
4 የካቲት 2024, 09:18 EAT
የፓኪስታን ፍድር ቤት የቀድሞው መሪ ኢምራን ካን እና ባለቤታቸው ትዳራቸው ሕጋዊ አልነበረም ሲል የሰባት ዓመት እሥር ፈርዶባቸዋል።
ችሎቱ እንዳለው በአውሮፓውያኑ 2018 ካን ከቡሽራ ቢቢ ጋር የመሠረቱት ጋብቻ እስላማዊ እና ሕጋዊ ያልሆነ ነው።
ኢምራን ካን ባለፈው ሳምንት ነው ከባለቤታቸው ጋር በሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ናቸው ተብለው እሥር የተፈረደባቸው።
ነገር ግን የ71 ዓመቱ የቀድሞው የሀገሪቱ መሪ የቀረቡባቸው የተለያዩ ክሶች ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ናቸው ሲሉ ይከራከራሉ።
የቀድሞው የፓኪስታን የክሪኬት ብሔራዊ ቡድን አምበል የፖለቲካውን ዓለም ከተቀላቀሉ በኋላ በ2022 ከሥልጣን እስኪወገዱ ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
ካን በሙስና ወንጀል የተፈረደባቸውን ፍርድ እያገለገሉ ባለቡት ማረሚያ ቤት ችሎት ተቋቁሞ ነው ትዳራቸው ሕጋዊ አይደለም የሚል ፍርድ የተከናነቡት።
ክሱን ያቀረቡት የቢቢ የቀድሞ ባል ሲሆኑ ከካን ጋር ያላቸው ትዳር ሕጋዊ አይደለም ሲሉ ከሰዋል።
በሙስሊም ቤተሰብ ሕግ መሠረት አንዲት ሴት ባሏ ከሞተ አሊያም ፍቺ ከፈፀመች በኋላ ሌላ ትዳር ለመመሥረት የተወሰነ ጊዜ መጠበቅ አለባት።
ችሎቱ እንዳለው ቢቢ የቀድሞው ትዳሯ ከፈረሰ በኋላ ብዙም ሳትቆይ ነው እንደገና ያገባችው።
- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምን ውጤት አመጣ? ወደፊትስ በምን ሊቋጭ ይችላል?3 የካቲት 2024
- ከስደተኛነት ተነስቶ በተለያዩ አገራት የግንባታ ኩባንያ ያቋቋመው ኤርትራዊ4 የካቲት 2024
- የናሚቢያው ፕሬዝደንት በ82 ዓመታቸው ከዚህ ዓመት በሞት ተለዩ4 የካቲት 2024
ሰባት ዓመት የተፈረደባቸው ካን እና ቢቢ ግማሽ ሚሊዮን ሩጲ አሊያም 1800 ዶላር እንዲከፍሉ ግድ ይላቸዋል።
ጥንዶቹ ጋብቻ የፈፀሙት ኢምራን ካን በ2018 ፕሬዝደንት ሆነው ከመመረጣቸው ከጥቂት ወራት በፊት ነበር።
መንፈሳዊ ፈዋሽ የሚባሉት እና ዕድሜያቸው በ40ዎቹ የሚገመተው ቢቢ የካን ሶስተኛ ሚስት ሲሆኑ ሁሌም አደባባይ ሲታዩ ፊታቸውን ሸፍነው ነው።
ካን በክሪኬት ተጫዋችነት ዘመናቸው ከአንዲት ሴት መርጋት አይሆንላቸው ተብለው ይታሙ ነበር። ነገር ግን 1995 ከታዋቂዋ ብሪታኒያዊት ጄሚማ ጎልድስሚዝ ጋር ትዳር ፈፀሙ።
ካን ዘጠኝ ዓመታት ከቆየው የመጀመሪያ ትዳራቸው ሁለት ወንድ ልጆች አፍርተዋል።
ሁለተኛው ትዳራቸው ደግሞ ከጋዜጠኛዋና ከቀድሞው የቢቢሲ የአየር ትንበያ አቅራቢ ሬሃም ካን ጋር ነበር። ነገር ግን ይህ ትዳር አንድ ዓመት አልቆየም።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ካለፈው ነሐሤ ጀምሮ እሥር ላይ ነው የሚገኙት።
ቅዳሜ ዕለት ሕጋዊ ያልሆነ ትዳር በሚል ክስ የተፈረደባቸው ካን በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ጥፋተኛ ሆነው ሲገኙ ይህ ሶስተኛው ነው።
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሚስጢራዊ መረጃ በማውጣት፣ ረቡዕ ዕለት ደግሞ ከባለቤታቸው ጋር ሆነው የሀገር ንብረት በመሸጥና ስጦታ በመቀበል፤ ቅዳሜ ሕጋዊ ያልሆነ ትዳር በመመሥረት ነው የተፈረደባቸው።
ከባለቤታቸው ጋር ሆነው ከሳዑዲው አልጋ ወራሽ ስጦታ ተቀብለዋል በሚለው ክስ ሁለቱም 14 ዓመት የተፈረደባቸው ሲሆን ቢቢ ይህን ፍርድ በቁም እሥር ማሳለፍ ይችላሉ።
የካን ፓርቲ ፒቲአይ ፍርዱ ፍፁም ሐሰትና ፖለቲካዊ ነው ብሎ ያምናል።
በርካቶች በሚቀጥለው ሳምንት የሚካሄደው ምርጫ እንዴት ተዓማኒ ይሆናል የሚል ጥያቄ የሚያነሱ ሲሆን በርካታ የፒቲአይ ፓርቲ አባላት እሥር ቤት አሊያም ስደት ላይ ነው የሚገኙት።
ተንታኞች እንደሚሉት የፓኪስታንን ፖለቲካዊ ምሕዳር የሚሾፍረው የሀገሪቱ ወታደራዊ መዋቅር ነው።