የናሚቢያው ፕሬዝደንት ሃጌ ግይንጎብ

4 የካቲት 2024, 08:31 EAT

በሀገራቸው መዲና ዊንድሆክ ካለ ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ የቆዩት የናሚቢያው ፕሬዝደንት ሃጌ ግይንጎብ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ምክትል ፕሬዝደንት ናንጎሎ ምቡምባ እንዳስታወቁት ሃጌ የሞቱት ቅዳሜ ለሊት ለእሑድ አጥቢያ ነው።

“ሕይወታቸው ስታልፍ ባለቤታቸው ማዳም ሞኒካ ጌይንጎስ እና ልጆቻቸው ነበሩ” ሲሉ ምክትል ፕሬዝደንቱ ገልጠዋል።

የ82 ዓመቱ ፕሬዝደንት የካንሰር ተጠቂ መሆናቸውን ይፋ ካደረጉ ቆይተዋል።

ነገር ግን ሕክምና እየተከታተሉ እንደሆነ ባለፈው ወር ነበር ለሕዝባቸው ያደረጉት።

የፕሬዝደንቱ ቢሮ ሃጌ ወደ አሜሪካ ተጉዘው ሕክምና ከተከታተሉ በኋላ በአውሮፓውያኑ የካቲት 2 ይመለሳሉ የሚል መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።

ፕሬዝደንት ሃጌ ጌይንጎብ በአውሮፓውያኑ 2015 ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ሥልጣን የያዙት።

በድጋሚ ምርጫ አሸንፈው ሀገራቸውን ለሁለተኛ እና ለመጨረሻ ጊዜ እየመሩ ነበር።

ባለፈው ዓመት የቀዶ ጥገና ሕክምና አድርገው ከሆስፒታል ወጥተዋል።

ፕሬዝደንቱ በ2014 የፕሮስቴት ካንሰር እንደነበራቸውና ከበሽታው ግን ማገገማቸውን ተናግረው እንደነበር ይታወሳል።

ናሚቢያ በሚቀጥለው ኅዳር ፕሬዝደንታዊ እና የሕዝብ እንደራሴዎች ምርጫ ታካሂዳለች።

ገዢው ስዋፖ ፓርቲ ናሚቢያ በ1990 ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣች ጀምሮ ሀገሪቱን ሲያስተዳድር ቆይቷል።

ፓርቲው ናንዲ-ንዳይትዋህ የተሰኙትን ፖለቲከኛ ዕጩ ፕሬዝደንት አድርጎ ለምርጫው አቅርቧል።

በአሁኑ ወቅት ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው እያገለገሉ ያሉት ናንዲ ምርጫውን ካሸነፉ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝደንት ይሆናሉ።

ከፕሬዝደንቱ ሞት በኋላ ምክንትል ፕሬዝደንት ናንጎሎ በጊዜያዊነት ሀገሪቱን እያስተዳደሩ ይገኛሉ።

ደቡብ አፍሪካዊቷ ናሚቢያ አልማዝን የመሳሰሉ ማዕድኖች መገኛ ስትሆን በ1990 ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ በአንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት ይዛ የቆየች ሀገር ናት።