ዛከርበርግ

ከ 1 ሰአት በፊት

በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች ያሉት የዓለማችን ዋነኛው ተጽእኖ ፈጣሪ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ፌስ ቡክ፣ ከተጀመረ 20 ዓመት ሆነው።

ይህ ሲጀመር “ዘ ፌስቡክ” የሚል ስያሜ የነበረው ማኅበራዊ ሚዲያ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በምድራችን ላይ በተከሰቱ የተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ የራሱ ሚና ነበረው።

ማርክ ዛከርበርግ እና የኮሌጅ ጓደኞቹ ዶርማቸው ውስጥ ሆነው ፌስቡክን ሲፈጥሩት የነበረው ገፅታ ከታች በፎቶው ላይ እንደምትመለከቱት ነበር።

በሂደትም የትየለሌ ጊዜ ቅርፁን ቀያይሯል። ከፍተኛ ሃብትንም ለማፍራት በመቻል ስሙ ይጠቀሳል።

ነገር ግን ሲጀመር የነበረውን ዓላማ አሁንም አንግቧል – ሰዎችን በበይነ መረብ አማካይነት መስተሳሰር።

እንደው ከተቻለ ደግሞ ከማስታወቂያ ሚሊዮንም፣ ቢሊዮንም ዶላሮች መሰብሰብ።

እነሆ ፌስቡክ 20 ዓመት ደፈነ።

ለመሆኑ ፌስቡክ ዓለማችንን የቀየረባቸው አራት መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

የፌስቡክ ፈጣሪ ማርክ ዛከርበርግ

1. የማኅበራዊ ሚድያውን መድረክ መቀየር

ከፌስቡክ ቀደሞ እንደ ማይስፔስ ዓይነት ሌሎች ማኅበራዊ ሚድያዎች ነበሩ።

ነገር ግን የማርክ ዛከርበርግ የፌስቡክ መድረክ በአውሮፓውያኑ 2004 ሲመሠረት ከመመንጠቅ ያገደው አልነበረም።

ፌስቡክ ገና በአንድ ዓመቱ እየዳኸ ሳለ ነው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎችን ያፈራው።

በአራት ዓመት ውስጥ ደግሞ ማይስፔስን ሰልቅጦ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማቅረብ ጀመረ።

ከጓደኞቻችሁ ጋር ማታ ወጥታችሁ ፍላሽ ያለው ካሜራ ይዛችሁ ፎቶ ካነሳችሁ በኋላ ፎቶ ለጥፎ “ታግ ማድረግ” የታዳጊነት ዘመን ትዝታ እየሆኑ መጥተዋል።

በርካታ ሰዎች በፌስቡክ ሱስ የተጠመዱት ድረ-ገፁ ያለማቋረጥ አዳዲስ ይዘት ይዞ ብቅ በማለቱ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2012 ፌስቡክ ለመጀመሪያ ጊዜ የወርሃዊ ተጠቃሚዎቹ ቁጥር ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሆነ።

በ2021 በየቀኑ ፌስቡክን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ዝቅ ብሎ 1.92 ቢሊዮን ከመግባቱ በቀር ቁጥሩ እየጨመረ እንጂ እየቀነሳ አልመጣም።

ብዙም ተጠቃሚ ወደሌለባቸው አገራት በመዛመትም እንዲሁም ነፃ የኢንተርኔት አገልግሎት በመስጠት ጭምር ኩባንያው የተጠቃሚዎችን ቁጥር ከፍ ማድረግ ችሏል።

በ2023 መጨረሻ ፌስቡክ በቀን ከ2 ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሉት ይፋ አድርጓል።

እርግጥ ነው በታዳጊዎች ዘንድ የፌስቡክ ተወዳጅነት እየቀነሰ መጥቷል። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ከዓለማችን ማኅበራዊ ሚድያዎች እጅግ ተወዳጅ ከመሆን አላገደውም።

አንዳንዶች ፌስቡክ እና ተቀናቃኝ ማኅበራዊ ሚድያዎች በሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጨምር አድርጓል ይላሉ።

ሌሎች ደግሞ ሱስ የሚያስዙ አጥፊ ቴክኖሎጂዎች አድርገው ይቆጥሯቸዋል።

ላይክ ሌሎች የፌስቡክ ሪያክሽኖች

2. ግላዊ መረጃ ዋጋ እንዲኖረው ማድረግ

ላይክ እና ዲስላይክ ሲመነዘር ረብጣ ዶላር እንደሚወጣው ቀድሞ የገባው ፌስቡክ ነው።

የፌስቡክ እናት ኩባንያ የሆነው ሜታ [ጉግልን ሳንረሳ] በማኅበራዊ ሚዲያው መድረክ ከሁሉ የላቀበት የሙያ መስክ ነው።

ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት 2023 በሦስተኛው ገሚስ ብቻ ሜታ ከማስታወቂያ 34 ቢሊዮን ዶላር አፍሷል። 11.5 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ትርፍ ነው።

ሜታ ማስታወቂያዎቹን የሚቸበችበው የተጠቃሚዎችን ግላዊ [የግል ማለት ቢከብድም] መረጃችንን ተጠቅሞ ነው።

ነገር ግን ፌስቡክ የመረጃ ስብሰባ የሚውለው “ለበጎ” ተግባር ብቻ አይደለም የተጠቀመበት።

ሜታ በተደጋጋሚ ግላዊ መረጃን በዝብዟል ተብሎ ቅጣት ተከናንቧል።

የኬምብሪጅ አናሊቲካ ታሪክ የሚረሳ አይደለም። ይህ የሆነው በ2014 (እአአ) ነው። ፌስቡክ በዚህ ክስ ምክንያት 725 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት እንዲከፍል ግድ ሆኖበታል።

