
እኔ የምለዉ የመሠረታዊ ፍላጎቶች እጥረት የምጣኔ ሀብት መንገራገጭ ማሳያ ነው
ቀን: February 4, 2024
በንጉሥ ወዳጅነው
አገራችን ባለፉት አምስት ዓመታት አዲስ ፖለቲካዊ ሥርዓት ለመፍጠር እንቅስቃሴ ስትጀምር በፖለቲከኞቿ መካከል በቂ መግባባት ባለመፈጠሩ በየአካባቢው ግጭት፣ ጦርነትና አለመረጋጋት ሲያጋጥሙ ቆይተዋል፡፡ አሁንም በማጋጠም ላይ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የሕዝቦች መፈናቀልና ሥቃይ፣ የንፁኃን ሞትና እንግልት ብሎም የአገር ሰላም መደፍረስ እያጋጠመ ይገኛል፡፡ መንግሥትም ለልማትና አገራዊ ምጣኔ ሀብት ሊሰጠው የሚገባውን ሀብት፣ አቅምና ትኩረት ወደሰላምና መረጋጋት ማስፈን አዙሮ እየባከነ ይገኛል፡፡
የፖለቲካ ስክነት ማጣትና አገራዊ የጋራና የተናጠል ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ተቋማትን ፈጥኖ በማቆም ወደመነጋገርና መደማመጥ ባለመገባቱ፣ የመከላከያና የፀጥታ ኃይሉን ከፍተኛ አቅም የፈለጉ ሥምሪቶች በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተካሄዱ ይገኛል፡፡ ትናንት በትግራይ፣ አሁን ደግሞ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች እየተካሄዱ ባሉ የእርስ በርስ ጦርነቶች ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት እየደረሰ ለመሆኑ ነብይ መሆን አይጠይቅም፡፡ መጠንቀቅ የሚያስፈልገው ጠባሳው ወደ ነገ አልፎ ችግራችንን እንዳያባብሰው ነው፡፡
የዛሬው ጽሑፌ ትኩረት ግን ስለአገራዊ ደኅንነትም ሆነ የግጭቶቹ መፍትሔዎች ሳይሆን፣ በወቅታዊው አገራዊ ሁኔታና በዓለም አቀፍ ፈተናዎች ጭምር እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት ነው፡፡ በተለይም በከተሞች መሠረታዊ የሚባሉት የመኖሪያ የምግብና ቤትን የመሳሰሉ ፍላጎቶች እጥረት (የዋጋ ንረት) እርስ በርስ ወደ መጨካከንና መበላላት እንዳይወስዱ መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች በወፍ በረር ቅኝት ማድረግ ነው፡፡ በተለይ በታችኛው እርከን የሚታየውን ሀቅ በማሳየት፡፡
በነገራችን ላይ ሰሞኑን የፌዴራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ በጋራና በተናጠል እየወሰዷቸው ባሉ ተከታታይ ዕርምጃዎች (የፖሊስ ማኅበራዊ ድረ ገጾችን ይመለከቷል) በርካታ ሌቦች፣ ገዳይ ዘራፊዎችና የተደራጁ ወንጀለኞች በሕግ ቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው፡፡ ተግባሩ ገና ተጠናክሮ ከቀጠለ የሞባይል፣ የንብረትና የገንዘብ ቅሚያ፣ የተሽከርካሪ ሌብነት፣ የቤት ካርታ ማጭበርበር፣ የመሬት ዘረፋና ውንብድና፣ ሙስና፣ በሥልጣን መባለግ፣ ማጭበርበር መሰል ወንጀሎች በስፋት ተሰምተዋል፡፡
