EthiopianReporter.com 

እኔ የምለዉ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ዓይጦች የበጣጠቁትን የእንጀራ መሶብ የመጠገን ታሪካዊ እንቅስቃሴ ነው

አንባቢ

ቀን: February 4, 2024

በሁሴን አዳል መሐመድ (ዶ/ር)

 በዚህ ጽሑፍ ኢትዮጵያ የጠረፍ ግዛቶቿን (Coastline Provinces) ስታጣ የባህር በር እንዳጣች፣ የተገላቢጦሽ ቀሪውን የኢትዮጵያ ግዛት የሚመኙ ጠላቶች እንደተከሰቱ፣ ዘመን የማያደበዝዘው ከኢትዮጵያ ጋር የመኖር የጠረፍ ግዛቶች ሕዝብ ፅኑ ፍላጎት፣ የእንግሊዝ የቅኝ ግዛት አስተዳደር ተንኮል፣ በቅርቡ የተደረገው የኢትዮጵያ-ሶማሌላንድ ስምምነት ያስነሳው ሞገድና የተነሳበት አቅጣጫ፣ ስምምነቱ የሚያስከትላቸው መልስ የሚሹ ጥያቄዎች ጥቆማ በአጭሩ ቀርቧል፡፡  የተጠቀሰው የዘመን አቆጣጠር እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር (እ.ኤ.አ.) ነው፡፡

 በዘመን ቅደም ተከተል የቱርክ ኦቶማን ኢምፓየር፣ ግብፅ፣ ሦስቱ  የአውሮፓ ኃያላን አገሮች (ጣሊያን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ) በምሥራቅ አፍሪካ ህንድ ውቅያኖስ ድረስ የቅኝ ግዛት ለማስፋፋት በመራወጥ ከምሥራቅ ጫፍ ከህንድ ውቅያኖስ ጀምሮ እስከ ሰሜን ጫፍ ድረስ ይዘልቅ የነበረውን የኢትዮጵያ የባህር ጠረፍ የግዛት ይዞታ ቀይረውታል፡፡ በአገር ውስጥ በመሣፍንቱ መካከል የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነትና ኅብረት ማጣት፣ በአንፃሩም ለዙፋኑ ብቻ በተደረገ ትንቅንቅ የባህር ጠረፍ ግዛቶች ቸል መባል ጠረፎቹ በዝግምታ በውጭ ኃይል መያዛቸው፣ አገሪቱም የጥንት የባህር ወደብ ይዞታዎቿን ማጣት ግድ ሆኗል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአንድ ብሔረሰብ ሕዝብን እስከ አምስት በሚደርስ የተለያየ አገር ከፋፍሎ በድንበር በመለያየት ኢትዮጵያን የዘመን ተሻጋሪ የፖለቲካ ችግር ሰለባ በማድረግ፣ ጊዜዋን ሁልጊዜ በጦርነት የምታሳልፍና በኢኮኖሚ ዕድገት ኋላቀር አገር አድርገዋታል፡፡  