በ2022 ደግሞ ግላዊ መረጃ ከቋቱ አውጥቶ ሸጧል በሚል በአውሮፓ የ265 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ተጥሎበታል።

ባለፈው ዓመት ደግሞ የአይሪሽ መረጃ ጥበቃ ኮሚሽን እስከ ዛሬ ተሰምቶ የማያውቅ 1.2 ቢሊዮን ዩሮ እንዲከፍል ፌስቡክ አዟል።

የዙከርበርግ ኩባንያ ይህ ቅጣት የተላለፈበት የአውሮፓውያንን መረጃ ከአህጉሪቱ ባሻገር አሳልፎ ሰጥቷል ተብሎ ነው።

ፌስቡክ ይግባኝ ጠይቆ ምላሹን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።

ትራምፕ ማሕበራዊ ሚድያ እየተጠቀሙ

3. ፌስቡክ በይነ-መረብን ፖለቲካዊ አደረገው

ፌስቡክ ማስታወቂያ ሲያቀርብልዎ ለእርስዎ የሆነውን መርጦ ነው። ለዚህ ነው ምርጫ ሲደርስ ተመራጨነቱ እየጨመረ የሚመጣው።

የአሜሪካ ምርጫ 2020 ሊካሄድ አምስት ወራት ሲቀሩት የተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን 40 ሚሊዮን ዶላር መድቦ በፌስቡክ ማስታወቂያ አስነግሮ ነበር።

ርዕዮተ-ዓለማቸውን ለነባር እና ለአዳዲስ ተከታዮቻቸው ማሰራጨት የፈለጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፌስቡክን ተመራጭ እና አማራጭ መንገድ አድርገውታል።

በበርካታ አረብ አገራት ተቀስቅሶ የመንግሥታት ለውጥ እና በአንዳንዶ ቹ ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነትን ከቀሰቀሰው “የአረብ ስፕሪንግ” ወቅት ተቃውሞ ለማስተባበር፣ እንዲሁም ወቅታዊ ዜና ለማሰራጨት ፌስቡክ እና ትዊተር ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

ነገር ግን ፌስቡክን ለፖለቲካ ዓላማ መጠቀም ከትችት አልተረፈም።

በ2018 የተባበሩት መንግሥታት ያወጣው ዘገባ፤ ሰዎች ፌስቡክን ተጠቅመው በምያንማር “ግጭት ቀስቅሰዋል” ሲል ይወቅሳል። ፌስቡክም በዚህ ይስማማል።

ማርክ ዛከርበርግ

4. ፌስቡክ ግዙፉን ሜታ መፍጠር

ፌስቡክ ስኬትን ያጎናፀፈው ማርክ ዛከርበርግ ሜታ የተሰኘ ግዙፍ የማኅበራዊ ሚድያ እና የቴክኖሎጂ ማዕከል አቋቁሟል።

ይህ ኩባንያ በዓለማችን አሉ ከሚባሉ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ተርታ የሚመደብ ነው።

ፌስቡክ ስሙን ወደ ሜታ የቀየረው በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2022 ነው።

ቢሆንም ፌስቡክ እነ ዋትስአፕ፣ ኢንስታግራም እና ኦኩለስን የጠቀለለው ከሜታ መወለድ ቀድሞ ነው።

ሜታ እንደሚለው በየቀኑ 3 ቢሊዮን ሰዎች ቢያንስ አንዱን ምርቱን ይጠቀማሉ።

ግዙፉ ሜታ ተቀነቃኝ መተግበሪያዎችን መግዛት ሲያቅተው በተመሳሳይ ምርት ተጠቃሚዎችን እያታለለ ነው እያሉ የሚወቅሱት ብዙ ናቸው።

ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ላይ ታይተው የሚጠፉት “ስቶሪዎች” ከስናፕቻት የተቀዱ ናቸው፤ የኢንስታግራም “ሪል” ደግሞ ከቲክቶክ የተኮረጀ ነው።

አዲሱ የሜታ ምርት የሆነው ትሬድስ ደግሞ የትዊተር መልክ አለው፤ የሚሉ ወቀሳዎች ይሰማሉ።

ውድድሩ ጨምሯል፤ ቁጥጥሩም እንደዚያው። ይህን ለማለፍ ሜታ የሚጠቀማቸው መንገዶች አሉ።

ቀጣዮቹ 20 ዓመታት?

የፌስቡክ አቅም እየጨመረ መምጣት እና ያለው ተፅዕኖ ማርክ ዛከርበርግ ምን ያህል ቴክኖሎጂውን ጠንቅቆ እንደያዘው ምስክር ነው።

ነገር ግን በሚቀጥሉት 20 ዓመታት እጅግ ተወዳጁ ማኅበራዊ ሚድያ ሆኖ ይቆያል ወይ? የሚለው ጥያቄ መልሱ ከባድ ሊሆን ይችላል።

ሜታ አሁን ሜታቨርስ እያለ ወደሚጠራው ፅንሰ-ሐሳብ እያቀና ነው። ይህን የሚያደርገው አፕልን ለመገዳደር ነው።

ሜታ ሌላኛው ሐሳቡ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ላይ ነው።

ኩባንያው ከተጠነሰሰበት ሰዎች የማገናኘት ሐሳብ እየሸሸ ሲመጣ ምን ሊገጥመው ይችላል? የሚለውን አብረን የምናየው ይሆናል።