EthiopianReporter.com 

ሰላማዊት መንገሻ

February 4, 2024

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የስድስት ወራት ሪፖርታቸውን ባቀረቡበት ወቅት

የታጠበ ጨው ሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባወጣው መመርያ ምክንያት ባለፉት ስድስት ወራት ከአፋር ክልል የቀረበው ጨው 63.4 በመቶ ብቻ በመሆኑ፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ችግር እየደረሰባቸው መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ጥር 22 ቀን 2016 ዓ.ም. የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት እንደተገለጸው፣ ለአገር ውስጥ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ለማቅረብ ታቅዶ ከነበረው 157,500 ኩንታል ጨው ውስጥ 99,800 ኩንታል የቀረበ ሲሆን ይህም የዕቅዱን 63.4 በመቶ ነው፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባወጣው ‹‹የጨው ግብዓት መመርያ›› ከአፋር ክልል ውጪ ያሉትን የጨው አቀነባባሪዎች ያገለለ መሆኑ በችግርነት ተጠቅሶ፣ ከዚህ በፊት በሁሉም ክልሎች ከሚገኙ አቀነባባሪዎች የታጠበ ጨው ሲወስዱ የነበሩ የኬሚካል፣ የጨርቃ ጨርቅና የመጠጥ ኢንዱስትሪዎች ለችግር ተጋላጭ እንዲሆኑ ማድረጉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ከዚህ በፊት በኢንዱስትሪ ግብዓቶች አቅራቢ ልማት ድርጅት (ኢግልድ) ይቀርብ የነበረው ጨው የአፋር ክልል አዲስ ባደራጃቸው መሥሪያ ቤቶች እንዲቀርብ የሚል ውሳኔ በክልሉ በመወሰኑ፣ ድርጀቶች ምንም ዓይነት ጨው እያቀረቡ አለመሆኑ፣ በዚህም ሳቢያ የጨው አቅርቦት 63 በመቶ ዝቅ እንዲል በማድረግ የግብዓት አቅርቦት ችግር መፈጠሩን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

የእንስሳት ዕርድ በብዛት በሚደረግባቸው በዓላት ወቅት ለቆዳ ፋብሪካዎች በቂ ጨው የማይቀርብ በመሆኑ፣ በኮንትሮባንድ የተያዘ ጨው ወደ ኢግልድ እንዲገባ ተደርጎ ለሽያጭ መቅረቡን፣ ወደፊትም በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ሌላ ከፍተኛ ችግር እንደሚፈጥር አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡

በአገሪቱ ያሉ ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅምና ዕድገት ለማምጣት በቂ ማሽነሪዎች፣ ማሽነሪዎች የሚንቀሳቀሱበት የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ግብዓቶችና የሰው ኃይል አስፈላጊ እንደሆኑ በመግለጽ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የቆዳና የኬሚካል ፋብሪካዎች የማምረት አቅም ዝቅ ያለው በእነዚህ ምክንያቶች ነው ብለዋል፡፡

የምርት ዋጋና መጠን የሚወሰነው በዋናነት የሸማቾችን ደኅንነት ለመጠበቅ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ በኩል 36 ሚሊዮን ኩንታል ጨው ተመርቶ ወደ ገበያ ሳይወጣ፣ በሌላ በኩል በጨው እጥረት ፋብሪካዎች ችግር ላይ ሆነው ከፍተኛ ችግር ተፈጥሯል ሲሉ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ለዚህ ዋነኛ መፍትሔ የሚሆነው የምርቱን ንፅህናና ደረጃ በመቆጣጠር የጨው ንግድ በነፃ ገበያ እንዲመራ በማድረግ፣ ለሚያስፈልጋቸው ኢንዱስትሪዎች የማድረስ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የጨው ምርት በብዛት የሚፈልጉት የቆዳ አቅራቢዎች በጨው እጥረት ምክንያት ሲዘጉ፣ የቆዳ ምርት ላይ የተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ጨው ገበያ ውስጥ መገኘት ባለመቻላቸው ከውጭ ለማስገባት ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ 165 ሚሊዮን የቀንድ ከብቶች እያሉ 40 ሚሊዮን ያህል ቆዳ ማቅረብ እየተቻለ፣ በጨው ምክንያት ከውጭ ለማስገባት የሚያስብ ነጋዴ እንዲኖር ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ችግሩን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንዴት ለመፍታት እንዳቀደ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

በአፋር ክልል እንዲያቀርብ የተመረጠው ኮርፖሬሽን የአመራር ችግር ያለበት በመሆኑ፣ ኢንዱስትሪዎቹ በሚፈልጉት ወቅት ማግኘት እንዳልቻሉ የገለጹት አቶ መላኩ፣ ለዚህም መፍትሔ ለማበጀት ከክልሎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ቢደረግም ችግሩ ግን እየቀጠለ ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም፣ ‹‹ጥሬ ጨውን ከአፋር ክልል ውጪ በሌሎች ክልሎች የሚገኙ አቅራቢዎች ማቅረብ አይችሉም፤›› የሚለው መመርያ ትክክል አለመሆኑን በመግለጽ፣ የክልሎች አሠራርን በማሻሻል የኢንዱስትሪዎች ችግር የሚፈታበት መንገድ እንዲፈጠር ከመንግሥት አቅጣጫ መሰጠት አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የሚኒስትሩን ሐሳብ የተጋሩት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አማረች ባካሎ (ዶ/ር)፣ በክልሉ የሚመረተው ሀብት የኢትዮጵያ ሕዝብና የመንግሥት እንጂ የክልሉ ብቻ ባለመሆኑ በቂ የጨው ግብዓት እያለ ኢንዱስትሪዎች መቸገር የለባቸውም ብለዋል፡፡

ክልሎች የሚይዙት ሀብት የክልሉ ብቻ ነው የሚል ዕሳቤ ከተስፋፋ ባለው መስተጋብር ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር በመሆኑ፣ አሁን ያለው አሠራር መፍትሔ ማግኘት አለበት ሲሉ አማረች (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ክልሎች ሕገ መንግሥቱን የሚያስፈጽሙና የፌዴሬሽኑ አካላት በመሆናቸው፣ ይህ ችግር ሕገ መንግሥቱን በሚያስፈጽመው አካል መፈታት አለበት ሲሉ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