ማርኮ ራዱዋኖ
የምስሉ መግለጫ,ማርኮ ራዱዋኖ

3 የካቲት 2024, 09:09 EAT

አንሶላ ተጠቅሞ ከፍተኛ ጥበቃ ሲደረግለት ከነበረው የጣሊያን እስር ቤት አምልጦ የነበረው የአደገኛ የማፊያ ቡድን መሪ ፈረንሳይ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋለ።

ማርኮ ራዱዋኖ ከእስር ቤት ካመለጠ በኋላ በአውሮፓ ውስጥ በጥብቅ ከሚፈለጉ ወንጀለኞች ተርታ ተቀምጦ ነበር።

የፈረንሳይ እና የጣሊያን ባለሥልጣናት ግለሰቡ ፈረንሳይ ውስጥ መያዙን አረጋግጠዋል።

ማርኮ በአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር እና በሌሎች ወንጀሎች የ24 ዓመት እስር ከተፈረደበት በኋላ ነበር ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግለት እስር ቤት ያመለጠው።

የደኅንነት ካሜራዎች ማርኮ አንሶላ ተጠቅሞ በእስር ቤቱ ግድግዳ ላይ ተንጠላጥሎ ሲወርድ እና እየሮጠ ሲያመልጥ አሳይተዋል።

ማርኮ ራዱዋኖ ከእስር ቤቱ ሲያመልጥ የሚያሳይ የደኅንነት ካሜራ ምስል
የምስሉ መግለጫ,ማርኮ ራዱዋኖ ከእስር ቤቱ ሲያመልጥ የሚያሳይ የደኅንነት ካሜራ ምስል

ከማርኮ ራዱዋኖ በተጨማሪ የማርኮ ቀኝ እጅ ነው የሚባለው አማካሪው ጂያንሉጂ ትሮኢኖ ስፔን ውስጥ በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን የጣሊያን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

የአውሮፓ አገራት ፖሊስ ጥምረት የሆነው ዩሮፖል ማርኮ ራዶኖ “ጨካኝ ገዳይ” ሲል ይገልጸዋል።

ማርኮ ራዱዋኖ እና አማካሪው ጂያንሉጂ ትሮኢኖ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ለተደራጁ የማፊያ ቡድኖች ትልቅ ኪሳራ ነው ሲሉ የጣሊያ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ማቲዮ ፒአንቴዶሲ ተናግረዋል።

የ40 ዓመቱ ማርኮ በአንድ ወቅት በጣሊያን አራተኛው ትልቁ የማፊያ ቡድን የሚባለው ፎጊአ ቡድን መሪ ነው።

የፈረንሳይ ዜና ወኪል የሆነው ኤኤፍፒ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ማርኮ በቁጥጥር ስር የዋለው በፈረንሳይዋ አሌሪያ ከተማ ከአንዲት ወጣት ሴት ጋር ምግብ ቤት ውስጥ እየተመገበ ሳለ ነበር።