በ1896 ከጣሊያን ጋር በተደረገው የዓድዋ ጦርነት ማግሥት ኢትዮጵያ ተጨማሪ አቅም አግኝታ ጣሊያንን እግር ለእግር ተከታትላ ከአካባቢው ባለማስለቀቋ የመረብ ምላሽ (ኤርትራ) ግዛቷ መልሳ ከእናት አገሯ ጋር  እስከ ተቀላቀለችበት በ1952 ድረስ፣ ለ60 ዓመታት ያህል በጣሊያን ቅኝ ግዛት ቀጥሎም በእንግሊዝ የሞግዚት አስተዳደር ሥር ኖራለች፡፡ በፊት  “መረብ ምላሽ”/”ምድሪ ባህሪ” እየተባለ ይጠራ የነበረው የኢትዮጵያ ግዛት በጣሊያን የቅኝ ግዛት አስተዳደር ሥር እንደ ወደቀ፡፡ “ኤርትራ” በሚባል የባዕድ ስም እየተጠራ ቆይቶ በ1993 ዓ.ም. እንደገና ከኢትዮጵያ ተነጥሎ ራሱን የቻለ ግዛት ቢሆንም፣ በዚሁ የባዕድ ስም መጠራት ቀጥሏል፡፡ ከኤርትራ በተጨማሪ ደቡብ ሶማሊያ፣ ሰሜን ሶማሊያና ጂቡቲ በቅደም ተከተላቸው የሦስቱ አውሮፓ አገሮች ቅኝ ግዛቶች ሆነው ቆይተዋል፡፡ በኋላም ጂቡቲ በፈረንሣይ የሞግዚት አስተዳደር ለረዥም ጊዜ ቆየች፡፡ በመሆኑም ከራስ ካሳር እስከ ባብኤል መንደብ ያለው ርዝመቱ  ከ1,000 ኪሎ ሜትር በላይ የቀይ ባህር ጠረፍ ከሶማሌና ከጂቡቲ የህንድ ውቅያኖስ ጠረፍ ጋር ተደምሮ፣ ጥንት የኢትዮጵያ የነበረ ረዥሙ የባህር ጠረፍ ዓይጦች የበጣጠቁት የእንጀራ መሶብ ሆኖ ቀረ፡፡ ዓይጦቹ እነማን ናቸው? የመሶብ እንጀራውስ ማን ነው?

ቱርኮች ሲዳከሙ ግብፅ እ.ኤ.አ. በ1875 እና በ1886 በሰሜን ኢትዮጵያ ኤርትራ ውስጥ ከአፄ ዮሐንስ ጋር ተዋግታ ሳይቀናት ሲቀር፣  በምሥራቅ በኩል ሐረርጌን ይዛ ቆይታ አሚር አብዱላሂን ለአካባቢው ሾማ ለቃ ወጣች፡፡ አፄ ምኒልክ በታኅሳስ ወር 1886 ሐረር ዘምተው ጨለንቆ ላይ አሚሩን ድል አድርገው የቅድመ አያቶቻቸው ግዛት የሆነውን የሐረርጌን ግዛት አስከብረው መልሰው ያዙ፡፡ ምኒልክ ይህንኑ ለጣሊያኑ ንጉሥ ኡምቤርቶ እንዲያውቁላቸው ደብዳቤ ጻፉ፡፡ አፄ ምኒልክ ዓድዋ በጣሊያን ላይ የተቀዳጁት ድል በአካባቢው የነበረውን የኃይል ሚዛን ስላናጋው፣ በሁኔታው የተደናገጠችው እንግሊዝ በቅኝ ግዛት በያዘችው ሰሜን ሶማሊያና የኢትዮጵያ ግዛት በሆነው የኦጋዴን ጠረፍ የድንበር ተሻጋሪ ግጦሽ ጉዳይ የፕሮቴክቶሬት ስምምነት ለመፈራረም (በኋላ ስምምነቱን በማፍረስ ኡጋዴን ጭምር ብትይዝም)፣ በ1897 ሬነል ሩድ የተባለ መልዕክተኛ ደብዳቤ አስይዛ አዲስ አበባ በላከችበት ወቅት መልዕክተኛው አፄ ምኒልክ ዘንድ ሲቀርብ ዛሬ ሞቃዲሾ በመባል የሚታወቀው አካባቢ በፊት “ቤናድር”  ተብሎ ይጠራ የነበረ አንዱ የኢትዮጵያ ግዛት እንደ ነበረ በማስረዳት፣ ‹‹አምላክ ካለና ዕድሜና ጥንካሬ ካገኘሁ የጥንቱን የኢትዮጵያን ወሰን ከህንድ ውቅያኖስ እስከ ካርቱም ያለውን ሳላስመልስ አልቀርም›› ሲሉ ገልጸውለታል፡፡  ለንግሥት ቪክቶሪያ እንዲያቀርብላቸውም ፍላጎታቸውንና ምኞታቸውን የሚገልጽ  ደብዳቤ አስይዘው ልከውታል፡፡

የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት በነበረው ሰሜን ሶማሊያ የሚኖሩ ይስሐቅ፣ ዱልበሃንቲ፣ ማሊንጉር፣ ገደቡርሲ፣ ሃበር አወል የተባሉ ጎሳዎች የዘር ግንድ መሠረት ከኢትዮጵያ መሆኑን ስለሚያምኑ የቅኝ ገዥዎችን አስተዳደር በመጥላት ሰሚ ባያገኙም፣ ከኢትዮጵያ ጋር ለመቀላቀል በየጊዜው ጥያቄ ሲያቀርቡ ኖረዋል፡፡ የዚያድ ባሬ የታላቋ ሶማሊያ ህልም መና ቀርቶ ሶማሊያ መንግሥት-አልባ አገር ስትሆን ሰሜን ሱማሌዎች ከደቡብ ሶማሊያ (ሞቃዲሾ) በመለየት ዕውቅና እየተጠባበቀ ያለ መንግሥት (Defacto State) መሥርተው ለብቻቸው በመኖር ከደቡብ ሶማሊያ ጋር ያላቸውን የልብ መራራቅ አስመስክረዋል፡፡

የጣሊያን ቅኝ ግዛት ከነበረው ከደቡብ ሶማሊያ መጀርቲና፣ መሪሃና (የዚያድ ባሬ ጎሳ)፣ ሃበርጊደር፣ አዲገሌ፣ ዩኒስ የሚባሉ ጎሳዎች ከ1935 ጀምሮ በየጊዜው እየፈለሱ ኡጋዴ በመግባት ሠፈሩ፡፡ ጣሊያን ተሸንፎ ሲወጣ ኦጋዴን፣ ሰሜኑና ደቡቡ  ሶማሊያ በእንግሊዝ ወታደራዊ የሞግዚት አስተዳደር ሥር ሲሆን የአገሩና የመሬቱ ባለቤት የሆኑት ኡጋደኖች (ኢሳቅና ዱልበሃንቲ) ያጣበቧቸው ሰፋሪዎቹ ወደ መጡበት እንዲመለሱ ሲጠይቁ ኖረዋል፡፡ የእንግሊዝ መንግሥት የመስፋፋት ዓላማውን ዕውን ለማድረግ የተንኮል ሴራውን ሲያውጠነጥን ስለነበረ የመጀርቲኖችና መሪሃኖች በአካባቢው መኖር አስፈላጊ ሆኖ ታየው፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍፃሜ በኋላ በእንግሊዝ ወታደራዊ አስተዳደር ሥር የቆየው የኦጋዴን ግዛት ለኢትዮጵያ ከተመለሰ ጀምሮ፣ ኦጋዴኖች በመጀርቲኖችና በመሪሃኖች የተያዘው መሬታቸው እንዲለቀቅላቸው ለአፄ ኃይለ ሥላሴ አስተዳደር ደጋግመው እያመለከቱ ምንም ውሳኔ ሳያገኙ ቀረ፡፡

