
3 የካቲት 2024
ካለፈው ዓመት አጋማሽ ወዲህ በአማራ ክልል የነበረው መረጋጋት እየተበላሸ ከሚያዝያ ወር በኋላ በነበረው ጊዜ ብሶበት ወደ ለየለት ግጭት ተገብቶ ክልሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ከገባ ስድስት ወራት ሆኖታል።
ጥቂት በማይባሉ ስፍራዎች የግብርና ሥራ ተስተጓጉሏል፣ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በመደናቀፉ የሚፈለገው ምርት እና አገልግሎት በቀላሉ አይገኝም። መሠረታዊዎቹ የመድኃኒት እና የሸቀጦች ዋጋ አልቀመስ ብሏል። የመንግሥት አገልግሎት እና ትምህርት ተስተጓጉሏል ወይም ስጋት ውስጥ ናቸው።
በበርካታ ቦታዎች በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በሚካሄዱ ግጭቶች ምክንያት ነዋሪዎች እና ንብረታቸው ሰለባ እየሆኑ መሆናቸውን ባለፉት ወራት ከተለያዩ ወገኖች የወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
‘የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ’ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ
በወርሃ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ነበር የአማራ ክልል የሰላም አየር መደፍረስ ጀመረው። ከሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ማግስት በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ ጉልህ አለመረጋጋት ተፈጥሮ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ የፋኖ ታጣቂዎች ወደ ከተሞች ዘልቀው በመግባት የተወሰኑ አካባቢዎችን ሲቆጣጠሩ እና የክልሉ የፀጥታ ኃይል ክስተቱን መቆጣጠር ሳይችል በቀረበት ጊዜ፣ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ጥያቄ አቀረበ።
የሚኒስትሮች ምክር ቤትም ሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ በክልሉ እንዲሁም እንዳስፈላጊነቱ በመላው አገሪቱ ተግባራዊ የሚደረግ ለስድስት ወራት የሚቆይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገ ሲሆን፣ ይህንን ውሳኔም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አጽድቆታል።
ይህንንም ተከትሎ የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት እና የፀጥታ ኃይሎች ወደ ክልሉ ተሰማርተው በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ስር ገብተው የነበሩ አካባቢዎችን በቀናት ውስጥ መልሰው መያዛቸው ቢገለጽም፣ ግጭቱ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ውስጥ ባስ ጋብ እያለ አሁን ድረስ ቀጥሏል።
- በአማራ ክልል መርዓዊ ከተማ ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የዐይን እማኞች ተናገሩ2 የካቲት 2024
- አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት ተራዘመ2 የካቲት 2024
- ኢሰመኮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም እንደሚያሳስበው ገለጸ2 የካቲት 2024
ባለፉት ወራት ምን ተከሰተ?
ሐምሌ 29/2015 ዓ.ም. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚመራ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ተቋቁሞ፣ ክልሉን በአራት ኮማንድ ፖስቶች በመክፈል አካባቢዎችን የማረጋጋት ተግባራትን ማከናወን የጀመረው “ተጠርጣሪዎችን” በቁጥጥር ስር በማዋል ነበር።
በዚህም የፌደራል እና የክልል የምክር ቤት አባላት፣ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና ሌሎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል። እስካሁን ባለው ሂደት ከእስር የተለቀቁ ያሉ ሲሆን፣ ባለፉት ወራት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ክስ ሳይመሠረትባቸው በእስር ላይ የሚገኙ በርካቶች ናቸው።