እነዚህ የአገርና የሕዝብ ፈተናዎች ታዲያ በተገቢው መንገድ መፍትሔ እንዲያገኙ በቂ ጥናት ላይ የተመሠረተ ዕርምጃና ሕግ ማስከበር ብቻ ሳይሆን፣ ፈጥኖ አብዛኛው አምራች ኃይል ወደ ሥራና አገራዊ ልማት እንዲገባ ማድረግ፣ በየክልሎችና ነዋሪው በተወለደባቸው አካባቢ ያልተማከሉ የሥራ መስኮችን ማጠናከር፣ ብሎም ከጥገኛ አስተሳሰብ ተላቅቆ በቤተሰብ ድጋፍም ራሱን የሚችል ትውልድ መፍጠር ነው መፍትሔው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡
እንኳንስ በመቶ ሚሊዮኖች ሕዝብ ባለት ደሃዋ አገራችን ይቅርና በየትኛውም የአደገ አገር ቢሆን፣ ሥራ አጡ ሕዝብ ሲበራከት ለቀውስ መንስዔ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ እንደ አገር ምግብና ማረፊያ ለማግኘት ከፍተኛ ችግር ሲገጥም፣ እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት ዋስትና ሲጠፋ ነግዶ፣ አምርቶ፣ የቀን ሥራ ሠርቶ፣ ሕዝብ አገልግሎ የሚኖረው አምራች ኃይል ሲደነቃቀፍና በማይመለከተው አጀንዳ ሁሉ ከተጠመደ ችግሮች እየተባባሱ እንጂ እየተቃለሉ ሊሄዱ አይችሉም፡፡ ስለሆነም አገራዊ ኃላፊነት እንዳለበት መንግሥትና ዜጋ ሁላችንም ጉዳዩን ከልብ አጢነን የመፍትሔው አካል ለመሆን ነው መነሳት ያለብን፡፡
የምጣኔ ሀብቱንና በተለይም የመሠረታዊ ፍላጎቶች እጥረት ለመቅረፍ ቅድሚያ መደረግ ካለበት እንጀምር፡፡ ማንኛውም ዜጋ እንደሚገነዘበው ወደ ተሟላ ልማትና አገራዊ ዕድገት ለመግባት ሰላምና መረጋጋትን ማምጣት ግድ ነው፡፡ ይህን እውነት መተግበር የሚቻለው ደግሞ በኃይልና ሕግ ማስከበር (አንዱ መፍትሔ መሆኑ ቢታወቅም) ብቻ ሳይሆን፣ በተቻለ መጠን በሰጥቶ መቀበልና በፖለቲካ ውይይት ጭምር ለመፍታት ከልብ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ አገራችን ሰፊና ውስብስብ ታሪክ ያለፈች ነች፡፡ ፍላጎቶችንም ብዙና የተለያዩ ናቸው፡፡ ይህን አቅርቦ መገኘትና መደማመጥ ከብልህነትም በላይ አዋቂነት ነው፡፡
በሌላ በኩል በአገር ደረጃ አረረም መረረም በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት መልካም አስተዳደርና ፍትሐዊ ሥርዓት እንዲሰፍን፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበር መትጋት ይኖርበታል፡፡ ከላይ እስከ ታች በሥልጣን ላይ ያሉ አካላት ከሙስናና ብልሹ አሠራር እንዲፀዱ፣ ቢሮክራሲው ከአድሏዊ አደራርና ብልሽት ተላቆ ዜጎችን በፍትሐዊነት የሚያገለግል ማድረግም ግድ ይላል፡፡ በዚህ መንገድ ነው የመሠረታዊ ፍላጎቶች እጥረትን ለማርገብም ሆነ የዕለት ፍላጎቱን ለማግኘት ወደ ተሳሳተ መንገድ እየገባ ያለውን ትውልድ ለማስቆም የሚቻለው የሚል እምነት የብዙዎች ነው፡፡ ቀዳሚው የአገራችን የመሠረታዊ ፍላጎት ችግር መኖሪያ ቤት ለአብነት ያህል ብንወስድ፣ ዋናዋ መዲናችን አዲስ አበባ በዓለም የመኖሪያ ቤት ዋጋ ውድ ከሆነባቸው ከተሞች በሦስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ከ‹‹ቢዝነስ ኢንሳይደር አፍሪካ›› ሪፖርት ሰምተናል፡፡ እንደ ሪፖርቱ ኢትዮጵያ ለዜጎቿ በውድ ዋጋ የምታቀርብ፣ ከአፍሪካ በቀዳሚነት በውድ ዋጋ ቤት ከምታቀርበው ካሜሩን ቀጥላ ሁለተኛዋ ውድ ቤት አቅራቢ አገር ያደረጋት፣ እ.ኤ.አ. በ2024 እስከ 2,100 ዶላር በሚደርስ የነፍስ ወከፍ ገቢ፣ በመሀል ከተማ በካሬ እስከ ሁለት ሺሕ ዶላር በዳርቻዎችም 1,500 ዶላር በሚደርስ ዋጋ የሚሸጥባት በማለት ነው፡፡