ከጦርነቱ በኋላ ስለሶማሊያ ጉዳይ በተባበሩት መንግሥት ድርጅት በተደረገው ውይይት ላይ የሶማሊያን ሕዝብ ከኢትዮጵያ ጋር የመቀላቀል ፍላጎትና የኢትዮጵያን የጥንት ግዛት የታሪክ ማስረጃ በማቅረብ፣ የሶማሊያ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን መብቱ እንዲረጋገጥለት የንጉሠ ነገሥቱ ወቅት ኢትዮጵያ ጥያቄ አቅርባለች፡፡ የሞግዚት አስተዳደሯ ወቅት ተዘግቶ እንግሊዝ አካባቢውን ለቃ ስትወጣ  በተንኮል የተከለችው መርዘኛ “የታላቋ ሶማሊያ” አጀንዳ የግዛት አንድነቷን የሚቃረን በመሆኑ ኢትዮጵያ በጥብቅ ብትቃወምም፣ በ1960 ሶማሊያ ራሷን ማስተዳደር ከጀመረችበት የመጀመሪያው የሶማሊያ ፕሬዚዳንት አደን አብደላ ኡስማን ጀምሮ እስከ ዚያድ ባሬ ምናልባትም እስካሁን ድረስ የታላቋ ሶማሊያ ጥያቄን ሲያላዝኑ ኖረዋል፡፡ በ1947 በእንግሊዞች ግፊት ልዩ ልዩ ስም በመስጠት ኦጋዴንን የሚገነጥሉ ሶማሌ ዩዝ ሊግ (SYL)፣ ናሽናል ዩኒቲ ፍሮንት (NUF)፣ በመቀጠልም ዚያድ ባሬ ከታማኝ ወታደሮቹ መካከል መልምሎ የሶማሊያ ነፃ አውጪ ድርጅት (SLF) የሚል ስም ሽፋን በመስጠት፣ እንዲሁም በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ሥፍራ ተበታትነው ከሚኖሩ የገሪ ዲጎዲያ ጎሳ ወጣቶች  “የሶማሌ አቦ” በሚል መጠሪያ በማደራጀት ለታላቋ ሶማሊያ እንዲታገሉ ጥረት አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያን ፊት ለፊት በጦርነት ለመግጠም ምቹ አጋጣሚ እየጠበቀች በ1960 በእነ ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግሥት በተሞከረ ማግሥት፣ በ1974 አብዮት በተቀጣጠለ ማግሥት በ1976 የእናት ጡት ነካሾች ከሆኑ የውስጥ ባንዳዎች ጋር በመቀናጀት ከኢትዮጵያ ጋር ተከታታይ መደበኛ ጦርነት አካሂደዋል፡፡ “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚል ወታደራዊ ስትራቴጂ የኢትዮጵያን ኃይል ከፋፍሎ በማዳከም ግባቸውን ለማሳካት ሻዕቢያ፣ ወያኔና ኦነግ ከሶማሊያ መንግሥት ጎን ተሠልፈዋል፡፡ የሶማሊያ መንግሥት የተማሩ ሆዳም የኦጋዴን ተወላጆችን በሥልጣንና በሀብት እያማለለ በማስኮብለል በመሣሪያነት ተጠቅሟል፡፡ ሞቃዲሾና ሐርጌሳ የሬዲዮ ጣቢያ በማቋቋም ሰፊ የፕሮፓጋንዳ ቅስቀሳ አድርጓል፡፡ ግን የሶማሊያ የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ ዛሬ የምናየው ነው፡፡  

የሞቃዲሾ  መንግሥት ይህንን ሁሉ ጥረት ቢያደርግም የሰሜን ሶማሊያ ጎሳዎች ‹‹ከሞቃዲሾ መንግሥት ጋር መኖር አንፈልግም፣ ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ጋር ሆነን በአንድ ሰንደቅ ዓላማ ሥር መኖር እንፈልጋለን›› በማለታቸው የሞቃዲሾ አስተዳደር የኃይል ዕርምጃ በመውሰድ ሁኔታውን ማቀዝቀዙ በታሪክ ገጽ ተመዝግቧል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከሰሜን ሶማሊያ በኩል የሚታየው ከኢትዮጵያ ጋር የመቀራረብ ዝንባሌ በአውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎችና በየጊዜው በተቀያየሩ ተስፈኛ የሶማሊያ መሪዎች ታፍኖ የቆየ የሕዝብ ተፈጥሯዊ ፍላጎት መግለጫ ነው፡፡ በ1950 ዓ.ም. ሁለቱ ሶማሌዎች በሞግዚት አስተዳደር ሥር፣ በኋላም በ1960 ዓ.ም. በሶማሊያ መንግሥትነት ቢታወቁም፣ ጂቡቲን ጨምሮ ሦስቱም ግዛቶች ጥንት የኢትዮጵያ አካል የነበሩ የኢትዮጵያ የጠፉ ክፍላተ አገሮች (Lost Provinces) ናቸው፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኤርትራን ወደ እናት አገሯ ለማስመለስ ያደረጉትን ጥረት ያህል ዕድሜና ጥንካሬ አግኝተው እነዚህ የጠፉ ግዛቶች እንዲመለሱ ቢያደርጉ ኖሮ፣ አሁን ያለው ሁኔታ የተለየ ገጽታ በነበረው፣ አሁን ላለው ትውልድም የተንከባለለ የቤት ሥራ ባልሆነም ነበር፡፡  

