ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር እና ደብረፂዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር)
የምስሉ መግለጫ,ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር እና ደብረፂዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር)

1 የካቲት 2024, 12:31 EAT

ከተመሠረተ ግማሽ ምዕተ ዓመት ሊሞላው የተቃረበው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከአማጺ ቡድንነት ተነስቶ በአገር መሪነት ጉልህ ሚና ይዞ ከቆየ በኋላ፣ ከማዕከላዊ መንግሥት ተገፍቶ ተመልሶ ወደ ትግራይ ክልል ከተመለሰ በኋላ ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት ወደ ሽምቅ ተዋጊነት ለመመለስ ተገዶ ነበር።

ደም አፋሳሹ የእርስ በርስ ጦርነት ያስቆመውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ተከትሎ በትግራይ ክልል የበላይ ገዢ በመሆን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ዳግም ቦታ ለማግኘት ጥረት እያደረገ መሆኑን አንዳንዶች ቢናገሩም፣ የህወሓት መሪዎች ግን ዋና ትኩረታቸው ትግራይ መሆኗን ይናገረሉ።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈውን እና ከፍተኛ መጠን ላለው የሃብት እና ንብረት ውድመት ምክንያት ከሆነው ከትግራይ ጦርነት እና ከአፈታቱ ጋር በተያያዘ እየተተቸ የሚገኘው ህወሓት፣ የስትራቴጂካዊ አመራር ችግር እየገጠመው መሆኑን የፓርቲው የቁጥጥር ኮሚሽን በተደጋጋሚ ሲያሳውቅ ተደምጧል።

ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት በሚልም በሥራ ላይ ያሉ አምስት ሥራ አስፈፃሚ አባላት፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የትግራይ ሠራዊት አዛዦችን እና ከፓርቲው የተሰናበቱ የቀድሞ አመራሮችን በመያዝ በሩን ለስብሰባ ዘግቶ ከሁለት ወር በላይ ቆይቷል።

ህወሓት ተመሳሳይ ችግር ሲያጋጥመው ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ከአመራር ጋር የተያያዙ በርካታ ፈተናዎችን እና ውጣ ውረዶችን ገጥመውታል።

የህወሓት የመጀመርያው ፈተና ተብሎ የሚጠቀሰው ክስተት ፓርቲው በተመሠረተበት አንደኛ ዓመቱ ያጋጠመ ሲሆን “ሕንፍሽፍሽ” (ክፍፍል/ትርምስ) በመባል የሚታወቅ እና በአመራሮቹ ውስጥ ያጋጠመ መከፋፈል ነው።

በወቅቱ ልዩነቶቹ የተፈቱበት መንገድ ኢ-ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እና በቡድኑ ላይ ጠባሳ ትቶ ያለፈ እንደነበር ብዙዎች ይናገራሉ።

በ1977 ዓ.ም. ያጋጠመ የፖለቲካ ልዩነት ደግሞ የፓርቲው መሥራቾች እና ከፍተኛ አመራሮች የነበሩትን አቶ አረጋዊ በርሄ እንዲሁም አቶ ግደይ ዘርዓጽዮንን ለስደት ዳርጓል።

ቀጣዩ መከፋፈል በ1993 ዓ.ም. የተከሰተ ሲሆን፣ በፓርቲው የፖለቲካ መዋቅር እና በተለይም በትግራይ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አስከትሏል ተብሎ ይታመናል።

በቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ የሚመራው ቡድን በወቅቱ የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩትን አቶ ገብሩ አስራትን እና የቀድሞ የሥራ አስፈፃሚ አባላትን አቶ ስዬ አብርሃ እንዲሁም ወይዘሮ አረጋሽ አዳነን ከሥልጣን በማባረር የፓርቲ እና የመንግሥት ሥልጣንን በመያዝ ቀጠለ።

ማባረሩ በፖለቲከኞች ላይ ብቻ አላቆመም። ከልዩነቱ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም የነበሩት ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ እና የአየር ኃይል አዛዥ ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖትንም ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል።