ይህ እንዴትና ለምን ሆነ ብሎ ለጠየቀ ሰው መሬት ጠፍቶ ወይም የግንባታ ማቴሪያሉ መወደዱ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ነዋሪ ሁሉም በሚሠራበት አካባቢ ባለው አቅም ቤት ሠርቶ/ገዝቶ መኖር ባለመቻሉ፣ መንግሥት በሕጋዊ መንገድ የቤት መሥሪያ ቦታን እያቀረበ ባለመሆኑ፣ ቤት የመሥራት አቅም የሌላቸውን ወገኖች የሚደግፍ መርሐ ግብር በመዳከሙ፣ ብሎም በርከት ያሉ ዝጎች ቤት ሠርተው ለዓመታት የኖሩባቸው ሥፋራዎች በሚፈለገው መንገድ ወደ ሕጋዊነት ከመቀየር ይልቅ፣ እንዲፈርሱና ሰዎቹም እንዲፈናቀሉ በመደረጋቸው የሚሉ መልሶችን ማግኘት ይቻላል፡፡
ከቀደመው መንግሥት አንስቶ በሚስተዋለው የመልካም አስተዳደር ብልሽት ምክንያት ደግሞ በመሬት ላይ መጠቀምና መወሰን እየቻሉ ያሉት ከባለሥልጣናት ጋር የሚቀራረቡ ጥገኛ ባለሀብቶችና የመዋቅሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ይህን አገራዊ ቀውስ ለመግታት ከተሃድሶው ጀምሮ የመሬት ይዞታ አስተዳደር፣ የሰነድ አልባ ይዞታዎችና ችግሮቻቸው፣ ግንባታና ፈቃድ፣ ካሳና ምትክ፣ የመንገድና ትራንስፖርት ችግሮች፣ የፍትሕ፣ የወሳኝ ኩነቶች፣ የውኃና ፍሳሽ፣ የከተማ ፅዳት፣ ወዘተ ዘርፎች በስፋት ሲፈተሹና ሲገመገሙ ቆይተዋል፡፡ በውስጡ የማንነትና የዴሞግራፊ አጀንዳ ስላለበት ግን በቂ መሻሻል እንዳልተገኘ ገለልተኛ ተቋማት ጭምር አስረድተዋል፡፡
በእርግጥ መልከ ብዙና ውስብስብ የሆኑ መንግሥታዊና ማኅበራዊ ችግሮችን የሚያጠፋ ሥር ነቀል ለውጥ በአንድ ጀንበር እንደማይመጣ የታወቀ ነው፡፡ መንግሥት ፋታ አግኝቶ ስለልማትና ፍትሐዊነት ጠበቅ ያለ ንቅናቄ ቢጀምር ግን ለውጥ ሊያመጣ ይችል ነበር፡፡ ሕዝቡም ሙሉ ተሳትፎ እያደረገባቸው ‹‹ችግር›› ተብለው የተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ቢመክርና ቢታገል ውጤት መምጣቱ አይቀርም፡፡ ሕዝቡን (ደሃውንም ሀብታሙንም) ያስመረሩ፣ የሕዝቡን ሆድ ያሻከሩ፣ መንግሥትና ሕዝብን የሚያቃቅሩ፣ የሕዝቡን የነገ ተስፋ የሚቦረቡሩ፣ የሕዝቡን የትዕግሥት ገደብ የሚገዳደሩ መሠረታዊ ችግሮች ቢያንስ እየተቃለሉ እንዲሄዱ ግን አሁንም ልዩ ትኩረት መስጠት ያሻል፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ዋነኛውና ግምባር ቀደሙ ችግር የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመሆኑ የሕዝቡ ጥያቄ መበርታት ብቻ ሳይሆን፣ ከላይ የጠቀስነው የሰሞኑ ጥናት ያረጋግጣል፡፡ በእርግጥ መንግሥትና የከተማው አስተዳደር መጠኑ በቂ ባይሆንም የሕዝቡን የቤት ችግር (በተለይ ለዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍል) ለመፍታት የሚያደርጉትን ተግባር በሚዛኑ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ጅምሩን ሳያንቋሽሹ እንዲጠናከርና በፍትሐዊነት ለሕዝቡ እንዲደርስ መትጋትም ከነዋሪ ይጠበቃል፡፡ ግን ጅምሩ ከተከማቸው የቤት ፍላጎትና ከሕዝቡ ብዛት አንፃር በቂ አይደለም፡፡
