
February 4, 2024 – EthiopianReporter.com
በሥልጣኔ በተራመዱ አገሮች መንግሥታት የፖሊሲ ውሳኔዎችን ሲያስተላልፉ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅምን፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትንና የሕዝብ ኑሮ ደረጃን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ የመንግሥት ውሳኔዎች ነባራዊ ሁኔታዎችን በማገናዘብ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ውሳኔዎቹ ፈራቸውን ሲስቱ ግን በተለያዩ መንገዶች አሉታዊ ጫና ያስከትላሉ፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጫና ሲፈጠር የዜጎች የሥራ ዋስትና፣ የገቢ ምንጭና የኑሮ ደረጃ ይናጋል፡፡ ማኅበራዊ ጫና ሲከሰት ደግሞ ትምህርት፣ የሕዝብ ጤና፣ እንዲሁም የሲቪል መብቶች ችግር ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጫናዎች ሲበራከቱ ወንጀሎች ይስፋፋሉ፡፡ መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎችም ሆኑ ስትራቴጂዎች በጥናት ላይ ሳይመሠረቱ ሲቀሩ፣ ከውጤታቸው ይልቅ አሉታዊ ተፅዕኗቸው እየበዛ አገር ችግር ላይ ትወድቃለች፡፡ በሁሉም ብሔራዊ ጉዳዮች የሚተላለፉ ውሳኔዎች ከአገር ነባራዊ ሁኔታና አቅም ጋር የማይገናዘቡ ከሆነ፣ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው የላቀ ስለሚሆን ችግሮች ይበራከታሉ፡፡ በአዋጭ ጥናቶች ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎች ግን ሁሉንም ወገኖች የሚያግባቡ መፍትሔዎች ስለሚያመነጩ፣ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ ያገለግላሉ፡፡ መንግሥት ሆይ ውሳኔዎችህ በዚህ መንገድ ይቃኙ፡፡
ሰሞኑን በተለያዩ ጉዳዮች በመንግሥት የተላለፉ ውሳኔዎች የፈጠሩት ግራ መጋባት ይታወቃል፡፡ በመንግሥት የሚተላለፉ ውሳኔዎች ከመፍትሔ ይልቅ ችግር ሲያስከትሉ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ በርካታ የሠለጠኑ አገሮች በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ ከመቀየራቸው በፊት የጊዜ ሰሌዳ አሰናድተዋል፡፡ ከባድ ተሽከርካሪዎችን ከናፍጣ ወደ ቤንዚን፣ ቀላል ተሽከርካሪዎችን መጀመሪያ በቤንዚንና በኤሌክትሪክ (Hybrid)፣ ከዚያም ሙሉ በሙሉ ወደ ኤሌክትሪክና ኃይድሮጂን ለመለወጥ ግብ አስቀምጠዋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሃ አገሮች ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ችግር ስላለባቸው፣ የመሠረተ ልማት ችግሮችን እየቀረፉ በሒደት ለውጡን መቀላቀላቸው ተገቢ ነው፡፡ ለነዳጅ የሚወጣ የውጭ ምንዛሪን ታሳቢ ብቻ ያደረገ ውሳኔ ተግባራዊ የመሆን ዕድሉ አናሳ ነው፡፡ ውሳኔዎች ሲተላለፉ ጠንካራ አመራርና ተግባራዊ ሊሆን ዕቅድ የሚፈጸሙ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ሙሉ በሙሉ ከማገድ በፊት፣ መንግሥት በራሱና የቅንጦት በሚባሉት ላይ ቅድሚያ በመስጠት በምዕራፎች የተከፋፈለ መርሐ ግብር ማውጣት ይገባዋል፡፡
በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ክልከላ ሲደረግ ወደፊት ሊገኙ የሚችሉ ጥቅሞች ማለትም የአየር ብክለት ቅነሳ፣ የነዳጅ ጥገኝነትን ማስቀረት፣ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አውቶሞቢሎችና የትራንስፖርት ተሽከርካሪዎችን በብዛት መጠቀምና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ የአየር ብክለት በመቀነስ የሕዝብ ጤናን ለመጠበቅ ያገለግላል፣ ከነዳጅ ጥገኝነት መላቀቅ ተለዋዋጭ ከሆነው የዓለም ገበያ ጫና የሚገላግልና ታዳሽ የኢነርጂ አማራጮችን እንደሚያስገኝ ይታመናል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ዋጋ በጣም ውድ ነው፡፡ መንግሥት ከፍተኛ ድጎማ ካላደረገ በስተቀር ዋጋቸው አይቀመስም፡፡ የኤሌክትሪክ ቻርጅ ማድረጊያ መሠረተ ልማት በጣም አነስተኛ በመሆኑ፣ መንግሥት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ካላደረገ በስተቀር ተግባራዊነቱ አጠራጣሪ ነው፡፡ ሌላው ተፅዕኖ በነዳጅ ኢንዱስትሪ ውስጥ የተሰማሩ በርካታ ዜጎች ሕይወት ላይ ከባድ ችግር ይፈጠራል፡፡ የመንግሥት ውሳኔ እነዚህንና ሌሎች ተዛማጅ ተግዳሮቶችን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል፡፡ ከነዳጅ ወደ ኤሌክትሪክ የሚደረገው ሽግግርም እንደ ዘበት የሚከናወን እንዳልሆነ መረዳት ይገባል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የግል አውቶሞቢሎችን እንቅስቃሴ ለመገደብ መታሰቡ ተነግሯል፡፡ በከተማው ውስጥ ካሉት ተሽከርካሪዎች ቁጥር አንፃር የግል አውቶሞቢሎች ድርሻ ምን ያህል እንደሆነ፣ የትራንስፖርት ችግር በሰፊው ባለበት ከተማ ውስጥ የግል አውቶሞቢል ተጠቃሚዎችን ችግሩን እንዲያባብሱ የማድረግ አስፈላጊነትን፣ በከተማው ውስጥ ሊኖር ይችላል የሚባለው የአየር ብክለት መጠንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ምን ዓይነት ጥናት ተደርጎባቸዋል? በሥራና መግቢያና መውጫ ሰዓት የግል አውቶሞቢሎች እንቅስቃሴ እንዲገደብ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ከየት አገር በተገኘ ልምድ እንደሆነ ቢገለጽ መልካም ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ግን ልምድ ቢቀሰምም ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ይህ ውሳኔ ጎጂ እንደሆነ ቢታሰብበት ይሻላል፡፡ ሌላው እዚህ ላይ ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ፣ ዜጎች ድንገት በሚተላለፉ ውሳኔዎች ምክንያት የሚደርስባቸው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳት ልዩ ትኩረት ያሻዋል፡፡ ለዚህም ነው ጥንቃቄ የተሞላባቸው ጥናቶች በማድረግ ማቀድ የሚያስፈልገው፡፡ በጥንቃቄ ማቀድና መወሰን ሲቻል ሊከተሉ የሚችሉ ኢኮኖሚዊና ማኅበራዊ ጉዳቶች ይቀንሳሉ፡፡ ውሳኔዎችን የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታና ፍላጎት ሲያገናዝቡ ተቀባይነታቸው ይጨምራል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ መጓዝ ግን የሕዝብ ኑሮን ከማናጋት የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡
መንግሥት የአገርና የሕዝብ አደራ የተሸከመ ትልቅ ተቋም ስለሆነ የአገር ሀብትን እንዴት ማስተዳደር እንዳለበት፣ ኢኮኖሚው ምን ቢደረግ ካለበት የሰቀቀን ሁኔታ ውስጥ መውጣት እንደሚኖርበት፣ ሀብት አባካኝ ከሆኑ ፕሮጀክቶች ይልቅ ፈጣን ዕድገት ሊያመጡ የሚችሉትን እንዴት ማማተር እንዳለበት፣ የውጭ ምንዛሪ ድርቅን ለማስቀረት የሚያስችሉ አማራጮችን የሚቃኝበት፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በማስቀረት ተኪ ምርቶች የሚገኙባቸው ልምዶችን የሚቀስምበት፣ የግሉ ዘርፍ ጤናማ በሆነ ውድድር ሥራውን እያከናወነ ኢኮኖሚውን የሚደግፍበት፣ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች መሠረታዊ ለውጥ የሚያስገኙ ዕድሎች የሚቃኙበትና የመሳሰሉት ኃላፊነቶችን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ በየሙያ መስኩ አገር ሊያግዙ የሚችሉ ባለሙያዎችን አሰባስቦ የአጭር፣ የመካከለኛኛ የረጅም ጊዜ ዕቅዶችን ማውጣት ይኖርበታል፡፡ ዕቅዶቹ አፈጻጸማቸው የሰመረ እንዲሆን ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል ያስፈልጋቸዋል፡፡ በዚህ መሠረት ኃላፊነትን መወጣት ሲችል ውሳኔዎች ችግር ፈቺ ይሆናሉ፡፡
በዚህ ዓለም እያንዳንዱ ችግር መፍትሔ አለው፡፡ መፍትሔ አይገኝለትም ተብሎ የሚተው ምንም ነገር የለም፡፡ ነገር ግን መፍትሔው ችግር ፈቺ እንጂ አባባሽ መሆን እንደማይኖርበት መስማማት ያስፈልጋል፡፡ የመንግሥት የመፍትሔ ሐሳብም ሆነ ውሳኔ በዚህ መሠረት ካልተቃኘ፣ ሕዝብ ሊሸከማቸው ከሚችላቸው ችግሮቹ የባሱ እንደሚከሰቱ ለመረዳት ነብይ መሆን አያስፈልግም፡፡ ‹‹ጫማ ጠበበ ተብሎ እግር አይቆረጥም›› እንደሚባለው ሁሉ፣ ችግር አጋጠመ ተብሎ የባሰ ችግር የሚያመጣ ድርጊት አይፈጸምም፡፡ እንደ ችግሩ መጠን፣ ይዘትና ባህሪ መፍትሔ ለመፈለግ ግን ችሎታና ብቃት ይጠይቃል፡፡ መንግሥትም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው በሙሉ ለብቃትና ለልምድ ዕድል ይስጡ፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነዳጅ ለማስገባት ተግዳሮት ሲፈጥር ለአይረቤ ጉዳዮች የሚባክን ሀብትን መጠበቅ አንዱ ዘዴ ነው፡፡ ለአገር ዕድገትና ለሕዝብ ኑሮ ፋይዳ ለሌላቸው የውጭ ምርቶች የሚባክነው የውጭ ምንዛሪ ቁጥጥር ቢደረግበት፣ ከአንድ የችግር አረንቋ ወደ ሌላው የሚያዘዋውር ውሳኔ ላይ አይደረስም፡፡ የመንግሥት ውሳኔዎች መፍትሔ አመንጪ እንጂ ችግር ፈጣሪ አይሁኑ!