መንግሥት ወሰድኳቸው ባላቸው እርምጃዎች ክልሉን ወደ ሰላም እየመለስኩ ነው ያለ ሲሆን፣ “ተራ ዘራፊ” የሚላቸው የፋኖ ኃይሎች “ተበትነዋል” እንዲሁ ቡድኑ ወደ “ተራ ሽፍታነት” ወርዷል ካለ ወራት ተቆጥረዋል።
ይሁን እንጂ መንግሥት “ሕግ ማስከበር” የሚለውን እርምጃ “ወረራ” የሚሉት የፋኖ ታጣቂዎች ይህንን አይቀበሉትም፤ እንዲያውም በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ያለው መንግሥታዊ መዋቅር መንኮታኮቱን በርካታ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸውን ይናገራሉ።
ባለፉት ወራት ጋብ እያለ እና እየተባባሰ በሚካሄደው የትጥቅ ግጭት ምክንያት አለመረጋጋት የክልሉ አንድ መለያ ሆኗል። መደበኛ እንቅስቃሴዎችም እንደ ከዚህ ቀደሙ እንዳልሆኑ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ይናገራሉ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መደንገጉን ተከትሎ የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ከተሰማራ በኋላ መንግሥት በክልሉ “አንጻራዊ ሰላም” አምጥቻለሁ ቢልም፣ የክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ግን ከዚህ እንደሚለይ ፖለቲከኞች ይናገራሉ።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባል የሆኑት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ አበባው ደሳለው በመንግሥት መግለጫዎች እና በነባራዊው የክልሉ ሁኔታ መካከል ሰፊ ልዩነት አለ ይላሉ።
አቶ አበባው “ዋና ዋና ከተሞችን መንግሥት የያዛቸው ይምሰል እንጂ፤ ተረጋግቶ መምራት አልቻለም” ሲሉ የት/ቤቶች መዘጋት እና የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት በመደበኛነት አለመጀመርን ለአብነት ያነሳሉ።
አዋጁ ግቡን መትቷል?
ለስድስት ወራት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመጠናቀቁ ከቀናት በፊት ጥር 24/2016 ዓ.ም. ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወስኗል። ለዚህም ክልሉን ለማረጋጋት “ተጨማሪ ሥራዎች በመኖራቸው” ምክንያት እንዲራዘም መደረጉ ተነግሯል።
የሕዝብ እንደራሴ የሆኑት አቶ አበባው ደሳለው አዋጁ ከመጽደቁ ከአንድ ቀን በፊት የገዥው ፓርቲ የም/ቤት አባላትን የሰበሰበው መንግሥት የክልሉን የፀጥታ ሁኔታ በሁለት ወር ውስጥ በቁጥጥር ስር እንደሚያውል አሳውቆ “ግፊት” በማድረግ ነበር ይላሉ።
የአዋጁን መጽደቅ ከተቃወሙ የምክር ቤት አባላት አንዱ ሆኑት አቶ አበባው፤ ባለፉት ስድስት ወራት ክልሉን ወደተረጋጋ ሁኔታ መመለስ አልተቻለም በማለት “አዋጁ ግቡን አልመታም” ይላሉ።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ም/ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ራሄል ባፌ፣ “ቀድሞውንም ለፖለቲካዊ ጥያቄ ወታደራዊ ምላሽ መስጠት ተገቢ አልነበረም” በሚል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ይቃወማሉ።
“ግልጽ ጦርነት ነው” ሲሉ የክልሉን ሁኔታ የሚገልጹት ፖለቲከኛዋ፤ በወታደራዊ እርምጃው አንጻራዊ ሰላምን ማምጣት አልተቻለም ይላሉ።
“. . . አንጻራዊ ሰላም በተፈለገው መጠን ማምጣት አልተቻለም። እርምጃዎች ሲወሰዱም ተመጣጣኝ አድርጎ ማየት አልተቻለም። ስለዚህ ኮማንድ ፖስቱ በአብዛኛው ሰላማዊ እንቅስቃሴዎችን እና ሕዝባዊ አገልግሎቶችን በአካባቢው ተግባራዊ ማድረግ አልቻለም” ይላሉ።
በስድስት ወራቱ የአዋጁ ቆይታ ክልሉ በሚፈለገው መጠን አለመረጋጋቱ እና ሰላም አለመስፈኑ፣ ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም ምክንያት መሆኑ ይታመናል። በቀጣይ ወራትስ የአማራ ክልል ወደ መረጋጋት ይመለስ ይሆን?