ዛሬም ድረስ የቤት ችግሩን ሩብ ያህል እንኳ ለመፍታት አልተቻለም የሚለው ትችት መነሻም ይኼው እውነታ ነው፡፡ እናም በአንድ በኩል ማኅበራት፣ ቤት አልባ የግል ሠሪዎች፣ እንዲሁም አቅም ያላቸው በሊዝ ገዝተው የሚገነቡ አካላት ቤት እንዲሠሩ የጠራ የፖሊሲና የተግባር ዕርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ የሪል ስቴትና የመንግሥት ቤቶች ኮርፖሬሽን ግንባታና የማስተላለፍ ሥራ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ሊሻሻጥ የሚችለው፣ ሥራዎች ቢያንስ የኢሕአዴጉ አስተዳደር ያህል እንኳን ተፍታተውና ተቀናጅተው መተግበር ሲችሉ ነው፡፡ በቀጣይነት የቤት ኪራይ ዋጋም ቢሆን ጋብ እያለ የሚሄደው በክልከላ ሳይሆን፣ ቤት እየተገነባ ፍላጎትና አቅርቦት እየተጣጣመ ሲሄድ ነውና፡፡
በነገራችን ላይ የቤት ኪራይ ነገር በተለይ በአዲስ አበባ በርካታ ብልሽቶች ያሉበት መሠረታዊ ፍላጎት ነው፡፡ መጀመሪያ የቤት ኪራይ ከሕዝቡ ኑሮ ጋር የማይመጣጠንና ውድ ነው፡፡ ሲቀጥል የሚከራዩ የግለሰብ ቤቶች የአሠራር ስታንዳርድ የላቸውም፡፡ በጭራሮ ግድግዳና በጭቃ ምርጊት የቆሙ መታጠቢያና መፀዳጃ የሌላቸው ሁሉ በሺሕ ብሮች ይከራያሉ፡፡ ቤቶቹ ከተሠሩ እስከ 50 ዓመት የሚደርስ ዕድሜ ያስቆጠሩም አሉ፡፡ ቢያንስ በአሥር ዓመት አንዴ እንኳ ዕድሳት ተደርጎላቸው አያውቅም፡፡ የማብሰያ ቦታ (ኩሽና) አይታሰብም፡፡ ይኼ ደግሞ በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ሲታይ የድህነት መገለጫ ነው፡፡
በዚህ ላይ አንዳንድ አከራዮች በየቀኑ ለተከራዮች የሚሰጧቸው ‹‹የውኃ ቀጠነ›› መመርያዎች የተከራዮችን ሰብዓዊ መብቶች የሚዳፈሩ ብቻ ሳይሆኑ የሚፃረሩ ጭምር ናቸው፡፡ የራስ ወዳድነትና የስግብግብነት ልማድ እየፈጠሩም ነው፡፡ ባልታሰበ ቀንና ባልተጠበቀ ሁኔታ ተከራዮች ‹‹ቤቱን ልቀቁ›› የሚባሉበት አሠራር በሕገወጥ ደላሎች ጭምር ሲባባስ ተከራይ እየተማረረ ነው፡፡ አሁንም በርካታ ተከራዮች ምንም ዋስትና በሌለው ሁኔታ ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡ ሁልጊዜ በሥጋት እንደተሸማቀቁ የሚኖሩ ብቸኛ ፍጡራን ቢኖሩ ተከራዮች ናቸው ማለትም ይቻላል፡፡ ይህንንም ቢሆን ከመንግሥት በላይ የሚያስተካክለው አካል የለም፡፡
