የምህንድስና ባለሙያው እና የከንዓን ኩባንያ ባለቤት በረከት ጎይቶም
የምስሉ መግለጫ,በረከት ጎይቶም

4 የካቲት 2024, 08:04 EAT

ኤርትራ በጦርነት በምትታመስባቸው ዓመታት እናቱ ሕይታቸውን ለመታደግ ወደ ጎረቤት አገር ይዘውት ተሰደዱ።

ኤርትራ ነጻ አገር እስክትሆን ድረስ የፊደል ዘር የቆጠረው በሰው አገር፣ በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ነው።

ወደ ኤርትራ ከተመለሱ በኋላም ቢሆን፣ ሕይወት ከስደት የሚያስቀረው አልሆነም።

ዛሬ የራሱን ድርጅት መሥርቶ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን ቀጥሮ ያሠራል።

የምህንድስና ባለሙያ የሆነው በረከት ጎይቶም እ.ኤ.አ. በ2007 ደቡብ ሱዳን ውስጥ ከጓደኛው ጋር በመሆን ‘ከነዓን’ የተሰኘውን ድርጅት የመሠረቱ።

በረከት ጎይቶም ስለ ልጅነቱ ሲናገር በ1970ዎቹ ኤርትራ ውስጥ መወለዱን ገልጾ፣ በወቅቱ አባቱ ወደ ትግል በመሄዱ እናቱ፣ እንደ አባትም እንደ እናትም ሆነው እንዳሳደጉት ያስረዳል።

“በ1980ዎቹ መጀመሪያ እናቴ፣ እኔን እና ሁለቱ ታላላቅ ወንድሞቼን ይዛ ወደ ሱዳን ሄደች” ሲል ኢንጂነር በረከት የስደት ሕይወት ጅምሬያቸውን ያስታውሳል።

“. . . ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ ሱዳን ከሰላ ውስጥ በኤርትራ ህዝባዊ የነጻነት ግንባር ይተዳደር በነበረው ትምህርት ቤት ተማርኩ። ከሰባተኛ ክፍል ጀምሮ ደግሞ በዩኤንኤችሲአር ወደሚደገፈው የስደተኞች ትምህርት ቤት ገባሁ” ይላል።

በ1995 ደግሞ በረከትም ከቤተሰቡ ጋር ወደ ኤርትራ ተመልሶ የሁለተኛ ደራጃ ትምህርቱን እዚያ በመቀጠል በ1997 (እአአ) በአሥመራ ዩኒቨርሲቲ ምህንድስና አጥንቶ በ2003 ተመረቀ።

ከዚያም እስከ 2006 ድረስ ብሔራዊ አገልግሎት ሲሰጥ ከቆየ በኋላ፣ ሰፊ ግንባታ እየተካሄደበት ወደ ነበረቸው ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ – ዱባይ በስደት አቀና።

የከነዓን ጅማሬ እና እድገት

የምህንድስና ባለሙያው በረከት ከአሥመራ ዩኒቨርሲቲ ከመመረቁ በፊት በብሔራዊ አገልግሎት ውስጥ በነበረበት ወቅት የአንድ ዓመት የሥራ ልምድ አግኝቷል።

“ዱባይ ስሄድ በአገሪቱ ውስጥ ብዙ የግንባታ እንቅስቃሴ ስለነበረ ቶሎ ሥራ ጀመርኩ። በዚህም መሠረት የሙያ አጋሬ ከሆነው ጓደኛዬ ጋር በ2007 ደቡብ ሱዳን ውስጥ ከነዓን ኮንስትራክሽንን አቋቋምን። ድርጅቱ አሁን ወደ ብዙ አገሮች ተስፋፍቷል” ይላል።

ከነዓን በኬንያ፣ በኡጋንዳ እና በሌሎች የአፍሪካ አገራት ቅርንጫፎች ያሉት ድርጅት ነው።

ኢንጂነር በረከት በ2006 ዱባይ ሲሄድ የዱባይ ዋና መለያ የሆነው ‘ቡሪጅ አል ኻሊፋ’ እና የዓለማችን ምርጥ አስር ታላላቅ ‘ዱባይ ሞል’ በግንባታ ላይ እንደነበሩና እሱም በሙያው ተቀጥሮ እንደሠራ ያስታውሳል።

በረከት እና ጓደኛው የግንባታ ተቋማቸውን ዱባይ ውስጥ ለማቋቋም ፍላጎት እና አቅም ቢኖራቸውም፣ ለጀማሪ ውድድሩ ከባድ ስለሚሆን ‘ቀለል ያለ ውድድር’ ያለባትን ደቡብ ሱዳንን ምርጫቸው ማድረጋቸውን አልሸሸገም።

