
ከ 7 ሰአት በፊት
የሶማሊያ የባሕር ጠረፍ ዘራፊዎች እንደ አዲስ መርከቦችን ዒላማ ማድረግ ጀምረዋል።
ይህ ክስተት ከአስርት ዓመታት በፊት የነበረውን ትዝታ አየመለሰ ነው።
በወቅቱ የታጠቁ የሶማሊያ ፓይሬቶች የባሕር ጠረፉን ተቆጣጥረው መርከቦችን በማገት ሚሊዮን ዶላሮች ክፍያ ይጠይቁ ነበር።
ይህ ዓለምን አስጨንቆ የነበረ ዝርፊያ ሀገራት ተደራጅተው የሥፍራውን ደኅንነት ለመጠበቅ ባደረጉት ሙከራ ቀዝቅዞ ነበር።
ነገር ግን ከሰሞኑ ታጣቂዎች መርከቦችን እያገቱ ክፍያ መጠየቅ መጀመራቸው አቅማቸውን አደራጅተው እንደ አዲስ ተነስተው ይሆን ወይ የሚለውን ጥያቄ ጭሯል።
- ከስደተኛነት ተነስቶ በተለያዩ አገራት የግንባታ ኩባንያ ያቋቋመው ኤርትራዊ4 የካቲት 2024
- የቀድሞው የፓኪስታን መሪ ኢምራ ካን ትዳራቸው እስላማዊ አልነበረም ተብለው 7 ዓመት ተፈረደባቸው4 የካቲት 2024
- የፌስቡክ 20ኛ ዓመት፡ ግዙፉ ማሕበራዊ ሚድያ ዓለምን የቀየረባቸው አራት ጉዳዮች1 የካቲት 2024
ከሰሞኑ የተከሰተው ምንድነው?
በምስራቅ አፍሪካ የባሕር ጠረፍ ደኅንነት የሚቆጣጠረው የአውሮፓ ኅብረቱ ኢዩናቫፎር አታላንታ መረጃ እያሰባሰበ ነው።
ድርጅቱ እንደሚለው ካለፈው ኅዳር ጀምሮ 14 መርከቦች በሶማሊያ የባሕር ጠረፍ ፓይሬቶች ታግተዋል።
በዚያው ወር የኢራን ባንዲራ የሰቀለች ዓሳ አጥማጅ መርከብ ጥቃት ደረሰበት። ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ የላይቤሪያ ባንዲራ ያነገበች መርከብ የፓይሬቶቹ ዒላማ ሆነች።
በሁለቱም መርከቦች ውስጥ የነበሩ ሠራተኞች አልተጎዱም።
ሴንትራል ፓርክ የተሰኘውን የላይቤሪያ መርከብ ያዳኑት የአሜሪካ ወታደሮች ሲሆኑ ታጣቂዎች የሶማሊያ ፓይሬቶች ሳይሆኑ አይቀሩም ይላሉ።
ባለፈው ታኅሣሥ ደግሞ የማልታ ባንዲራ የሰቀለችው ኤምቪ ሩዌን ታገተች።
መርከቧ አሁንም በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ሥር ያለች ሲሆን 17 የመርከቧ ሠራተኞችም ታግተው ይገኛሉ።
ዓለም አቀፉ ማሪታይም ቢሮ እንደሚለው ይህች መርከብ ባለፉት ስድስት ዓመታት በሶማሊያ የባሕር ጠረፍ ዘራፊዎች ቁጥጥር ሥር የዋለች የመጀመሪያዋ መርከብ ናት።
ባለፈው የጥር ወርም እንዲሁ ተመሳሳይ ጥቃቶች የደረሱ ሲሆን የሕንድ ባሕር ኃይል ባሳፍነው ሳምንት ብቻ ሶስት መርከቦችን አድኗል።
ባለፈው አርብ የሕንድ ባሕር ኃይል 11 ኢራናዊያን እና 8 ፓኪስታናዊያን የያዘች መርከብ ማዳኑን ተናግሯል።
እገታው ለምን እንደ አዲስ ጀመረ?
