የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን
የምስሉ መግለጫ,የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን

3 የካቲት 2024

የቱርክ የፀጥታ ኃይሎች ለእስራኤል የስለላ ተቋም ሞሳድ መረጃ አሳልፈው ሲሰጡ ነበሩ ያሏቸውን ሰባት ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋላቸው ተነገረ።

ሰባቱ ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት የቱርክ የደኅንነት ኤጀንሲ የሆነው ኤምአይቲ በኢስታንቡል እና ኢዝሚር በተባሉት ከተሞች ውስጥ ድንገተኛ ዘመቻዎችን ካደረገ በኋላ ነው።

ቱርክ ከአንድ ወር በፊት ከሞሳድ ጋር ግንኙነት አላቸው ያለቻቸውን 34 ሰዎች በተመሳሳይ በቁጥጥር ስር አውላ ነበር።

የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን እስራኤል የሐማስ አባላትን ቱርክ ውስጥ ዒላማ ብታደርግ “ከፍተኛ መዘዝ” እንደሚጠብቃት አስጠንቅቀው ነበር።

ከመስከረም ማብቂያ ጀምሮ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ የገባውን ሐማስን በርካታ ምዕራባውያን እና አረብ አገራት አሸባሪ ቡድነት ቢፈርጁትም፣ ቱርክ ግን እዚህ ውሳኔ ውጥ የለችበትም።

ከዚህ በተጨማሪ ፍልስጤማውያን በቱርክ ጠንካራ ድጋፍ አላቸው። በኢስታንቡል እና ሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ውስጥ እስራኤል በጋዛ ከምታካሄደው በታደራዊ ዘመቻ አንጻር ለፍልስጤማውያን ድጋፍ ለመግለጽ ተደጋጋሚ ሰልፎች ይደረጋሉ።

ከሞሳድ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል በቁጥጥር ስር ስለዋሉት ሰዎች የቱርክ መንግሥት እስካሁን ይፋዊ መግለጫ ባያወጣም፤ የቱርክ መገናኛ ብዙኃን ግን ሞሳድ የግል መርማሪዎችን ተጠቅሞ የሐማስ ቡድን አባላትን እንቅስቃሴ እንዲከታተሉ እና ፎቶግራፍ እንዲያነሱ ስለማድረጉ የአገሪቱ የደኅንነት ተቋም ደርሶበታል ብለዋል።

ከአንድ ወር በፊት በቁጥጥር የዋሉት 34 ሰዎች “ፖለቲካ እና ወታደራዊ” ዓላማን ለማሳካት ለእስራኤል የደኅንነት ተቋም ስለላ በማድረግ ክስ እንደተመሠረተባቸው የቱርክ የፍሕት ሚኒስትር ይለማዝ ቱነከ ተናግረው ነበር።

ሞሳድ የስለላ ተግባሩን እንዲፈጽሙለት በቱርክ ነዋሪ የሆኑ ፍልስጤማውያን እና ሶሪያውያን ሳይቀጥር እንደማይቀር ይገመታል።

የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስተር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል።

ኤርዶዋን የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁን የጋዛ ወታደራዊ ዘመቻ “ዘር ማጥፋት” ብለው ከመግለጻቸውም በላይ ኔታኒያሁን ከናዚ ጀርመን መሪው ሂትለር ጋር አነጻጽረዋል።

እስራኤል በበኩሏ ከጋዛ በተጨማሪ በሊባኖስ፣ ኳታር እና ቱርክ የሚገኙ የሐማስ አባላትን ዒላማ እንደምታደርግ ስትዝት ቆይታለች።

መስረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ ወደ እስራኤል ድንበር በመሻገር የፈጸምውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት መጀመሩ ይታወሳል።

ሐማስ ድንበር ተሻግሮ በፈጸመው ጥቃት ከ1300 በላይ ሰዎችን ገድሎ ከ250 ያላነሱ ሰዎችን አግቶ መውሰዱ ተዘግቧል።

እስራኤል ለሐማስ ጥቃት እያካሄደቸው ባለው የአጸፋ ምላሽ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕጻናት የሆኑ ከ26 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቻውን እና በጋዛ ከፍተኛ የሆነ የመሠረተ ልማት ውድመት አጋጥሟል።