በጥቃቱ ከተሳተፉት ረጅም ርቀት ተጓዥ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች መካከል አንዱ የሆነው ቢ1
የምስሉ መግለጫ,በጥቃቱ ከተሳተፉት ረጅም ርቀት ተጓዥ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች መካከል አንዱ የሆነው ቢ1

3 የካቲት 2024, 08:56 EAT

አሜሪካ በሶሪያ እና ኢራቅ ውስጥ በሚገኙ ከኢራን ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ቡድኖችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን አርብ ሌሊት መፈጸሟ ተገለጸ።

ይህ ጥቃት ባለፈው እሁድ ዮርዳኖስ ውስጥ በሚገኝ የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች በፈጸሙት የድሮን ጥቃት ለተገደሉ ሦስት ወታደሮቿ ሞት አጸፋ ነው።

አሜሪካ ኢራቅ እና ሶሪያ ውስጥ በሚገኙት ዒላማዎች ላይ ጥቃት የፈጸመችው ከግዛቷ በተነሱ ረጅም ርቀት ተጓዥ በሆኑ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች መሆኑ ተገልጿል።

የአሜሪካ ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ እንዳስታወቀው ጥቃቱ የተፈጸመባቸው በሁለቱ አገራት ውስጥ የሚገኙ ዒላማዎች በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች የሚጠቀሙባቸው ናቸው።

አርብ ሌሊት ሦስት ኢራቅ ውስጥ አራት በሶሪያ በሚገኙ ስፍራዎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጓድ፣ ቁዱስ የተባለው ኃይል እና ተባባሪ የሆኑ ሌሎች ቡድኖች የሚገኙባቸው ስፍራዎች ናቸው።

በጥቃቱ ከአሜሪካ ምድር የተነሱ ረጅም ርቀት የሚጓዙ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች እና ሌሎችም የጦር አውሮፕላኖች ሲሳተፉ፣ ከ85 በላይ ዒላማዎች ከ125 በሚበልጡ ዒላማቸውን ለይተው በሚመቱ የጦር መሳሪያዎች ተመትተዋል።

በጥቃቱ ዒላማ የሆኑት የታጣቂ ቡድኖቹ የማዘዣ፣ የመረጃ እና የቁጥጥር ማዕከላት፣ ሮኬቶች እና ሚሳኤሎች የተጠመዱባቸው ስፍራዎች፣ የድሮኖች ማከማቻ ቦታዎች እና የአቅርቦት ማዕከላት መሆናቸውን የአሜሪካ ሠራዊት እስታውቋል።

አርብ ሌሊት በበርካታ ቦታዎች ላይ ለ30 ደቂቃዎች በተፈጸመው የመጀመሪያው የአጸፋ ጥቃት የደረሰውን ጉዳት መጠን ለማወቅ የአሜሪካ ሠራዊት ዛሬ ቅዳሜ ግምገማ እንደሚያደርግ ተነግሯል።

ከኢራን ጋር የቀጥታ ግጭት ውስጥ መግባት እንደማትፈልግ የገለጸችው አሜሪካ፣ ነገር ግን በምታካሂደው ጥቃት በኢራን የሚደገፉ ታጣቂ ቡድኖች በአሜሪካ ላይ ጥቃት የሚፈጽሙበትን አቅም ማዳከምን ዓላማ አድርጋለች።

አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን እንዳስታወቁት የአርም ሌሊቱ ጥቃት የመጨረሻ አለመሆኑን “ይህ [ጥቃት] በዚህ የሚያበቃ አይደለም” ብለዋል።

ጥቃቱን ተከትሎ የአንድ የኢራቅ ባለሥልጣን የአሜሪካ አውሮፕላኖች በግዛታቸው ውስጥ ጥቃት መፈጸማቸው የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚጥስ ነው በማለት ተቃውመውታል።