
4 የካቲት 2024, 08:05 EAT
በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7 ሐማስ፤ እስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ነው የመካከለኛው ምስራቅ ሰላም መናጋት የጀመረው።
በሐማስ ጥቃት 1300 ሰዎች ተገድለዋል።
ለዚህ ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ወታደራዊ ዘመቻ የጀመረችው እስራኤል ጋዛን እንዳይሆን አድርጋታለች።
በጋዛ በደረሰው ጥቃት ደግሞ እስካሁን ከ26 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያስ ተገድለዋል።
በዚህ ምክንያት ሁሌም ግጭት የማያጣው ቀጣና ወደላቀ ውጥረት አምርቷል።
በእስራኤልና ሐማስ መካከል የተነሳው ግጭት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ይስፋፋ ይሆን?
የጋዛ ጦርነት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ይስፋፋ ይሆን ብለን መጠየቅ ማቆም ሳይኖርብን አይቀርም። ምክንያቱ ግጭቱ ተስፋፍቷልና።
የሁቲ አማፂያን እስራኤል ጋዛ ላይ እያደረሰች ላለው ውድመት መልስ ለመስጠት ቃል ለመግባት ጊዜ አልወሰደባቸውም።
ቀጥሎ በአራን የሚደገፉ መቀመጫቸውን ኢራቅና ሶሪያ ያደረጉ ታጣቂዎች በቀጣናው ባሉ የዩኤስ ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት ማድረስ ያዙ።
እስራኤል፤ ሐማስን ሳላጠፋ አልቀመጥም በማለት ጋዛ ላይ ከባድ ድብደባ እያደረሰች ትገኛለች።
- ሊባኖስን የሚያንቀጠቅጠው፣ የእስራኤል ስጋት ሒዝቦላህ፡ መሪው ሐሰን ናስራላህ ማን ናቸው?4 ህዳር 2023
- በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማፂያን ለምን ከአሜሪካ እና አጋሮቿ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባትን መረጡ?28 ጥር 2024
- የተባበሩት መንግሥታት በጋዛ እና ዩክሬን ጉዳይ የሚወቀሰው ለምን ይሆን? ምንስ ማድረግ ይችላል?25 ጥር 2024
ሊባኖስ
የእስራኤል-ጋዛ ግጭት አየበረታ ሲመጣ ጦርነቱ ወደ ጎረቤት አገር ሊባኖስ ሊስፋፍ ይችላል የሚል ትልቅ ፍራቻን አስከትሎ ነበር።
ሔዝቦላህ የሺዓ እስልምና ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና ማኅበረሰባዊ ድርጅት ነው። መሠረቱን በሊባኖስ ቢያደርግም ዋነኛ ገፋፊው ኢራን ናት።
ምንም እንኳ ቡድኑ በምዕራባውያን እና በተለያዩ አረብ አገራት ሽብርተኛ ተብሎ ቢፈረጅም፣ በሊባኖስ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ተፅዕኖ አለው።
የጋዛ ጦርነት በተጀመረ ማግስት ሔዝቦላህ እና የእስራኤል ጦር ድንበር ላይ ጦር ተማዘዋል። ነገር ግን ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም፤ የመጨረሻቸውም አይመስልም።
የተባበሩት መንግሥታት ጥር 2024 (እአአ) ባወጣው መረጃ መሠረት በሊባኖስ እና እስራኤል ድንበር አቅራቢያ በተነሳው ግጭት ምክንያት ከ82 ሺህ በላይ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተፈናቅለዋል።
ከ20 በላይ ሰዎች ደግሞ ሊባኖስ ውስጥ መገደላቸው ተዘግቧል።
በደቡብ ሊባኖስ እና በሰሜን እስራኤል አካባቢ ያለው ግጭት ጉልበት ማሳያ ሆኖ ይቀራል ወይስ ይቀጥላል የሚለው ግልጽ አይደለም።
እርግጥ ነው እስራኤልም ሆነች ሔዝቦላህ ጭልጥ ወዳለ ጦርነት መግባት እንደማይፈልጉ ይናገራሉ። ነገር ግን ወደ ጦርነት ከመግባት የሚያግዳቸው ነገር ያለ አይመስልም።
ሁለቱም ወገኖች ወደለየለት ጦርነት የሚገቡ ከሆነ አንዱ አንደኛውን የማጥፋት አቅም እንዳለው ሲዝቱ ይሰማሉ።

ዌስት ባንክ
የጋዛው ጦርነት ከጀመረ በኋላ በእስራኤል ቁጥጥር ሥር ባለችው ዌስት ባንክ ያሉ ፍልስጤማውያን ከሰፋሪ እስራኤላዊያን የሚደርስባቸው ጥቃት ጨምሯል።
የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ሰፋሪዎቹ ስምንት ፍልስጤማውያንን የገደሉ ሲሆን፣ 80 ገደማ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
357 ፍልስጤማዊያን ደግሞ በእስራኤል ጦር ተገድለዋል።
