
February 4, 2024
በስድስት ወራት ከአምራች ኢንዱስትሪ ከወጪ ንግድ የተገኘው 140.3 ሚሊዮን ዶላር፣ ማግኘት ከታቀደው አንፃር አነስተኛ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ጥር 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት እንደተገለጸው፣ በስድስት ወራት ወደ ውጭ የተላከው የምርት መጠን 74,956 ቶን ነው፡፡ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ340 ቶን ቅናሽ ማሳየቱን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡
ከተላኩት የኢንዱስትሪ ምርቶች የተገኘው 140.3 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ፣ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 194 ሚሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር በ53.7 በመቶ መቀነሱ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
የጂቡቲ ጉምሩክ አሠራር በየጊዜው መቀያየር (አነስተኛ የኮንቴይነር መጠን ገደብና የዶክመንት አቀራረብ ሥርዓት መለወጥ)፣ እንዲሁም የቀይ ባህር መስመር ሥጋት ከጥቅምት ጀምሮ በወጪና በገቢ ንግድ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት ገልጸዋል፡፡
ከዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ (የዩክሬን የሩሲያ ጦርነት፣ የቀይባህር መስመር ሥጋት)፣ ከዋጋዎች ግሽበትና ከሎጂስቲክስ ወጪ መናር ጋር ተያይዞ የዓለም አቀፍ ገዥዎች ፍላጎት እየቀነሰ መምጣት የወጪ ንግድ ዝቅ እንዲል ካደረጉት ምክንያቶች መካከል እንደሚጠቀሱ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
ከቀረጥ ነፃ የንግድ ዕድል (አጎዋ) ስረዛ ጋር በተያያዘ የገዥዎች የምርት ትዕዛዝ በመቀዛቀዙ ምክንያት፣ በኢንዱስትሪዎች የምርቶች ክምችት መታየቱ አንደኛው ችግር እንደነበር ገልጸዋል፡፡
የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የአጎዋ ዕገዳ በ2016 ዓ.ም. ይስተካከላል የሚል ሐሳብ የነበራቸው ኢንዱስትሪዎች እያመረቱ ቢሆኑም፣ የአጎዋ ገደብ አለመነሳት ኢንዱስትሪዎቹን የመደናገጥ ሁኔታ ውስጥ ከቷቸዋል ሲሉ አቶ መላኩ አክለዋል፡፡
የወጪ ንግድ አፈጻጸም እንዲሻሻልና የአገር ውስጥ ምርታማነት እንዲጨምር የአገሪቱን ሦስት የፖለቲካ ስብራቶች ማለትም የማክሮ ኢኮኖሚ፣ የፍትሐዊ ተጠቃሚነትና የምርታማነት ችግሮች ማስተካከል እንደሚገባ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የስድስት ወራት ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ለሥራ ማስኬጃና ሊዝ ፋይናንስ 2.9 ቢሊዮን ብር ለማቅረብ ታቅዶ 3.3 ቢሊዮን ብር ቀርቧል፡፡
የዓለም ባንክ የሚያቀርበው ገንዘብ በ2016 ዓ.ም. የሚጠናቀቅ በመሆኑ፣ ወደ 2017 ዓ.ም. እና 2018 ዓ.ም. እንዲቀጥል ለማድረግ ውይይት እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ለከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች 23.7 ቢሊዮን ብር የቀረበ መሆኑን፣ በአገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ሁለት መሠረት፣ በአጠቃላይ ለኢንተርፕራይዞች ከሚቀርበው ብድር ውስጥ ከ12 በመቶ ወደ 24 በመቶ ማሳደግ የሚል ውሳኔ የተላለፈ ቢሆንም፣ ውሳኔው ባለመተግበሩ በአጠቃላይ ከተሰጠ ብድር ጋር ሲነፃፀር 13.8 በመቶ ብቻ አፈጻጸም ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ለማቅረብ ከታቀደው 338 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ውስጥ 274 ሚሊዮን ዶላር የቀረበ ቢሆንም፣ አሁንም የግብዓት እጥረት ችግርን ለመፍታት በዱቤ ግዥ (Supply Credit) እና ፍራንኮ ቫሉታ አማራጮች መታየት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
በሪፖርቱ መሠረት 67 ያህል የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ታቅዶ 129 ኩባንያዎች እንዲገቡ በማድረግ፣ 18.76 ቢሊዮን ዶላር ያህል ፍሰት ማግኘት መቻሉ ተገልጿል፡፡
የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ የሆነበት ምክንያት ኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነትን በመቀላቀሏ የተፈጠረ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሆኑን፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