የአይቮሪ ኮስት ተጫዋቾች በደስታ ሲጨፍሩ

ከ 9 ሰአት በፊት

በአፍሪካ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ያለምንም ጎል በተጠናቀቀው የኬፕ ቨርዴ እና ደቡብ አፍሪካ ግጥሚያ የባፋና ባፋናዎቹ ግብ ጠባቂ ሮንዊን ዊሊያምስ አራት መለያ ምቶችን በማዳን ቡድኑን ለግማሽ ፍጻሜ አብቅቷል።

በጨዋታው ድንቅ ኳስ ማዳን ችሎ የነበረው አምበሉ ዊሊያምስ በመለያ ምቱ ደግሞ የቤቤን፣ የዊሊ ሴሜዶን፣ ላሮስ ዱአርቴን እና ፓትሪከክ አንድራዴን ኳሶች አድኗል።

የኬፕ ቨርዴው ግብ ጠባቂ ቮዝንሃ በበኩሉ በተጨማሪው ሰዓት የተደረጉበትን ሁለት ድንቅ ሙከራዎች አክሽፏል።

ደቡብ አፍሪካ በግማሽ ፍጻሜው ናይጄሪያን የምትገጥም ሲሆን ይህም በ2000 የደረሰባትን ሽንፈት የምትበቀልበት አጋጣሚን ፈጥሮላታል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአብዛኛው ጥሩ የሚባል የጎል ዕድል ያልታየበት ሆኖ አምሽቷል።

በጊልሰን ቤንችሞል የተደረገበትን ሙከራ በአስደናቂ ሁኔታ ማዳን የቻለው ዊሊያምስ ውድድሩ ሲጠናቀቅ ኮከብ ግብ ጠባቂ ፉክክር ውስጥ እንደሚገባ ይጠበቃል።

በመለያ ምት ወቅት ደግሞ ሦስት ኳሶችን በተከታታይ ለማዳን ችሏል።

ከእያንዳንዱ ምት በኋላም ውሃ ኮዳነው ሲመለከት መታየቱ በውሃ ኮዳው ላይ የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾቹች በየትኛው አቅጣጫ እንደሚመቱ መረጃ ጽፎ ይሆናል የሚሉ ግምቶችን ከፍ አድርጓል።

ኬፕ ቨርዴ በኳስ ቁጥጥር የበላይ ሆና ብትጀምርም ደቡብ አፍሪካዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል።

በጨዋታው ኬፕ ቨርዴ 51 በመቶ የኳስ ቁጥጥር ነበራት።

25 ሙከራዎችን ብታደርግም ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎቿ ቁጥር ሁለት ብቻ ናቸው። በአንጻሩ ደቡብ አፍሪካ ከ16 የግብ ሙከራዎች ስድስቱ ዒላማቸውን ጠብቀዋል።

የደቡብ አፍሪካ ተጫዋቾች በደስታ ሲጨፍሩ

ምሽት 2 ሰዓት በጀመረው ሌላኛው የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ አዘጋጇ አይቮሪ ኮስት በ122ኛው ደቂቃ ባስቆጠረችው ጎል አራቱን ቡድኖች ተቀላቅላለች።

በመጀመሪያው አጋማሽ የአይቮሪ ኮስቱ ኦዲሎን ካሶኖ በሁለት ቢጫ ካር ከሜዳ መሰናበቱን ተከትሎ አዘጋጇ ሀገር ብልጫ ተወስዶባት አምሽታለች።

ማሊዎች በኔኔ ዶርጌሌስ ጎል አንድ ለምንም እየመሩ ሳለ በ90ኛው ደቂቃ ሳይመን አዲንግራ ለአይቮሪ ኮስት አስቆጥሮ ጨዋታው ወደ ጭማሪ ደቂቃ እንዲያመራ አድርጓል።

የተጨመረው 30 ደቂቃ ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ደቂቃዎች ሲቀሩት ዲያኪቴ ለአይቮሪ ኮስት በማስቆጠር ደጋፊዎቹን አስቦርቋል።

የምድብ ድልድሉን ምርጥ ሶስተኛ ሆነው ያጠናቀቀችው አይቮሪ ኮስት አሠልጣኝ ዦን ሉዊ ጋሴን አሰናብታ በጊዜያዊ አሠልጣኝ ነው ለዚህ የበቃችው።

ወደ ሩብ ፍፃሜ ለማለፍ ከሴኔጋል ተመድባ የነበረችው አይቮሪ ኮስት እዚህ ትደርሳለች ብለው የገመቱ እጅግ ጥቂት ናቸው።

ነገር ግን ጊዜያዊው አሠልጣኝ ኤሜርሴ ፋየ በብዙ ድራማ ታጅበው ብሔራዊ ቡድናቸውን ለግማሽ ፍፃሜ ማብቃት ችለዋል።

የአፍሪካ ዋንጫው ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ረቡዕ ዕለት የሚከናወኑ ይሆናል።

ናይጄሪያ ደቡብ አፍሪካ የምትገጥመበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

በአስቸጋሪ ሁኔታ ከምድቧ ያለፈችው አዘጋጇ አይቮሪ ኮስት ለዋንጫ ለማለፍ ዲሞክራቲክ ኮንጎን ትገጥማለች።