ከላይ በርዕሱ ወደ ተጠቀሰው ምሥለት (Analogy) ስመለስ ዓይጦቹ አገራችን ኢትዮጵያ ከባህርና ውቅያኖስ ጋር የምትዋሰንባቸውን ጠረፎች ከግዛቷ ላይ ተበጣጥቀው በመከፋፈል፣ ኢትዮጵያን የባህር ወደብ ያሳጧት ሦስቱ የአውሮፓ አገሮች ሲሆኑ የእንጀራ መሶቧ ደግሞ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ዛሬ በአገርነት የታወቁት የጠረፍ  ግዛቶቿ እያንዳንዳቸው እስከ አንድ ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ የባህር ጠረፍ ሲኖራቸው፣ ኢትዮጵያ ከራሷ ጠረፍ እንድትርቅ በመገደዷ የጥንት ወደቦቿን አጥታ ወደብ አልባ አገር መሆኗ እጅግ ያሳዝናል፡፡ በዓይጦች የተበጣጠቀ የስንደዶ መሶብን በቀላሉ ጠግኖ እንደነበር ማድረግ ያስቸግራል፡፡ በማንኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው ይህ ታሪካዊ ክስተት እንዲፈጠር ካደረጉ በስም የተጠቀሱት አገሮች ጋር ለአንገት በላይ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ትክክለኝነት ካልሆነ በስተቀር፣ አገሮቹ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተብለው በቋሚነት መፈረጅ ሲያንሳቸው ነው፡፡

በቅርቡ ኢትዮጵያና ሰሜን ሶማሊያ (ሶማሌላንድ) አደረጉት በተባለው ስምምነት ላይ ደቡብ ሶማሊያን (ሞቃዲሾ) ጨምሮ ከባድ ሞገድ ከውስጥም ከውጭም መሰማቱ ሌላ “ታሪክ ራሱን ደገመ” ክስተት ነው፡፡ ነገሩ ‹‹ከሳሽ የተከሳሽን መልስ ቢያውቅ ኖሮ ፍርድ ቤት አይቀርብም ነበር›› ቢሆንም፣ የሞቃዲሾ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታትንና የአፍሪካ ኅብረትን ምርኩዝ ተደግፎ ያለፈ የአጭር ጊዜ የታሪክ ወቅት በማስታወስ ስምምነቱ ሉዓላዊነቴን የሚደፍር ነው ማለቱ አያስገርምም፡፡ ሌላ ሌላው የውጭ ሞገድ የታሪካዊ ጠላትነት የዞረ ድምር ነው ሊባል ይችላል፡፡ የባህር ጠረፏን ተበጣጥቀው የበሉና ኢትዮጵያ ክብሯ ተደፍሮ ዘላለም በድህነት እንድትኖር  የሚተጉ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያ መልሳ ወደ ባህር ጠረፍ መዝለቂያ ወሽመጥ መሬት እንድታገኝ ከልባቸው ይደግፋሉ ማለት ዘበት ነው፡፡ እንደ እኛ ሁሉ እነሱም የአባቶቻቸው ልጆች ስለሆኑ የአባቶቻቸውን አሻራ ማስቀጠል ባህሪያቸው ነው፡፡    