በወቅቱ “አንጃ” ተብሎ የተባረረውን ቡድን ይደግፋሉ የተባሉ በርካታ ሰዎችም ከመንግሥት ኃላፊነታቸው ተሰናብተዋል።

ከዚህ ባሻገር በፓርቲው ታሪክ የቅርብ ጊዜ ፈተና ተብሎ የሚጠቀሰው በ2010 ዓ.ም. የተደረገው የአመራር ለውጥ ነው።

በወቅቱ አስር ቀናት በወሰደው ግምገማ የፓርቲው አመራርን “በፀረ-ዴሞክራሲያዊነት እና ቡድንተኝነት” በመገምገም ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ የፓርቲውን አመራርነት በመረከብ የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት የሆኑትን አቶ አባይ ወልዱን ከሥራ አስፈፃሚነት በማንሳት ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት አውርዷል።

የሥራ አስፈፃሚ አባል የነበሩትን ወይዘሮ አዜብ መስፍንንም ከኃላፊነት በማንሳት ከፓርቲው አባልነት አግዷል።

አቶ በየነ መክሩንም ከፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ ዝቅ አድርጓል።

ይህን ተከትሎ ፓርቲው ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤልን የድርጅቱ ሊቀመንበር እና የክልሉ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት፣ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄርን ምክትል አድርጎ ሾመ።

በእነዚህ ሁለት ሰዎች የሚመራው ህወሓት የፌደራል መንግሥት ሕገወጥ ብሎ የፈረጀውን ምርጫ አካሄደ። በፓርቲው እና በፌዴራል መንግሥት መካከል የነበረው የፖለቲካ ውጥረት ተባብሶም በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም. ላይ ጦርነት ተቀሰቀሰ።

የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎም በርካታ የህወሓት መሪዎች እና ነባር ታጋዮች የወጣትነት ዘመናቸውን ወደ አሳለፉበት የትግራይ በረሃ ለመመለስ ተገደዱ።

በተለያየ የፖለቲካ አቋም የሚታወቁት የክልሉ ተወላጆች የትግራይ መከላከያ ሠራዊት በመባል የሚታወቀውን ጦር መሥርተው ከስምንት ወራት ትግል በኋላ ዋና ከተማዋን መቀሌን ጨምሮ አብዛኛውን የትግራይ ክፍል ተቆጣጠሩ።

ህወሓትም “ሕዝብ የመረጠው መንግሥት ወደ ቦታው ተመልሷል” ብሎ ነበር።

ጦርነቱን ለማቆም የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላም በህወሓት የበላይነት የተያዘ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቋመ።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በአቶ ጌታቸው ረዳ በሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር እና በህወሓት አመራሮች መካከል ልዩነቶች እንደተፈጠሩ የሚገልጹ መረጃዎች በስፋት ሲደመጡ ቆይተዋል።

የፓርቲው የቁጥጥር ኮሚሽንም ፓርቲው “ብቃት ያለው አመራር በማጣቱ እየፈራረሰ መሆኑን” በተደጋጋሚ አስታውቆ ነበር።

ህወሓት ይህንን የአመራር ችግር ለመፍታት በሚል ከሁለት ወራት በላይ በዝግ ስብሰባ ሲያካሂድ ቆይቶ፣ ስብሰባውን ትናንት ረቡዕ ጥር 22/2016 ዓ.ም. ማጠናቀቁን ቢገልጽም የሚጠበቀውን የአመራር ለውጥ ግን አላደረገም።

ህወሓት የአመራር ለውጥ ማድረግ ለምን ተሳነው?

በመቀለ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ስትራቴጂክ ጥናት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ገብረመድኅን ገብረሚካኤል፣ የህወሓት የአመራር ቀውስ ለብዙ ዓመታት የቀጠለ መሆኑን በመጥቀስ፣ የፓርቲው እውነተኛ እምነት ይህ ነው ወይ የሚል ጥያቄ ያነሳሉ።

“ህወሓት አሁን ብቻ ሳይሆን የቆየ የአመራር ቀውስ ገጥሞታል። በዚህ መልኩ ራሱን ከገመገመ ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል። ታድያ እንደዚህ ከሆነ የችግሩ ምንጭ የሆነው አመራር በተለይም ስትራቴጂካዊ እየተባለ በሚጠራው አመራር ላይ ለውጥ ይመጣል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

