
2 የካቲት 2024, 11:11 EAT
ላለፉት ስድስት ወራት በዋናነት በአማራ ክልል ላይ ተጥሎ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም የቀረበውን ሐሳብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጸደቀ።
ምክር ቤቱ ዛሬ አርብ ጥር 24/2016 ዓ.ም. ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 ለማራዘም የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ አጽድቋል።
በዛው ልዩ ስብሰባ የሕዝብ ተወካዮች ምክረ ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም በሁለት ተቃውሞ እና በሦስት ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል።
በሚቀጠለው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የስድስት ወር ጊዜው የሚጠናቀቀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማራዘም ያስፈለው “ተጨማሪ ሥራዎች በመኖራቸው” እንደሆነ በዛሬው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ መገለጹን ብሔራዊ የቴሌቪዥን ኢቲቪ ዘግቧል።
- በአማራ ክልል የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምን አካቷል?5 ነሐሴ 2023
- የቀድሞው የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ምን አሉ?15 ነሐሴ 2023
- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማራዘም በሚቀርብ ሐሳብ ላይ ለመወሰን የተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ልዩ ስብሰባ ያደርጋል1 የካቲት 2024
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መራዘም በተመለከተ ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብን የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ለምክር ቤቱ አቅርበው ማብራሪያ ሰጥተው በሕዝብ እንደራወሴዎች ውይይት እንደተደረገበት ተገልጿል።
በተጨማሪም ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ የሥራ ዘመንን ለማራዘም ለምክር ቤቱ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በሁለት ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ምክር ቤቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከማራዘሙ በፊት በሰጡት አስተያየት አዋጁ የሚያራዘም ከሆነ በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ ሊያስከትል የሚችለው አሉታዊ ተጽእኖ አሳሳቢ ነው ብለው ነበር።
ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚራዘም ከሆነ የግጭት ተጎጂ በሆኑ፣ በሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ባሉ እና ለፍርድ ሳይቀርቡ ለረዥም ጊዜያት በእስር ላይ በሚቆዩ ሰዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ የሚያመጣው አሉታዊ ተጽእኖ አሳሳቢ መሆኑን በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የፌደራሉ መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የጣለው የአማራ ክልል ያጋጠመውን አለመረጋጋት ለመቆጣጠር የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገናባ ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ነው።
ይህንን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም. የደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ በእረፍት ላይ የነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነሐሴ 8/2015 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ መጽደቁ ይታወሳል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤትም ““በትጥቅ የተደገፈ ሕገወጥ እንቅስቃሴ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር ወደ ማይቻልበት ደረጃ ተሸጋግሯል” ሲል የአዋጁን አስፈላጊነት ገልጾ ነበር።
ካለፈው ዓመት አጋማሽ ወዲህ በአማራ ክልል ውስጥ የተከሰተውን እና እየተባባሰ የመጣውን የፀጥታ መደፍረስ ለመቆጣጠር የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአማራ ክልል እና እንደ አስፋላጊነቱ በቀሪው የአገሪቱ ክፍል ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግ ነው።