EthiopianReporter.com 

የጤና ሚኒስትር ደኤታ ደረጀ ድጉማ (ዶ/ር)

ማኅበራዊ የሥርዓተ ምግብ አለመመጣጠን ሕፃናትን ያለ ዕድሜያቸው እየቀጨ መሆኑ ተነገረ

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: February 4, 2024

በየማነ ብርሃኑ

የምግብ እጥረትና የሥርዓተ ምግብ አለመመጣጠን ችግር 50 በመቶ ለሚሆኑ ሕፃናት ያለ ዕድሜ ሕይወት ማለፍ ምክንያት መሆኑ ተገለጸ፡፡

ጥር 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ፍኖተ ካርታ ዲያግኖስቲክ ጥናት መድረክ ላይ የጤና ሚኒስትር ደኤታ ደረጀ ድጉማ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ የምግብ እጥረትና ሥርዓተ ምግብ አለመመጣጠን በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለጤና ችግሮች ተጋላጭ እያደረገ ነው፡፡

በቅርቡ በተደረገ ጥናት 39 በመቶ ያህሉ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት የቀነጨሩ፣ 11 በመቶ ደግሞ የቀጨጩ መሆናቸው እንደተረጋገጠ ያስረዱት ደረጀ (ዶ/ር)፣ አሁን ያሉት የተለያዩ የሥርዓተ ምግብ ችግሮች ሥር ከሰደዱና ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ሥርጭት መጠን እየጨመረ መምጣት ጋር ተዳምረው ምርትና ምርታማነትን በመቀነስ የሰው ኃይል ልማትና የአገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ሊጎዳ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ በ2015 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) እና ከዓለም አቀፍ የምግብ ጥናት ተቋም (International Food Policy Research Institute-IFPRI) ጋር በመተባበር በተደረገ ጥናት በ2014 ዓ.ም. በተከናወነው የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራ 59,717 ሕፃናት ከመቀንጨርና 2,904 ያህሉን ከሞት ለመታደግ ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ በ2015 ዓ.ም. ባካሄደው ጥናት፣ 99,080 ሕፃናትን ከመቀንጨር መታደግና 3,033 ጨቅላ ሕፃናትን ከሞት ለመከላከል መቻሉን ተናግረዋል፡፡

የምግብ እጥረትና ሥርዓተ ምግብ አለመመጣጠን ችግር ለደም ማነስ፣ ከክብደት በታች ለመሆንና ለመቀንጨር አጋላጭ መሆኑን የገለጹት ደረጀ (ዶ/ር)፣ በተለይም መቀንጨር በሕፃናት አዕምሯዊና አካላዊ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የማሳደር፣ ዝቅተኛ የትምህርት አቀባበል፣ አዳዲስ ነገሮችን የማፍለቅ ችሎታ ውስንነትና በሚሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ ብቁ፣ ውጤታማና አምራች ዜጋ እንዳይሆኑ የሚያደርግና ለተደጋጋሚ በሽታም የሚያጋልጥ ነው ብለዋል፡፡

የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራ የሞት ምጣኔን መቀነስ ያስቻለ መሆኑን፣ ይህንን ውጤት በተቻለ መጠን ለማስቀጠል እንዲቻል የፕሮግራም ትግበራው ከ240 ወደ 700 ወረዳዎች እንዲሰፋ በቅርቡ በተካሄደ ከፍተኛ አመራር መድረክ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2013 በተደረገው ጥናት በመቀንጨር ተፅዕኖ ብቻ አገራችን ከጥቅል አገራዊ ምርት (GDP) 16.5 በመቶ ያህሉን እያጣች ነው የሚሉት ሚኒስትሩ፣ ይህም ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