“ዱባይ እያለን ወደ ምዕራብ አገራት የመሄድ ዕድሎች ነበሩ። እኛ ግን ወደ ደቡብ ሱዳን ሄድን፤ ይህ እንደ ጥሩ ውሳኔ እና ጥሩ አጋጣሚ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል” ሲል እርምጃው በሕይወቱ ካደረጋቸው ውሳኔዎች መካከል ትልቁ መሆኑን ይናገራል።

እነ በረከት ከደቡብ ሱዳን በመቀጠል፣ በ2010 ኡጋንዳ ውስጥ የቤቶች ግንባታ ከጀመሩ በኋላ ከሦስት ዓመታት በኋላ በኬንያ፣ በኢትዮጵያ፣ በአንጎላ፣ በጋና እና በሌሎች አገራት ቅርንጫፎችን እየከፈቱ ሥራቸውን ማስፋፋት ቀጠሉ።

ከነዓን የቤት ግንባታ፣ የፕላስቲክ ፋብሪካ፣ የወተት ፋብሪካ፣ የመንገድ ግንባታ፣ የጭማቂ እና ሌሎች የንግድ ሥራዎች ላይ ሁሉ መሰማራቱን ኢንጅነር በረከት ይገልጻል።

የድርጅታቸውን ስኬት ሲያስረዳም፣ ኬንያ ውስጥ ብቻ እስካሁን ድረስ ከ1000 በላይ ቤቶችን ገንብተዋል።

“ደቡብ ሱዳንን በመሳሰሉ አገራትም ብዙ ቤቶችን ገንብተናል። በመንገድ ግንባታ ላይም እየተሳተፍን ነው። በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ነው። በኡጋንዳም ልክ እንደ ኬንያ በሰፊው እየገነባን ነው” ይላል በረከት።

በሌሎች የአፍሪካ አገራት ውስጥ እየሠሩ ያሉትን ሥራዎች በአገሩ ኤርትራ የመሥራት ዕድል ቢያገኝ በእጅጉ ደስተኛ መሆኑን የሚገልጸው በረከት ይህም የወደፊት ምኞቱ ነው።

“እዚህ እየሠራን ያለነው ዕድሎች ስላሉ ነው፣ ዕድሎቹ በኤርትራ ውስጥ ሲከፈቱ ደግሞ እየሠራን ካለነው ጋር የሚመሳሰል እና ከዚያም በላይ እንሠራለን ብለን እናስባለን።”

ከነዓን ዴቬሎፐርስ በኬንያ ከሚያስገነባቸው ግዙፍ ሕጻዎች መካከል አንዱ
የምስሉ መግለጫ,ከነዓን ዴቬሎፐርስ በኬንያ ከሚያስገነባቸው ግዙፍ ሕጻዎች መካከል አንዱ

የከነዓን ኩባንያ በምን ያህል ካፒታል ጀመረ?

ከነዓን በአሁኑ ጊዜ ኬንያ ውስጥ እስከ 1,000 የሚደርሱ ቋሚ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ ሌሎች ከአንድ ሺህ በላይ ደግሞ በየቀኑ በግንባታ ቦታ ላይ ይሠራሉ። በሌሎች አገራት ውስጥም ከዚህ የበለጠ ሠራተኞች ቁጥር እንዳላቸው ይናገራል።

ኢንጂነር በረከት ይህን የመሰለ ድርጅት ለመመሥረት “የመጀመሪያው ነገር ፍላጎት እና ውሳኔ ነው። ቀጥሎ ትክክለኛውን ቦታ መምረጥ ይመጣል። ከዚያም በተመሳሳይ ሁኔታ ኢንቨስትመንቱ በምን ያህል ጊዜ ዋጋውን መመለስ እንደሚችል ማጥናት ያስፈልጋል” ይላል።

በረከት እና ጓደኛው ይህንን ኩባንያ ሥራ ሲያስጀምሩ ዋነኛው ሀብታቸው የነበረው ለሥራው የሚያስፈልገው ትምህርት እና ስኬታማ ለመሆን ጽኑ ፍላጎታቸው መሆኑን ይጠቅሳል።

ስኬታማ ለመሆን ደግሞ ሙሉ ትኩረትን ሰጥቶ መሥራት አስፈላጊ እና ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ይጠቁማል።