“ሆኖም ግን ይህ እየታየ አይደለም። ምክንያቱም አንደኛ ‘ችግሩ አለብኝ’ ብሎ እያመነ ያለው ከውጭ ጫና ስላለበት እና ተደጋጋሚ ትችት ስለሚደርስበት እሱን ለማረጋጋት እንጂ ‘በእርግጥ እምነቱ ነው ወይ? በዚህ መሰረት ራሱን ለመፈተሽ እና ለመታገል ቁርጠኛ ነው ወይ?’ የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። ብልሹ መሪዎችን እና ድክመቶቹን ለመለወጥ ቅን የሆነ እውነተኛ የውስጥ ትግል ስለሌለው ይመስለኛል” በማለት ያስረዳሉ።

ከመሪዎቹ መካከል በአቅም ጎላ ብሎ መታየት የሚችል ተደማጭነት ያለው ሰው አለመኖሩንም እንደ ሁለተኛ ምክንያት አቶ ገብረ መድኅን ይጠቅሳሉ።

“ሁሉም በተመሳሳይ የብልሽት ደረጃ ላይ ናቸው። ውድቀቱ የአንድ ወይም የሁለት አይደለም። ድርጅታዊ፣ ስትራቴጂያዊ እና የአመራር ነው። የተሻለ ሆኖ የሚታይ ግለሰብ ወይም መሪ የለም። ማን ከማን ይበልጣል? ማን ነው ሊወጣ የሚችለው? ማን ይለወጣል? የሚል ጥያቄ አለ። እኔም እንደዛ ነው የማምነው” ብለዋል።

ቀደም ሲል በፖለቲካው ተሳትፎ የነበራቸው በአሁኑ ወቅት ግን የትግራይን ፖለቲካን በመከታተል የሚተነትኑ በአዲግራት የዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አብርሃ ተክሉም ከዚህ ጋር የሚስማማ ሐሳብ አላቸው።

“ህወሓቶች ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እስካለፉበት ድረስ በአንፃራዊ ሁኔታ ያጋጠሙ ነገሮችን በተገቢው ማዕቀፍ ውስጥ አስገብተው የማየት ብቃቱ ነበራቸው። ‘ምንድን ነው ያጋጠመን? ለምን ተከሰተ?’ ይላሉ። ዓለም አቀፋዊ እና ቀጠናዊ ሁኔታን እንዲሁም ራሳቸውን ይመለከቱ ነበር።

“አሁን ያለው አመራር ግን ከዚህ ሂደት የተለየ ነው። የሐሳብ ለውጥ እንዳያመጣ በሐሳብ ደረጃ አይደሉም እየተሟገቱ ያሉት። የአመራር ለውጥ ያላመጡበት ምክንያት ደግሞ እርስ በርስ እየተጨቃጨቁ እና እየተባሉ ስላሉ ነው፤ ይህ ደግሞ ወደ ከፍተኛ አለመተማመን እና ጥርጣሬ ወስዷቸዋል” ብለዋል።

መምህር አብርሃ ተክሉ የውጭ ጣልቃ ገብነትም ሌላ ችግር ሊሆን እንደሚችል “ፓርቲው በተነጻጻሪ ዝግ በሆነ ሂደት ችግሮቹን የመፍታት ልምድ ነው ያለው። ዛሬ ላይ ግን ምስጢሮችን መደበቅ አይችልም። መረጃዎች በየጊዜው ነው የሚለቀቁት። በዚህ መጠንም ከውጪ ሆኖ ሁኔታውን ሊያባብሰው የሚሻ አካል በሚፈልገው ሰው በኩል የማተራመስ እንዲሁም መረጋጋት እንዳይኖር የማድረግ ዕድሉ ሰፊ ነው” በማለት ያስረዳሉ።

