለከተው ሕግ በጥንቃቄ ሲዘጋጅ መሆኑን የገለጹት አቶ ኢየሱስ አሁን በተሳበው አደረጃጀት ግን ይህ ሊሳካ ይችላል ብለው አያምኑም፡፡ ንግድ ኅብረተሰቡ ጠንካራ ማኅበር እንዲኖረው ከታሰበም አጠቃላይ የንግድ ምክር ቤቶች አሠራር አሁን ከሚታየው በተለይ ተዋቅሮ የማኅበሩ አባላትም በቀጥታ በኩባንያ ባለቤቶች እንዲወከል ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ንግድ ምክር ቤቶች ጠንካራ ሆነው እንዲወጡ ምን መደረግ እንዳለበት የተጠየቁት አቶ ክቡር በበኩላቸው ቀዳሚው ነገር መንግሥትና የንግድ ምክር ቤቶች አብረው መሥራት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት የሚለውን አስቀድመዋል፡፡ ይህንን ያሉበትን ምክንያት ሲያብራሩም ንግድ ምክር ቤት በአንድ በኩል መንግሥት በሌላ ጎራ ሆነው መሥራት የሚችሉበት ወቅት ባለመሆኑ ነው፡፡ ‹‹ንግድ ምክር ቤቶች የመንግሥት ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የንግድም ሆነ የኢንዱስትሪ ዘርፉ እንዲያድግ የመንግሥት ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል›› ያሉት አቶ ክቡር የመደጋገፍ አንዱ መገለጫ አብሮ የመሥራት ባህልን ማዳበር ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ማስተዋል እንደተቻለው ሁለቱ አካላት የተለያዩ ኃይሎች ተደርገው ይታዩ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ ‹‹የንግዱ ዓለምና የመንግሥት ዓለም የሚፈልገው ሁለቱ ተገናኝተው መነጋገር ሲችሉ የሚገኘው ጥቅም ከፍ ይላል›› የሚሉት አቶ ክቡር እርሳቸው አመራር በነበሩበት ሰዓት የመንግሥት ተወካይ የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ ውስጥ አባል ሆኖ እንዲካተት በማድረግ አብረው ይሠሩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ይህ አሠራር መንግሥት ያለውን ሐሳብ የሚያቀርብበትና ከንግድ ማኅበረሰቡ የሚነሳውን ሐሳብ ደግሞ ወደ መንግሥት ይዞ የሚሄድበትን ዕድል የፈጠረ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁንም ቢሆን ተቀራርቦ መሥራቱ ጠቀሜታ እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡ መንግሥት ከንግድ ምክር ቤቶች ጋር ተቀራርቦ መሥራት የሚገባው ለአገርና ሁለንታዊ ጥቅም እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ክቡር፣ የንግድ ምክር ቤቶችን ተቋማዊ ጥንካሬና ጉልበት በማየት ሲፈልግ ተቀራርቦ የሚሠራ ሳይፈልግ ደግሞ በሩቅ የሚያያቸው መሆን እንደሌለበት አስረድተዋል።‹‹ንግድ ማኀበረሰቡ እንደ መንግሥት ጉልበት ያለው ባለመሆኑ መንግሥት ከፈለገ የሚያናግረው፣ ካልፈለገ ደግሞ የማያናግረው መሆን የለበትም፤›› ብለዋል።መንግሥት የሚፈልገውን ብቻ እየመረጠ የሚያናግር ከሆነ የንግድ ማኅበረሰቡን የሚወክሉ ንግድ ምክር ቤቶች እየተዳከሙ ድምፃቸውም እየቀነሰ ለዕድገት የሚኖራቸው አስተዋጽኦም እየተመናመነ ስለሚሄድ በትብብርና በጋራ መሥራት ለሁሉም ዘርፍ ጠቃሚ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ሐሳብ እንዲሰጡን ያነጋገርናቸው የቀድሞ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት የቦርድ አባል ኢንዱስትሪና ንግድን ለየብቻ ነጣጥሎ እንዲደራጁ ማድረግ ለምክር ቤቶች ጠቀሜታ እንደማይሰጥ ተናግረዋል፡፡ አሁን ሥራ ላይ ያለው አዋጅ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ለንግድ ምክር ቤቶች አሠራር የማይመችና ብዙ ችግሮች ያለበት መሆኑ ሲገለጽ የቆየው አዋጁ በወቅቱ የነበረው ፓርቲ በቀጥታ እጅን በማስገባቱ መሆኑን ያስታውሳሉ፡፡ ንግድ ምክር ቤቶች አመራሮች የፖለቲካ መጠቀሚያ ሆነዋል ከሚል እምነት ይህንን የመንግሥት ሥጋት ለማስቀረት አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማትን የግዴታ የንግድ ምክር ቤቱ አባል እንዲሆኑ በማድረግ አዋጁ እንዲወጣ መደረጉ አጠቃላይ የንግድ ምክር ቤቶችን አሠራር ሊቀይረው መቻሉን አመልክተዋል፡፡ መንግሥት በወቅቱ እንዲህ እንዲሆን የፈለገበት ምክንያት እንደፈለገ ለመጠምዘዝ እንዳያመቸው ስለነበር አሁንም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይህ መደገም እንደሌለበት ይገልጻሉ፡፡ እኚሁ ስሜ አይጠቀስ ያሉት የንግድ ምክር ቤቶች የቦርድ አባል በተለይ ከአደረጃጀት አንፃር አሁን የታሰበው የተነጣጠለ አደረጃጀት ትግበራው ላይ እንቅፋት ሊገጥመው ይችላል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡ ይህንንም ሲያብራሩ አንድ ባለኢንዱስትሪ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የገቢና የወጪ ንግድ ፈቃድ ያለው በመሆኑ በየትኛው ምክር ቤት ሊታቀፍ ይችላል? የሚለው አጨቃጫቂ ስለሚሆን ነው፡፡ ባለኢንዱስትሪው ነጋዴም ነውና አሁን የታሰበው አደረጃጀት የበለጠ ችግር እንዳይፍጥር አጠቃላይ የንግድ ኅብረተሰቡን የያዘ ምክር ቤት ሆኖ አባልነቱ መሥፈርት ወጥቶለት ቢሠራ የሚበጅ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ የንግድ ምክር ቤቶችን ቀድሞ ከነበረው አደረጃጀት በኢንዱስትሪና በንግድ ከፋፍሎ ማደራጀቱ ተገቢ መሆኑን የሚያምኑ ወገኖች በበኩላቸው በተለይ ከሌላው በተለየ ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለመደገፍ ለብቻው መውጣቱ ጠቃሚ ነው የሚል ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ምክር ቤቱን ለማቋቋም ረቂቁን በአስተባባሪነት እያሰናዳ ያለው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢንዱስትሪም ምክር ቤትን ለማቋቋም የተፈለገበት ዋና ምክንያት ዘርፉን የበለጠ ለማሳደግ ይጠቅማል በሚል እንደሆነ መገለጹ አይዘነጋም፡፡ ከኢንዱስትሪው ባህሪም አንፃር ውጤታማ እንዲሆን እንዲህ ባለአደረጃጀት መውጣቱ ጠቃሚ መሆኑ ስለታመነበት ነው፡፡