የሚያስደነግጠው ነገር ግን ከአገሪቱ ዜጎች መካከል ስምምነቱን በሙሉ ልብ የሚቀበሉ የመኖራቸውን ያህል፣ በስምምነቱ የማይደሰቱ ብሎም የሚቃወሙ የመኖራቸው ክስተት ዓይጦች የበጣጠቁት የእንጀራ መሶብ ቢጠግኑት እንደነበረ መሆን አለመቻሉን ማሳያ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ይነስም ይብዛ ከውስጥ የሚነሳው ሞገድ መንስዔ ምንድን ነው ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ ችግሩ የብሔር ፖለቲካው ውጤት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ወደ ፌዴራል መንግሥት መንበር መንጠላጠያው ዕርካብ የብሔር ፓርቲ ውግንና በሆነበት ሥርዓት ከራስ ብሔር ይልቅ፣ ለአገር ጥቅም የሚታመን ግንባር ቀደም የፌዴራል መንግሥት ምድብተኛ የብሔር ፖለቲከኛ ወይም ለብሔር መብት መከበር እታገላለሁ የሚል የማኅበረሰብ አንቂ ይኖራል ብሎ መገመት የዋህነት ነው፡፡ ያለፉት 30 የብሔር ፖለቲካ ዓመታት ተሞክሮ ያረጋገጠው ሀቅ ይኸው ስለሆነ ግምቱ ከእውነታው ብዙም አይርቅም፡፡ ይህ የአስተሳሰብና የአመለካከት መዛባት የብሔር ፖለቲካው ውጤት መሆኑን በቀላሉ ለማወቅ  ከፖለቲካ መሪዎቹና የማኅበረሰብ አንቂዎች ባህሪ ግምገማ ጎን ለጎን፣ ከተራው ዜጋ መካከል ስምምነቱን የሚያወግዘው የየትኛው ነገድ ይበዛል? ምክንያቱስ ምንድነው ብሎ መጠየቅ ወደ ማስረጃው ምንጭ ያቃርባል፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድ ልብ የሚቀበለው ስምምነት እንዲሆን ምን መደረግ አለበት ብሎ መንግሥት ራሱን ሊጠይቅ ይገባል፡፡ አለበለዚያ ስምምነቱ የማይዋጥላቸው የዚህ ነገድ ፖለቲከኞች እንጂ እነዚህኞቹ  ከእኔ ጎን ቆመዋል በማለት ኅብረተሰብን በመከፋፈል መፅናናት ለመንግሥት የዘለቄታ ጥቅም አያስገኝም፡፡ ይልቁንም መታረም ያለበትን ስህተት በጋራ በማፈላለግ መፍትሔ ለመሻት መሞከር ዜጎች በስምምነቱ ላይ ተቀራራቢ ዕይታ እንዲኖራቸው ይረዳል፡፡ የአገሪቱን ቀሳፊ ወቅታዊ ችግር በማዘናጋት የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር ነው ከሚል ማዕዘን በመነሳት፣ መንግሥት የባህር ጠረፍ ጥያቄ በአሁኑ ወቅት አምጥቶ መደንቀሩ ጉዳዩ ‹‹እኔ የምሞት ዛሬ ማታ፣ እህል የሚደርስ ለፍስለታ›› ነው የሚሉ አሉ፡፡ በእርግጥ  በአገራችን የብሔር ፖለቲካው ያስከተለው ቀውስና የዜጎች የእርስ በርስ ያለ መተማመን ችግር በጣም ከባድ ነው፡፡ ግን በርካታ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይቻላል፡፡ ስምምነቱ የተደረገው አገራችን በውስጣዊ ቀውስ ባልተዘፈቀችበት ወቅት ቢሆን ኖሮስ ከውስጥ ሊነሳ የሚችለው ሞገድ መንግሥትን አበጀህ የሚያሰኝ ነበርን? ከስምምነቱ በፊት በቅደም ተከተል በዕቅድ ያልተሠራ የፖለቲካ ሥራ ይኖር ይሆን? የመንግሥት የተግባር መመርያ የሆነው የብሔር ፖለቲካ የሴራ ፖለቲካ በመሆኑ ምናልባት ከስምምነቱ ጀርባ አንዱን ብሔር ጠቅሞ ሌላውን የሚጎዳ የድብብቆሽ ጨዋታ ዝንባሌ ይኖር ይሆን? ለጋራ ስምምነቱ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ወቅታዊ ነው ወይስ ትውልድ ተሻጋሪ ጥያቄ ነው? የአሁኑ ወቅት ለምን ተመረጠ? ስምምነቱ ሌላስ ምን ጉድለቶች አሉት?

ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር! 

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በወሎ  ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው adalhusm@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