February 3, 2024 – Konjit Sitotaw
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች፤ በመጪው ማክሰኞ ምላሽ ሊሰጡ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች፤ በመጪው ሳምንት መጀመሪያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት ምላሽ እና ማብራሪያ እንደሚሰጡ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የፓርላማ አባላቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን አስገብተው ያጠናቀቁት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ነው።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስት የፓርላማ አባላት፤ ጥያቄዎችን እንዲያቀርቡ የተሰጣቸው ቀናት ብዛት ሶስት ብቻ እንደነበር ገልጸዋል። በዚህም መሰረት የፓርላማ አባላቱ ከባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ጥር 18 ጀምሮ እስከዚህ ሳምንት ሰኞ ጥር 20 ድረስ ጥያቄዎቻቸውን ማስገባታቸውን አስረድተዋል።
በ2008 ዓ.ም የወጣው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሰራር እና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ፤ “ማንኛውም የቃል መልስ የሚፈልግ ጥያቄ የሚያቀርብ አባል፤ ጥያቄውን ቢያንስ ከአስር ቀናት በፊት ለአፈ ጉባኤው በጽሁፍ ማሳወቅ አለበት” ሲል ይደነግጋል። የፓርላማው አፈ ጉባኤ፤ ከምክር ቤቱ አባላት የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች መርምረው የመቀበል ወይም ውድቅ የማድረግ ስልጣን በደንቡ ተሰጥቷቸዋል።
አፈ ጉባኤው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን የመለየት ስራ የሚያከናውኑት በተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ከሆኑት አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ጋር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላት የሚያቀርቡትን ምላሽ እና ማብራሪያን ጨምሮ፤ “የተወካዮች ምክር ቤት የሚወያይበትን ማንኛውም አጀንዳ የመቅረጽ” ኃላፊነት ያለበት ደግሞ “የምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ” ነው።