የአዋጁ ግብ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶ/ር የሺጥላ ወንድሜነህ ደግሞ አማራ ክልል በአሁኑ ወቅት “በእርስ በርስ ጦርነት” ውስጥ ነው ይላሉ።
በክልሉ የተነሳው ችግር በእሳቸው አጠራር “ፖለቲካዊ አመጽ” በመሆኑ የኃይል እርምጃን አማራጭ አድጎ መውሰዱ “የተፈለገውን ውጤት” አላመጣም የሚል እምነት አላቸው።
“ችግሮቹ ሊፈቱ አልቻሉም። በስድስት ወር ውስጥ መንግሥት ችግሮቹን እፈታለሁ ብሎ አስቦ ነበር የተንቀሳቀሰው። በስድስት ወር ውስጥ ችግሮቹ አልተፈቱም።
“መንግሥት ‘የሕግ የበላይነትን አረጋግጣለሁ’ ብሎ ነው ወደ ክልሉ የተንቀሳቀሰው። ይህ ምን ያህል ዕውን ሆኗል የሚለውን ስናይ አሁንም አማጺያን አሉ፤ የፖለቲካ አመጹ አሁንም እንደቀጠለ ነው፤ ክልሉ አሁንም በፖለቲካ፣ በፀጥታ እና በደኅንነትም የተረጋጋ አይደለም። ስለዚህ ከዚህ አንጻር ግቡን አሳክቷል ለማለት በጣም ያስቸግራል” ይላሉ።
የም/ቤት አባሉ አቶ አበባው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውጤት “ቀውሱን ማባባስ ነው” በማለት “እያንዳንዱ የአማራ ክልል ከተሞች በከባድ መሳሪያ ተደብድበዋል። ንጹሃን ሞተዋል። ይሄ ደግሞ ሕዝቡን እልህ ውስጥ ነው ያጋባው።
“ፖለቲከኞቹ ሲታሰሩ፣ እህት እና ወንድሞቻቸው ሲሞቱ፣ ሲቆስሉ፣ ሲደፈሩ እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናት፣ ት/ቤቶች፣ የጤና ተቋማት ሲወድሙ በእልህ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲገባ ነው ያደረገው” ሲሉ መንግሥት “የተሳሳተ ስሌት” ውስጥ መግባቱን ይናገራሉ።
አዋጁ የሕዝቡን ጥያቄ ከግምት ውስጥ ባለማስገባቱ ስኬት የለውም የሚሉት ዶ/ር ራሄል ባፌ፤ “የአዋጁ ውጤት የጅምላ እስር ነው። በመሆኑም አዋጁ ለጥሰቶች ሽፋን ከመስጠት ውጪ እውነተኛ ሰላምን ያመጣ አይደለም” ይላሉ።
ፖለቲከኛዋ አክለውም በክልሉ ውስጥ የተሰማራው የፀጥታ ኃይል አልፎ አልፎ መንገዶችን ከማስከፈት የዘለለ ጠብ ያለ አዎንታዊ ነገር አላሳየም ባይ ናቸው።
መንግሥት ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጠቅላይ መምሪያ ባከናወነው ተግባር “ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከመፍረስ መታደግ ተችሏል” ሲል ስኬቱን ይናገራል። አዋጁ ከመታወጁ በፊት የታጠቁ ኃይሎች “በተዛባ መረጃ” የከተሞችን እንቅስቃሴና ግንኙነትን እንዲገታ አድርገዋል ሲል በንጽጽር ያነሳል።
ዶ/ር የሺጥላ ወንድሜነህ፣ የአዋጁ ግብ ቀድሞውኑ “የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ነው” ወይስ “የፖለቲካ ሥርዓቱን ኅልውናው ማስቀጠል” የሚለው ሊሰመርበት ይገባል ባይ ናቸው።
“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ግብ እውነት በክልሉ የተከሰተውን የፀጥታ እና የፖለቲካ ቀውስ በመፍታት ዜጎች የተሻለ ነገር እንዲያገኙ ለማድረግ ነው? ወይስ ደግሞ በክልሉ መንግሥት ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ ታስቦ የተደረገ ነው? የሚለው በደንብ ማየት ያስፈልጋል” ይላሉ።
መቋጫው ምን ይሆናል?