የሶማሊያ ፓይሬቶች በአዲስ መልክ ሥራ የጀመሩት ያለውን የደኀንነት ክፍተት አይተው ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ።
ትሮልስ በርሻል ሄኒንግሰን የሮያል ዳኒሽ ዲፌንስ ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው።
በአውሮፓውያኑ 2005 እና 2012 በሥፍራው የባሕር ጠረፍ ዘራፊዎች መንሰራፋት ሲጀምሩ የዓለም ሀገራት ተደራጅተው ቦታውን መጠበቅ ጀምሩ።
ነገር ግን በቅርቡ በቀይ ባሕር ጠረፍ የየመን ሁቲ ታጣቂዎች የሚያደርሱትን ጥቃት ለመግታት በማለት እኒህ ኃይሎች አድራሻቸውን ቀይረዋል ይላሉ።
“በወታደራዊ ቋንቋ ስናወራ የየመን ሁቲዎችን ሚሳዔል እና ድሮን ጥቃት መመከት ትልቅ ሥራ ነው። ስለዚህ ሁለቱንም በአንድ ጊዜ ማድረግ ከባድ ነው” ይላሉ ምሑሩ።
የኢንዲያን ኦሽን ኮሚሽን እንደ ሲሼልስ እና ኮሞሮስ ያሉ ሀገራት ያሉበት ቀጣናዊ ድርጅት ነው።
ኮሚሽኑ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ የባሕር ጠረፍ ዘራፊዎች እንደ አዲስ ያገረሹበት ሌላም ምክንያት አለ ይላል።
የሶማሊያ ፓይሬቶች ከፍተኛ ጥቃት አድርሰው የነበረው ከ10 ዓመታት በፊት ነበር።
አሁን አሁን አንዳንድ ዓሳ አጥማጆች ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ዓሳ የሚያጠምዱ የውጭ ድርጅቶች ኑሮ የሚገፉበትን መንገድ ሲቀሟቸው ወደ ባሕር ጠረፍ ዘራፊነት ገብተዋል ይላል ኮሚሽኑ።
ኢስላማዊው ታጣቂ ቡድን አል-ሸባብ የባሕር ጠረፍ ዘራፊዎች ከዘረፉት ገንዘብ ኮሚሽን የሚያገኙ ከሆነ ለዘራፊዎች የጦር መሣሪያ እንደሚሰጡ የሚጠቁሙ ዘገባዎች መውጣት ጀምረዋል።

አጋቾቹ የሚፈልጉት ምንድነው?
በአውሮፓውያኑ 2005 እና 2012 በአፍሪካ ቀንድ ያሉ የባሕር ጠረፍ ዘራፊዎች ከ339 እስከ 413 ሚሊዮን ዶላር ዘርፈዋል ይላል የዓለም ባንክ ዘገባ።
ይህ የሚያደርጉት መርከቦችን በቁጥጥር ሥር በማዋልና ሠራተኞችን አግቶ ክፍያ በመጠየቅ ነው።
የናይጄሪያው ፌዴራል ዩኒቨርሲቲ መምሕር የሆኑት ሳሙዔል ኦየዌሌ በቅርብ ጊዜ እየታዩ ያሉት እገታዎች ዋና ዓላማቸው ገንዘብ ነው ይላሉ።
የምስራቅ አፍሪካን የባሕር ጠረፍ የሚያጠኑት ምሑሩ ሌላም ምክንያት ሊኖር እንደሚችል ቡገምቱም ማወቅ ቀላል አይሆንም ይላሉ።
“ከዚህ ቀደም በሥፍራው የነበሩትን እገታዎች ዓለም አቀፍ የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች መግታት ችለው ነበር።”
“አሁን ግን ምክንያታቸው ምን እንደሆነ ማወቅ ከባድ ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።
ኢንዲያን ኦሽን ኮሚሽን በቅርቡ የታዩት እገታዎች “አሳሳቢ ናቸው” ብሎ የተባበሩት መንግሥት ፀረ-ፓይሬትስ ተቋም አስቸኳይ ስብሰባ ማድረግ አለበት ሲል ይመክራል።
