የምክር ቤቱ አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ እና የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)
የምስሉ መግለጫ,የምክር ቤቱ አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ እና የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)

ከ 2 ሰአት በፊት

ላለፉት ስድስት ወራት በዋናነት በአማራ ክልል ላይ ተጥሎ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም የቀረበውን ሐሳብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጸደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ አርብ ጥር 24/2016 ዓ.ም. ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 ለማራዘም የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ አጽድቋል።

በዛው ልዩ ስብሰባ የሕዝብ ተወካዮች ምክረ ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም በሁለት ተቃውሞ እና በሦስት ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል።

በሚቀጠለው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የስድስት ወር ጊዜው የሚጠናቀቀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማራዘም ያስፈለው “ተጨማሪ ሥራዎች በመኖራቸው” እንደሆነ በዛሬው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ መገለጹን ብሔራዊ የቴሌቪዥን ኢቲቪ ዘግቧል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መራዘም በተመለከተ ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብን የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ለምክር ቤቱ አቅርበው ማብራሪያ ሰጥተው በሕዝብ እንደራወሴዎች ውይይት እንደተደረገበት ተገልጿል።

በተጨማሪም ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ የሥራ ዘመንን ለማራዘም ለምክር ቤቱ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በሁለት ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል።

የፌደራሉ መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የጣለው የአማራ ክልል ያጋጠመውን አለመረጋጋት ለመቆጣጠር የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገናባ ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ነው።

ይህንን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. የደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ በእረፍት ላይ የነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነሐሴ 8/2015 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ መጽደቁ ይታወሳል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤትም ““በትጥቅ የተደገፈ ሕገወጥ እንቅስቃሴ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር ወደ ማይቻልበት ደረጃ ተሸጋግሯል” ሲል የአዋጁን አስፈላጊነት ገልጾ ነበር።

ካለፈው ዓመት አጋማሽ ወዲህ በአማራ ክልል ውስጥ የተከሰተውን እና እየተባባሰ የመጣውን የፀጥታ መደፍረስ ለመቆጣጠር የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአማራ ክልል እና እንደ አስፋላጊነቱ በቀሪው የአገሪቱ ክፍል ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግ ነው።