ኢንጅነር በረከት፣ ከሥራው ጎን ለጎን በኬንያ እና በሌሎች አገራት ታዋቂ ከሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ከሆነው ስትራትሞር በማስተርስ ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ተመርቋል።

ከዚህ በመነሳትም ማንኛውም ሰው የያዘውን ሙያ በትምህርት እንዲያጠናክረው ይመክራል።

ኢንጂነር በረከት ጎይቶም፣ የከነዓን ዴቬሎፐርስ መስራች እና ባለቤት
የምስሉ መግለጫ,ኢንጂነር በረከት ጎይቶም

ሽርክና እና ሸሪክን መምረጥ

ኢንጂነር በረከት የቤቶች ግንባታ ላይ በመጀመሪያ ሲሰማራ አብሮት ለመሥራት የወሰነው በቅርበት ከሚያውቀው ጓደኛው ኢንጂነር በእምነት ጋር በመሆኑ ለእድገቱ አስተዋጽኦ ማድረጉን ይናገራል።

“ትክክለኛውን ሸሪክ ማግኘት በስኬት እና በውድቀት መካከል ያለው ልዩነት ነው እላለሁ። ከሚመስልህ ሰው ጋር ሲሠራ ስኬታማ የመሆን ዕድል ከፍ ያለ ነው። ነገር ግን በምርጫህ ስህተት ከፈጸምክ መዘዙ መውደቅ ሊሆን ይችላል” በማለት ከሥራ ሸሪኩ ጋር እስካሁን አብረው የመቆየታቸውን ምስጢር ያብራራል።

የንግድ ሸሪክን መምረጥ በተለይ ደግሞ ለጀማሪ ባለሙያዎች በሚገባ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን የሚገልጸው በረከት ተመሳሳይ ፍላጎት እና ዓላማ ያላቸው ከሆኑ እጅግ ጠቃሚ ነው ይላል።

ሌላው ደግሞ “ልዩነቶችን አምኖ በመቀበል መሥራት ነው። አንድ መሆን አይቻልም፤ ሽርክና ውስጥ የሚያጋጥመው ችግር ሌላውን እንደራስ እንዲያስብ ከመጠበቅ የሚመነጭ ነው ብዬ አስባለሁ።”

ኢንጂነር በረከት በብቸኝነት ከመሥራት ይልቅ ከሌሎች ጋር አብሮ በሽርክና መሥራት ያለውን ጥቅም ሲያስረዳ “አንድ ሽርክና ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ያደርጋል፤ ሌላው ደግሞ ወደ ሌላ ደረጃ ያደርሳል” በማለት ነው።

ከነዓን ዴቬሎፐርስ ከገነባቸው የመኖርያ ቤቶች መካከል የተወሰኑት
የምስሉ መግለጫ,ከነዓን ዴቬሎፐርስ ከገነባቸው የመኖርያ ቤቶች መካከል የተወሰኑት

‘ከአገር ከወጣን ጠንክረን እንሥራ’

በረከት ሱዳን ውስጥ ስደተኛ ነበር፣ ኤርትራ ውስጥ በብሔራዊ አገልግሎት ውስጥ ተሳትፏል ከዚያም ወደ ስደት ተመለሰ። ይህ የበርካታ ኤርትራውያን ታሪክ መሆኑን ይናገራል።

በዚህ ሁሉ ውስጥ “የጥገኝነት ወይም የተጎጂነት ስሜትን ወደጎን በማድረግ፣ በእጅህ ያለውን ነገር ተጠቅመህ እንዴት ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንደምትደርስ ማሰብ እና መጣል አስፈላጊ ነው” ሲል ይመክራል።

ለዚህም እንዴት የተሻለ ኑሮ መፍጠር እና እንዴት መማር እንደሚቻል ማሰብ አስፈላጊ እንደሆነ በመጥቀስ፣ ደቡብ ሱዳን ውስጥ ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ኤርትራውያን አስደናቂ ሥራዎችን ሲያከናውኑ ማየቱን በምሳሌነት ያነሳል።

“ስለዚህ ፍላጎቱ ካለ ብዙ መሥራት ይቻላል። ከአገራችን መውጣታችን ካልቀረ ጠንክረን በመሥራት የያዝነውን ነገር እናሳድግ።”

ጨምሮም በስደት በተለያዩ መስኮች የተሳካላቸው ኤርትራውያን ምሳሌ በመሆን፣ ልምዳቸውን ለወጣቶቹ በማካፈል እነሱም ለስኬት እንዲበቁ ማገዝ እና ማበረታታት አስፈላጊ መሆኑን ያነሳል።