ሌሎች መሰል ተቋማት በሶማሊያ ባሕር ጠረፍ ላይ እየታዩ ያሉትን እገታዎች “እጅግ አሳሳቢ ናቸው” የሚሉ መግለጫዎች እያወጡ ነው።
ቢሆንም ይህ የዓለም አቀፍ ንግድ መተላለፊያ የሆነ ቦታ ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት “በሌላ ክስተት ተውጧል” ይላሉ ተባባሪ ፕሮፌሰሩ።
“በቀይ ባሕር ላይ እየሆነ ያለው ነገር በእርግጥም ከዚህ የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፤ አደገኛም ነው” ሲሉ የየመን ታጣቂዎች ጥቃት የሶማሊያውን እንደሸፈነው ይናገራሉ።
የሥፍራው ውጥረት
ኢንዲያን ኦሽን ኮሚሽን እንደሚለው በቅርቡ ከተከሰቱት እገታዎች 6 ያክሉ የባሕር ጠረፍ ዘረፋ ባሕሪ አላቸው።
ኢንተርናሽናል ማሪታይም ቢሮም እንዲሁ “እገታዎች የባሕር ጠረፍ ዘረፋ [ፓይሬሲ] ናቸው” ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።
መገናኛ ብዙኃን ዘራፊዎቹ መርከቦችና ሠራተኞቻቸውን ካገቱ በኋላ ማስለቀቂያ ገንዘብ እየጠየቁ ነው ሲሉ ዘግበዋል።
የቼስተር ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ቀንድ ምሑር የሆኑት ዶ/ር ጄስ ሲሞንድስ ከሰሞኑ የተከሱት እገታዎችን በዝግታ ማጥናት ያስፈልጋል የሚል አስተያየት ይሰጣሉ።
የተባበሩት መንግሥታትን ትንታኔ ጠቅሰው እንደሚሉት የባሕር ጠረፍ ዘረፋ ከአንድ ሀገር የውሃ ክልል ውጭም ሊከሰት ይችላል።
ዶ/ር ሄኒንግሰን እና ዶ/ር ኦየዌሌ ሥፍራውን ሲቆጣጠሩ የነበሩት ዓለም አቀፍ የባሕር ኃይሎች በየመን ጠረፍ አቅራቢያ ያለውን ጥቃት ለመመከት ወደ ሥፍራው ቢያቀኑም የሶማሊያውን ዘረፋ ለመመከት የሚያስችል አቅም አሁንም አላቸው ይላሉ።
ኢዩናቭፎር እና ሌሎች እንደ ሕንድ፣ እና ዩናይትድ ስቴትስ ያሉ የባሕር ኃይሎች ከሰሞኑ በርካታ ጥቃቶችን ማክሸፍ ችለዋል።
ነገር ግን ኢንዲያን ኦሽን ኮሚሽን እንደሚለው ከሕንድ ባሕር ኃይል በቀር ሌሎቹ አቅማቸውን ቀንሰው ነው በሥፍራው እየተንቀሳቀሱ ያሉት።
ዶ/ር ኦየዌሌ እንደሚሉት በሥፍራው ያለው ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ አሁን ለተከሰተው የባሕር ጠረፍ ዝርፊያ አስተዋፅዖ አድርጓል።
የሁቲ አማፂያን እስራኤል በጋዛ የምታደርሰውን ወታደራዊ እርምጃ የምታቆም ከሆነ መርከቦች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ለማቆም ቃል ገብተዋል።
ሶማሊያ ደግሞ ነፃነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር አለመግባባት ላይ ናት።
ሶማሊላንድ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ጋር የገባቸውን ስምምነት ተከትሎ ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ውጥረት ዘንቦበታል።