ባለፈው ታኅሣሥ አንድ አክቲቪስት ለቢቢሲ እንደተናገረው ጥቅምት ወር መጀመሪያ አካባቢ ከቤቱ ተወስዶ በእስራኤል ኃይሎች ለ10 ሰዓታት ያክል ድብድባ እንደደረሰበት ይናገራል።
አክቲቪስቱ እንደሚለው ድብደባውን ከፈፀሙበት መካከል ጎረቤቱ የሆኑ ሰፋሪዎች ይገኙበታል።
አንድ የእስራኤል ወታደር በዚህ ድብደባ ምክንያት የ10 ቀናት እሥር ተፈርዶበታል።
ዌስት ባንክ ያሉ አብዛኞቹ ፍልስጤማውያን ጥቃት እንዳይደርስባቸው በመስጋት ከቤት አይወጡም።
ሁቲዎች እና ቀይ ባሕር
በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማፂያን አብዛኛውን የየመን ክፍል ይቆጣጠራሉ።
ባለፈው መስከረም ወር ማብቂያ ላይ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ጦርነት ከተጀመረ በኋላ፣ የሁቲ አማፂያን በቀይ ባሕር በኩል የሚያልፉ የእስራኤልም ሆኑ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸውን አገራትን መርከቦች ማጥቃት ጀምረዋል።
ይህን ተከትሎ አሜሪካ እና እና አጋሮቿ በኢራን የሚደገፉ የሁቲ አማፂያን ላይ የአጸፋ እርምጃ እየወሰዱ ነው።
ነገር ግን ይህ እርምጃ የሁቲ አማፂን የእስራኤል፣ የዩናይትድ ኪንግደም እና የዩናይትድ ስቴትስ የጦር መርከቦችን ከማጥቃት አላገዳቸውም።
ታኅሣሥ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ሄሊኮፕተሮች ሦስት የሁቲ አማፂያንን የያዙ ጀልባዎችን አስጥመዋል።
በተመሳሳይ ወር የሁቲ አማፂያን አንድ የኖርዌይ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ላይ የሚሳዔል ጥቃት ሰንዝረው በእሳት እንድርያያዝ አድርገዋል።
በአውሮፓውያኑ ጥር 27 ሦስት አሜሪካዊያን ዮርዳኖስ ውስጥ ከሁቲ አማፂያን በተሰነዘረ የድሮን ጥቃት ተገደሉ።
ኢራን እና ሐማስ ጦርነቱ በመካከለኛው ምሥራቅ እንዲስፋፋ ይፈልጋሉ?
በቅርቡ ዩኬ እና አሜሪካ በሁቲ አማፂያን ላይ እየሰነዘሩ ያለው ጥቃት ጦርነቱ ለመስፋፋቱ ማሳያ ነው።
ነገር ግን ኢራን እና አጋሮቿ ከጦርነቱ በላይ የምዕራቡ ዓለም ለእስራኤል የሚሳየውን ድጋፍ መገዳደር ነው የሚፈልጉት።

ኢራን
ኢራን መስከረም ማብቂያ ላይ በሐማስ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር የሚያገናኘኝ ነገር የለን ስትል ታስተባብላለች።
በጥር ወር መጀመሪያ ላይ በደቡባዊ ኢራን ከርማን በተሰኘ አካባቢ ሰዎች በተሰበሰቡበት ሥፍራ የፈነዳ ቦምብ ለ84 ሰዎች ሕልፈት ምክንያት ሆኗል።
ሰዎቹ የተሰበሰቡት የኢራን የስለላ አባት የሚባለውን ቃሲም ሶሌይማኒን ሞት አንደኛ ዓመት ለመዘከር ነበር።
ቃሲም፤ ኢራቅ መዲና ባግዳድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አቅራቢያ በአሜሪካ በተፈጸመበት ጥቃት ነው የተገደለው።
መጀመሪያ ኢስላሚክ ስቴት የቦምብ ጥቃቱን ያደረስኩት እኔ ነኝ ሲል ኃላፊነት ቢወስድም፣ ኢራን ግን ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ራስ አልወርድም ብላ ነበር።
የቢቢሲው የመካከለኛው ምሥራቅ የደኅንነት ዘጋቢ ፍራንክ ጋርድነር እስራኤል ይህንን የቦምብ ጥቃት ለማድረስ የሚያነሳሳ ምንም ምክንያት የላትም ይላል። ነገር ግን ኢራን ጥቃቱን ማን እንደፈጸመው ለማጣራት ደፋ ቀና እያለች ነው።
ኢራቅ
አሜሪካ፤ ኢራቅ የሚገኙ በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መውሰድ የጀመረችው በወርሃ ጥር ነው።
አሜሪካ እንደምትለው ይህ ጥቃት በአራቅ እና በሶሪያ እንዲሁም በአሜሪካ እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ኃይሎች ላይ ለተወሰደው እርምጃ ምላሽ ነው።
ኢራቅ የሚገኙ በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች በቀጣናው የተፈጠረው ውጥረት መነሻ በጋዛ የተቀሰቀሰው እና ወራትን ያስቆጠረው ጦርነት ነው ይላሉ።
ኢራን ሐማስን ትደግፋለች፤ ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ እስራኤልን።
ከጦርነቱ በኋላ በኢራቅ እና ሶሪያ ያሉ ወታደራዊ መቀመጫዎች ከ150 ጊዜ በላይ ጥቃት ደርሶባቸዋል።
አብዛኛውን ጊዜ ታጣቂዎቹ ጥቃት የሚሰነዝሩት በድሮኖች እና በሮኬት በመታገዝ ነው።