ማናችንም ብንሆን ቤቶች ስታንዳርድ እንዲኖራቸው እንፈልጋለን፡፡ ምን ዓይነት ቤት፣ ከምን ግብዓት የተሠራ ቤት፣ በምን ያህል ብር የኪራይ መጠን (ጣሪያ) እንደሚከራይ አቅጣጫ የሚሰጥ ሕግ እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡ በሥርዓትና በአግባብ ውል ተዋውለን የአከራይ ተከራይ ግንኙነታችን እንዲመሠረት እንፈልጋለን፡፡ አከራዮች የሚያከራዩት ቤት ውል በስንት ጊዜ እንደሚታደስ፣ ኪራይ ስለሚጨመርበት ሁኔታ፣ ተከራዩ ከተከራየው ቤት ስለሚለቅበት አግባብ፣ የአሠራር ደንብ እንዲዘረጋልን እንፈልጋለን፡፡ ይህ ሁሉ አገራዊ ገጽታ ተላብሶ በሥርዓት መመራት አለበት፣ የግድም ነው፡፡
በመሠረቱ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት የኮንዶሚንየም ቤቶችን እየሠራ የቤት ችግርን ለማቃለል ከአሥር ዓመታት ለበለጠ ጊዜ ያደረገውን ጥረት ከእነ ጉድለቱም ቢሆን በበጎ ማንሳት ስህተት አይደለም፡፡ አሁን ደግሞ የኮንዶሚንየም ቤቶች ግንባታ ከመቆሙ ባሻገር ተገንብተው ማጠናቀቂያ (ፊኒሺንግ) የቀራቸውን ቤቶች፣ ጨርሶ ለሕዝብ ጥቅም ማዋል ላይ እንኳን በርካታ ተግዳሮቶች ተሰንቅረዋል፡፡ ተገንብተው ሰው ያልገባባቸው ሕንፃዎችም የሚያስቆጩ ሆነው ዓመታትን ቀጥለዋል፡፡ እናም አማራጭ መፍትሔ ማማተር ብልህነት ነው፡፡
ሁለተኛው መሠረታዊ ችግር የምግብ ጉዳይ
ለዕለት ጉርስ ጥሬና ድንችም ጎርሶ ይዋላል፡፡ ዋናው ጎን ማሳረፊያ ነው ይባላል፡፡ ቢሆንም ካለምግብ መኖርም የሚቻል አይደለም፡፡ ለግንዛቤ መነሻ ይሆነን ዘንድ ስለምግብ ስናነሳ ስለሥጋ ምግቦች ወይም ስለተመጣጠኑ ምግቦች እየተነጋገርን አለመሆኑ ልብ ይባልልን፡፡ እያወራን ያለነው በከተሞች (በገጠርም ያው ነው) በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኘው አብዛኛው ሰው ሕይወቱን ለማቆየት ያህል ብቻ ስለሚመገባቸውና ዋጋቸው ቀላል የሆኑ፣ በግማሽ እንጀራ ደረጃ፣ ግማሽ ማካሮኒ፣ ግማሽ አቡካዶ በዳቦ፣ ሳምቡሳና ፓስቲ ደረጃ ያሉትን ምግብ ተብዬ የዕለት ቀለቦች ነው፡፡
የተወሰኑ ምልከታዎችን (ቅኝቶችን) አድርጌያለሁ፡፡ ለምሳሌ በታችኛው ሠፈር በቅርቡ እንዳስተዋልኩት ሽሮ ፈሰስ በሙሉ እንጀራና በግማሽ እንጀራ (ሙሉና ግማሽ) የሚባል ደረጃ መጀመሩን አስተውያለሁ፡፡ የዛሬ ዓመት ገደማ ‹‹ሽሮ በሙሉ እንጀራ›› ዋጋው 50 ብር ነበር፡፡ ሽሮ በግማሽ እንጀራ ደግሞ 35 ብር ነበር አሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ግን ‹‹ሽሮ በሙሉ እንጀራ›› 80/90 ብር ሲሆን፣ ‹‹በግማሽ እንጀራ›› 60 ብር ሆኗል፡፡ ለነገሩ አንድ ደረቅ እንጀራ እንኳን 20 ብር፣ ሦስትና አራት ጊዜ የምትጎረሰው ዳቦም እስከ አሥር ብር (ያውም በመንግሥት ድጎማም ተጋግሮ) ገብቷል፡፡ የነገሩ መክፋት ደግሞ ዝቅተኛ የቀን ገቢ ያላቸው የጉልበት ሠራተኞች ሳይቀሩ ሥራ አጥነታቸው መብዝቱ፣ ዝቅተኛ ተቀጣሪውም ቢሆን የቀን ገቢው የዕለት ጉርሱን ለመሸፈን እያዳገተው መሆኑን በርካቶች ይናገራሉ (በአዲስ አበባ በርካታ አካባቢዎች ከተቀቀለ ድንች የሚሠራ እርጥብ የተባለ ምግብ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው)፡፡