ህወሓት ችግሮቹን በስብሰባ እና በግምገማ የመፍታት ልምዱን የሚያደንቁ በርካታ ሰዎች ቢኖሩም፣ በፓርቲው ውስጥ የተለመደ የቡድንተኝነት አካሄድ ግን ፓርቲው እውነተኛ ለውጥ እንዳያመጣ እንቅፋት ሆኗል ይላሉ። በአሁኑ ጊዜም ፓርቲው በተመሳሳይ ሁኔታ በቡድንተኝነት ተከፋፍሎ ከሐሳብ ትግል ወጥቶ በመወነጃጀል እና በመካሰስ ላይ እንደሚገኝ የሚያመለክቱ መረጃዎች ከፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ሳይቀር እየተደመጡ ነው።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በአንድ ሕዝባዊ መድረክ ላይ ሲናገሩ፣ ፓርቲው ለሁለት ወራት ባካሄደው ስብሰባ በሕዝብ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ አለመወያየቱን እና በግምገማው ወቅት ወደ አካባቢያዊነት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን ለማስተሳሰር የሞከሩ መሪዎች እንዳሉ በግልጽ አመልክተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የህወሓት የቀድሞ አመራር አባል የሆኑት አቶ ስብሃት ነጋ በቅርቡ ትግራይ ሚድያ ሀውስ ለተባለው ቴሌቭዥን በሰጡት ቃለ-መጠይቅ በስም ያልጠቀሷቸው የተወሰኑ የክልሉ ሠራዊት አመራር እና የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ አባላትን “የሲአይኤ ወኪሎች” በማለት ፓርቲውን ለማፍረስ እያሴሩ ነው ሲሉ ከስሰዋል።

በአመራሩ መካከል ያለው ልዩነት የሐሳብ ወይስ የጥቅም ?

የመቀለ ዩኒቨርሲቲው መምህር ገብረመድኅን እንደሚሉት በፓርቲው አመራሮች መካከል ያለው መቧደን በጥቅም ላይ የተመሠረተ ነው።

“እኔ ከጥቅም አልፈው በሃሳብ እና በሕዝብ ጉዳዮች ላይ የተመሠረቱ አይመስለኝም። አንደኛው በሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ወደ ሥልጣን ለመምጣት ነው የሚጥሩት” በማለት ያስቀምጣሉ።

መምህር አብርሃም ተክሉም ተመሳሳይ መረጃ እና ግንዛቤ ነው ያላቸው።

“ጥቅም ነው። መቧደኑ ለውጥን በሚፈልጉ እና ለውጡን በማይቀበሉት የሚገለጽ አይደለም። ‘አሮጌው አዲስ አመራሮች ወደፊት እንዳይመጡ እየተከለከለ ነው’ የሚለው አባባልም ከእውነታው የራቀ ነው” ይላሉ።

ህወሓት ረቡዕ ጥር 22/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ለ41 ቀናት ያካሄደውን ስብሰባ እና ግምገማ እንዳጠናቀቀ፤ “የስትራቴጂክ አመራር ድክመት ቁልፍ ችግሩ መሆኑን ለይቶ ማወቅ እንደቻለ” በመግለጽ በቀጣይ የአመራር ለውጥ እንደሚያደርግ አመልክቷል።

የፓርቲው የመንፈስ አባት ናቸው የሚባሉት አቶ ስብሃት ነጋ ከቴሌቪዥን ጣቢያው ጋር በነበራቸው ቆይታ “ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ከህወሓት ጋር ሊወዳደር የሚችል ፓርቲ የለም” ሲሉ አስረግጠው ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለቱ የትግራይ ምሁራን እንደሚገመግሙት ግን ፓርቲው መሠረታዊ ለውጥ ካላመጣ ህልውናውን በቅርቡ የሚያከትም ይሆናል።

በመቀለ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሑሩ አቶ ገብረመድኅን ገብረሚካኤል “ህወሓት ተጠናክሮ ይወጣል ብዬ አልጠብቅም። ለተወሰነ ጊዜ መቆየቱ አይቀርም። ምክንያቱም ሌላ የተዘጋጀ ኃይል እና አማራጭ የለም። እንደ ፓርቲ ግን በተለይም ሥልጣን ላይ ሆኖ ራሱን አስተካክሎ ወደ ተሻለ ደረጃ ይሸጋገራል ብዬ አላምንም” ሲሉ ደምድመዋል።

የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ መምህሩ አብርሃም ተክሉ በበኩላቸው “የተጠላ እና የተናቀ ፓርቲ” ያሉት ህወሓት መሠረታዊ ለውጥ ካመጣ መዳን ይችላል የሚል ግምት አላቸው።

“ለሕዝብ ሲሉ የግል ፍላጎታቸውን ትተው ራሳቸውን ለመስዋዕትነት ዝግጁ እስከማድረግ ከመጡ መትረፍ ይችላሉ” በማለት ሐሳባቸውን ቋጭተዋል።