

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ ዶ/ር) እና ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር ውይይት ባደረጉበት ወቅት
ዜና የአውሮፓ ኅብረት ቡናን በሚመለከት ያወጣውን ሕግ ተፈጻሚ ለማድረግ ኮሚቴ ተዋቀረ
ቀን: February 4, 2024
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የአውሮፓ ኅብረት ያወጣውን ሕግ ተፈጻሚ ለማድረግና ዘላቂ አሠራሮችን ለመከተል፣ በርካታ ተቋማት የተካተቱበት ኮሚቴ ማዋቀሩን አስታወቀ፡፡
ባለሥልጣኑ ይህንን ያስታወቀው የአውሮፓ ኅብረት ያወጣውን ሕግ በተመለከተ ከኢትዮጵያ ቡና ማኅበር፣ ከዩኒየኖች፣ ከቡና ላኪዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ሐሙስ ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ውይይት ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡
የአውሮፓ ኅብረት ቡናን ጨምሮ ወደ አባል አገሮቹ የሚላኩ ሰባት የምርት ዓይነቶች ከደን ጭፍጨፋና መመናመን ነፃ መሆናቸው ሳይረጋገጥ፣ ለግብይት እንዳይቀርቡ የሚከላከል ሕግ አውጥቶ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ ማቀዱ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ከቡና የምታገኘው ገቢ እንዳይቀንስና የአውሮፓ ኅብረት ያወጣው ሕግ እንቅፋት እንዳይፈጥር ከታች ጀምሮ ለመሥራት ኮሚቴ መዋቀሩን፣ የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት ያወጣውን ሕግ ለመፈጸም ሰፊ ሥራ እንደሚጠይቅ የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ቡና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ጠቃሚ በመሆኑ ተረባርቦ መሥራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት ባዘጋጀው የአፈጻጸም መርሐ ግብር መሠረት፣ የኢትዮጵያ የቡና ምርት ከደን ጭፍጨፋ ነፃ ሆኖ እየተመረተ ነው የሚለውን ለመለየት የተዋቀረው ኮሚቴ ትልቁን ድርሻ ይይዛል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ ኅብረት ያወጣውን ሕግ ለማሟላት በሒደት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ሕጉ ከመውጣቱ በፊት የአውሮፓ ኅብረት የሚያዘውን አሠራር የተከተለ ሰነድ ዩኒየኖችና አልሚዎች ማዘጋጀታቸውን አብራርተዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት የሚፈልገውን ሰነድ ለማስገባት ባለሥልጣኑ በሒደት ላይ ቢሆንም ጉዳዩ ጊዜ የሚጠይቅ ስለሆነ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አገሮች ተጨማሪ ጊዜ መጠየቃቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡
ባለሥልጣኑ የአውሮፓ ኅብረት ካወጣው ሕግ ጋር የሚናበቡ ሥራዎችን ማከናወን የሚያስችለው የሦስት ዓመት የአፈጻጸም መርሐ ግብር ማዘጋጀቱን፣ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት ያወጣውን ሕግ ለመተግበር ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ አርሶ አደሮችን በተገቢው መንገድ ሥልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ከደን ጭፍጨፋና መመናመን ነፃ የሆነ አቅርቦት ለማከናወን እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና አቅራቢዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ደሳለኝ ጀና ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአውሮፓ ኅብረት ያወጣውን ሕግ ለመተግበርና የአፈጻጸም ሥርዓቱን መሬት ለማውረድ ዘርፉ ውስጥ ያሉ ተዋናዮች በሙሉ ተቀናጅተው መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ውጭ 117 ሺሕ ቶን ቡና በመላክ 571 ሚሊዮን ዶላር ያገኘች ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ 1.7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱ ይታወሳል፡፡