በእርግጥ በአገራችን በተለይ በከተሞች በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ለመጣው የዋጋ ግሽበት የሽንኩርትና ቲማትምን የመሰሉ አትክልቶች ዋጋ መናር፣ ጥራጥሬ፣ ዘይት፣ በርበሬ፣ ሽሮና ቅመማ ቅመም ዋጋ ተሰቅሎ መቅረት፣ እንደ ዕንቁላል፣ ቅቤና ሥጋ ዓይነቶቹም ለደሃው ብርቅ ግብዓቶች መሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ለነገሩ የሰብል እህልን ጨምሮ ለተፈጠረው የዋጋ ግሽበትና አማራጭና ሸማች በቀላሉና በተሳለጠ መንገድ አለመገናኘታቸው ችግሩን አባብሶታል፡፡
በክልሎች በተለይም ግጭትና ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ደግሞ የምግብ ዋስትና ችግሩ ተባብሶ በመቀጠሉ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለምግብ እጥረትና ወደ ከተማ ተፈናቅሎ በልመና ለመተዳደር ተዳርገዋል፡፡ በዚህ ላይ በተለያዩ ሰበባ ሰበቦች ረጅ አገሮችና ድርጅቶች የተለመደውን ዕገዝ ማድረግ ባለመፈለጋቸው ችግሩ በመንግሥትና በሕዝብ ጫንቃ ላይ በመውደቁ ሥጋቱን አባብሶታል፡፡
ከላይ በመንደርደሪያው እንደጠቀስነው ይህ በልቶ የማደር ችግር መባባሱ ደግሞ፣ ማጅራት መቺና በውንብድና ሕገወጥ ተግባር ላይ እየተሠማራ ያለውን እንዳያበራክተው ያሠጋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች እየታየ ያለው ንጥቂያ፣ መንገድ እየዘጉ መዝረፍና እስከ ግድያ የሚደርስ ውንብድና መፈጸም (በቅርቡ ከአዲስ አበባ ወደ አርባ ምንጭ በመጓዝ ላይ እንዳሉ በዝዋይና አዳሚ ቱሉ መሀል አሸናፊ በቀለ የተባለ የሦስት ልጆች አባትና የአርባ ምንጭ ከተማ ሾፌርና ረዳቱ መንገድ በቆረጡ ነፍሰ በላዎች በግፍ በስለት ተወግተው ሕይወታቸው ማለፉ ብቻ ሳይሆን፣ መኪናቸውንም ከእነ ጫነው ሸቀጥ መዘረፋቸውን ከአካባቢው ሰምተናል)፡፡ ፖለቲካዊ ፍላጎትን በኃይል ለመጫን ሳይሆን ነጥቆ የመኖር ጉጉት የወለደው ወንጀል እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡
ከቅርብ ጊዘ ወዲህ ደግሞ በየከተሞቹ እየተባባሰ እንደሚታየው ገንዳ ውስጥ የተጣሉ የምግብ ዘር ፈላልገው ካገኙ የሚበሉ በርክተዋል፡፡ በየቤተ ክርስቲያኑና በመስጊዶች ከሚውሉ ገዳዮች ላይ በገንዘብ ገዝተው በፌስታል ቋጥረው ከጓደኞቻቸው ጋር የሚበሉ ወጣቶችን ማየትም ብርቅ አይደለም፡፡ እውነት ለመናገር የለውጡ መንግሥት በተለይ በአዲስ አበባ በማዕድ ማጋራትና አቅመ ደካሞችና ተማሪዎችን ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ለመመገብ እያደረገ ባለው ጥረት በመጠኑም ቢሆን ችግሩን ማስተንፈሱ እንጂ፣ ችግሩ ከዚህም በላይ በተባባሰ ነበር፡፡
