በግለሰቡ የእቃ ማከማቻ ጋራዥ ውስጥ የተገኘው ሮኬት
የምስሉ መግለጫ,በግለሰቡ የእቃ ማከማቻ ጋራዥ ውስጥ የተገኘው ሮኬት

ከ 9 ሰአት በፊት

የአሜሪካዋ ዋሽንግተን ግዛት ፖሊስ ከአንድ ግለሰብ ቤት የአሮጌ እቃዎች ማከማቻ ጋራዥ ውስጥ የተገኘው የዛገ ሮኬት የኑክሌር ሚሳኤል መሆኑን አስታወቀ።

ባለፈው ረቡዕ በኦሃዮ ግዛት ቤልቩ ከተማ የሚገኝ ወታደራዊ ሙዚየም አንድ እምብዛም ያልተለመደ ስጦታ እንደተበረከተለት በመግለጽ ለፖሊስ ሪፖርት ማድረጉን ተከትሎ ነው ጉዳዩ ይፋ የሆነው።

ይህ እንደ ጦር ቅርስነት በስጦታ እንዲቀመጥ ሙዚየሙ እንዲወስደው የጠየቁት ግለሰብ ጥያቄ ግራ መጋባትን በመፍጠሩ፣ ፖሊስ ሪፖርቱ ከደረሰው በኋላ ቦምብ አምካኝ ቡድን ወደ ግለሰቡ ቤት ልኳል።

ፖሊስ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የተገኘው ቁስ “1.5 ኪሎ ቶን የኑክሌር አረር መሸከም የሚችል ከአየር ላይ የሚተኮስ ሮኬት” መሆኑን በዝርዝር አመልክቷል።

ነገር ግን በሮኬቱ ውስጥ ሊተኮስ የሚችል የኑክሌር አረር የሌለበት ቀፎ መሆኑን በመግለጽ፣ በዚህም ሳቢያ በተገኘበት ስፍራ በሚገኝ ማኅበረሰብ ላይ ጉዳይ የሚያደርስ እንዳልሆነ አረጋግጧል።

የቤልቩ ፖሊስ መምሪያ ቃል አቀባይ የሆኑት ሴዝ ታይለር አርብ ዕለት ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ የተገኘው ቁስ “ለሮኬት ማስወንጨፊያነት የሚያገለግል ጋዝ ማከማቻ ዓይነት ነው።”

ጨምረውም የተገኘውን ነገር በተመለከ “የቦምብ አምካኝ ቡድን አባላት ስለዚህ ቀፎ ብረት መግለጫ ማውጣት አስፈላጊ አይደለም ብለው ነበር” በማለት ጉዳዩ “ብዙም የሚያሳስብ አይደለም” ሲሉ አቃለውታል።

የኑክሌር አረር መሸከም የሚችል ሮኬት
የምስሉ መግለጫ,የኑክሌር አረር መሸከም የሚችል ሮኬት

በአንድ ግለሰብ ቤት የተገኘውን የኑክሌር አረር አቃፊውን በተመለከተ ለፖሊስ ጥቆማ የደረሰው ዳይተን ኦሃዮ ውስጥ ከሚገኝ የአሜሪካ አየር ኃይል ብሔራዊ ሙዚየም ነበር።

ቁሱ በቤታቸው ውስጥ የተገኘው ግለሰብ ማንነት ያልተገለጸ ሲሆን፣ በመገናኛ ብዙኃን ለጉዳዩ በተሰጠው ሽፋን ምክንያት “በጣም መበሳጨታቸውን” የፖሊስ ቃል አቀባይ ተናግረው፣ ሙዚየሙ ጉዳዩን ለፖሊስ እንደሚያሳውቅ ስላላሳወቃቸው “ፖሊስ ይደውልልኛል ብለው አላሰቡም ነበር” ብለዋል።

ግለሰቡ ፖሊስ የጦር መሳሪያ ቅሪቱን እንዲመለከት እና እንዲፈትሽ መተባበራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህም ምንም ጉዳት የማያስከትል መሆኑ ተረጋግጧል።

ባለሥልጣናትም ከሲያትል በስተምሥራቅ በምትገኘው እና 150 ሺህ ሕዝብ በሚኖርባት ከተማ የኑክሌር አረር ይኖራል ብለው ፈጽሞ አስበው አያውቁም።

ግለሰቡ የኑክሌር ተሸካሚ ሮኬቱ ከይዞታ ሽያጭ ጋር የገዛው እና በሕይወት የሌለው ጎረቤታቸው ንብረት እንደሆነ ለፖሊስ አሳውቀዋል።

በመጨረሻም ፖሊስ የተገኘውን ሮኬት “የፍንዳታ ጉዳትን የማያደርስ ቅርስ” በማለት ለይቶታል።

“የኑክሌር አረር ተሸካሚው የማይፈነዳ እና ጉዳት የማያደርስ በመሆኑ የአገሪቱ ሠራዊትም እንዲመለስለት አልጠየቀም። ስለዚህ ባለበት ጊቢ ውስጥ ቆይቶ በሙዚየም ውስጥ ለዕይታ በሚቀርብበት ሁኔታ እንዲታደስ ፈቅዷል።”

ሲያትል ታይምስ ጋዜጣ እንደዘገበው ሮኬቱ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በአሜሪካ እና በካናዳ ጥቅም ላይ ውሏል።

ጋዜጣው ጨምሮም የመጀመሪያው እና ብቸኛው የዚህ የኑክሌር አስወንጫፊ ሮኬት የተተኮሰው በ1957 (እአአ) ነበር። የሮኬቱ ምርት ደግሞ በ1962 ተቋርጧል።