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ አበባው በቀጣይ ድርድር ሊኖር እንደሚችል ተስፋቸውን በመጠቆም፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲያበቃ እንደማይራዘም ተስፋ ነበራቸው።
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶ/ር የሺጥላ፣ አሁንም መንግሥት የኃይል አማራጭን መርጦ የሚቀጥል ከሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የመራዘም ዕድል አለው ይላሉ። በቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ ሦስት የቢሆን ዕይታዎች እንዳሉም ያነሳሉ።
“መንግሥት የፋኖ ኃይሎችን ለመደምሰስ ሙከራ ያደርጋል” ሲሉ የመጀመሪያ የቢሆን ዕይታ የሚያነሱት ዶ/ር የሺጥላ፤ “የመሆን ዕድሉ ግን አነስተኛ ነው” ሲሉ የእስካሁን ውጤቱን ይጠቅሳሉ።
“የፋኖ ኃይሎች ተጠናክረው መንግሥትን ለመጣል ይሞክራሉ” በማለትም ሁለተኛውን የቢሆን ዕይታቸውን በማንሳት “ይህም ግን ብዙም የሚያስኬድ” እንዳልሆነ ይጠቁማሉ። ለዚህም “ታጣቂ ቡድኑ ግልጽ አቅጣጫ” እንደሌለው በምክንያትነት ያቀርባሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ክልሉ “የተራዘመ ጦርነት” ውስጥ የመቆየት ዕድሉ ሰፊ ነው የሚሉት ዶ/ር የሺጥላ፤ መጪው ጊዜ አሳሳቢ እንደሆነ ይጠቁማሉ።
“በክልሉ የተራዘመ ጦርነት ይኖራል። በጦርነቱ ምክንያት ክልሉ እየደቀቀ ይሄዳል። . . . አደጋው ለክልሉ በጣም ከፍተኛ ስለሚሆን፤ ቀውሱ ይቀጥላል ማለት ነው” ይላሉ።
በአማራ ክልል ያለው ጦርነት “አሸናፊው የማይለይበት ጦርነት” ነው የሚሉት ዶ/ር ራሄል ባፌ፤ መሸናነፍ ቢኖር እንኳ ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ አይሆንም ሲሉ መጪው ጊዜ አስጊ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ።
“አሁንም ቢሆን አልረፈደም” የሚሉት ፖለቲከኛዋ ጦርነቱ ቆሞ “ወደ ሰላማዊው መፍትሄ መምጣት የግድ ነው። አሁን ግን የበላይነትን እስከምናገኝ የሚል ፉክክር መታየቱ እንደ አገር ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም” ሲሉ እንደ ጊዜው እንራመድ ይላሉ።
በአማራ ክልል የተከሰተው “ችግር በኃይል አይፈታም፤ የኃይል አማራጭ መሠረታዊ ችግሮችን አይፈታም” ሲሉ የፖለቲከኛዋን ሀሳብ የሚደግፉት ዶ/ር የሺጥላ ወንድሜነህም “መፍትሔው ንግግር ነው” ይላሉ።
መንግሥት በተደጋጋሚ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ፍላጎት እንዳለው ቢገልጽም፣ እስካሁን በሁለቱም ወገን ለዚህ ግብ መሳካት የሚሆን ይፋዊ እርምጃ ስለመወሰዱ የሚታወቅ ነገር የለም።
__________
*ማስታወሻ፡ ለዚህ ዘገባ ቃለ ምልልሶች የተደረጉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማራዘም ውሳኔን ከመሳለፉ ከቀናት በፊት ነው።