በአገራችን በምግብ እጥረትና ውድነት ረገድ ጥናትና ምርምር ቢደረግበት ብዙ መረጃ የያዘ ወፍራም ሰነድ እንደሚወጣው አያጠራጥርም፡፡ እዚህ ላይ ሳይጠቀስ ማለፍ የሌለበት የሕዝቡ የኖረው የመረዳዳትና የመተዛዘን ባህልም እንደቀጠለ መሆኑ ነው፡፡ መጠናከር ያለበት ሌላው ጥረት ደግሞ በተለይ ትልልቅ ሆቴሎች፣ ሱፐር ማርኬቶች፣ የምግብ አምራች ድርጅቶች፣ ወዘተ ያሉ ተቋማትም ከምርታቸውና ተረፈ ምርታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ለገበያ ከሚያቀርቡትም የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ማለቂያ ሳይደርስ ለተቸገሩ ወገኖች የሚያካፍሉበት ዘዴ መፈጠር ይኖርበታል (እዚህ ላይ ደቡብ አፍሪካና ኬንያ ጥሩ ተሞክሮ እንዳላቸው ይነገራል)፡፡
የምግብ እጥረትና ውድነት ነገር ሲነሳ አዲስ አበባን ጨምሮ በርከት ባሉ ከተሞች ጉራማይሌ እውነታዎች እንዳሉ መዘንጋት አይገባም፡፡ በእርግጥ በርከት ባሉ ሥጋ ቤቶችና ሆቴሎች ለአንድ ኪሎ ሥጋ ከሁለት ሺሕ ብር በላይ እየከፈሉ በወረፋ የሚቆርጡና ጠርሙስ ውስኪ እስከ 30 ሺሕ ብር ከፍለው የሚራጩም አሉ፡፡ ይህ ሁኔታ የብዙኃኑን አገራዊ ሁኔታ ባያሳይም አስረሽ ምቺውም ቀጥሏል፡፡ የመንግሥት አንዱ ኃላፊነት ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ማምጣት በመሆኑ ልዩነቱን ማየት ተገቢ ይሆናል፡፡
እዘህ ላይ ወጥነትና መስፋፋት ቢቀረውም መንግሥት (በተለይ የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳዳር) የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ብዙ ድጎማዎችን እያደረገ መሆኑ አይካድም፡፡ ለምሳሌ በየወረዳው ‹‹የሕዝብ መዝናኛ›› በሚባሉ የኅብረት ቡና ቤቶች ያሉ የቀበሌ ሥጋ ቤቶች ለሸማቾች ‹‹ወደ ቤት የሚሄድ›› የሚባለውን ሥጋ በኪሎ እስከ 600 ብር፣ እንዲሁም ‹‹እዚያው የሚበላ›› የሆነውን ሥጋ ደግሞ በኪሎ 700 ብር ድረስ ይሸጣል፡፡ በሰንበት ገበያ የሚቀርቡ አስቤዛዎችም አሉ፡፡ ዋጋቸው ግን እምብዛም ቅናሽ የሚባል አይደለም፡፡
በመጨረሻም ላነሳኋቸው ሁለት መሠረታዊ ችግሮች የሚሆን አንድና አንድ የሆነ መፍትሔ ላይኖር ይችላል፡፡ ግን በማንኛውም ሰው እንደሚታመነው የአገር ሰላምና ደኅንነትን ማረጋገጥ፣ ምርታማነትን የሚጨምሩ ጥረቶችን ማጠናከር፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን ማበረታትና ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብትን ዋስታና መስጠት እጅግ ወሳኝ ዕርምጃዎች ናቸው፡፡
የኑሮ ውድነትን በተለይ በወጣቱ ኃይል ላይ ያለውን የምግብ ችግር ለመፍታት፣ ወጣቱን ከሥራ አጥነት የሚያላቅቁ የልማት ፕሮጀክቶችን አጠናክሮና አፋጥኖ መፍትሔ ሰጪ እንዲሆኑ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ እነዚህም መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና ሕዝቡም ጭምር ሊጨነቁባቸው የሚገቡ ቁምነገሮች ናቸው፡፡
ሰላም ለአገራችን!!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው nwodaj@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