ንጉሥ ቻርለስ
የምስሉ መግለጫ,ንጉሥ ቻርለስ

ከ 8 ሰአት በፊት

የዩናይትድ ኪንግደም ንጉሥ ቻርልስ የካንሰር ህመም በምርመራ እንደተገኘባቸው ቤተ መንግሥታቸው ባኪንግሃም ይፋ አደረገ።

ካንሰሩ የሽንት ቧንቧ ዕጢ ካንሰር (ፕሮስቴት) እንዳልሆነ ያመለከተው ቤተ መንግሥቱ፣ ካንሰሩ ሊገኝ የቻለው በቅርቡ ባደረጉት ሕክምና ወቅት መሆኑ ገልጿል።

ንጉሡ የተገኘባቸው የካንሰር ዓይነት የትኛው እንደሆነ ባይገለጽም፣ ከቤተ መንግሥታቸው የወጣው መግለጫ እንዳለው ንጉሡ ዛሬ ሰኞ “መደበኛ ሕክምና” መከታተል ጀምረዋል።

በሕክምና ላይ በሚቆዩበት ጊዜ የ75 ዓመቱ ንጉሥ ከሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ገለል የሚሉ ሲሆን፣ ባለቤታቸው ንግሥት ካሚላ እና ልዑል ዊሊያም እሳቸውን ይወክላሉ ተብሏል።

ንጉሡ የገጠማቸው የካንሰር ህመም ያለበት ደረጃን በተመለከተ ምንም ዓይነት ዝርዝር መረጃ አልተሰጠም።

ቤተመንግሥታቸው ንጉሡ “ስለሕክምናቸው ሙሉ ለሙሉ አዎንታዊ ምላሽ ያላቸው ሲሆን፣ ወደ ሕዝባዊ ኃላፊነታቸው በፍጥነት ለመመለስ ፍላጎት አላቸው” ብሏል።

ምንም እንኳን ንጉሡ ለተወሰነ ጊዜ ከሕዝባዊ ሁነቶች ራቅ ቢሉም፣ በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን የአገር መሪነት ሚናቸውን እየተወጡ ይቀጥላሉ ተብሏል።

ንጉሡ እሁድ ዕለት ሳንድሪንግሃም ውስጥ በተካሄደ የቤተክርስቲያን የፀሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ለተሰበሰበው ሕዝብ ሰላምታ ሲሰጡ ታይተዋል።

ንጉሥ ቻርልስ ከሳምንት በፊት ለንደን ውስጥ በሚገኝ አንድ የግል ክሊኒክ ውስጥ የፕሮስቴት ሕክምና አድርገው ነበር።

ንጉሡ ወንዶች የፕሮስቴት ምርመራ እንዲያደርጉ ለማበረታት በማለም ስላደረጉት ሕክምና ሕዝቡ እንዲያውቀው አድርገዋል።

ንጉሡ ስለጉዳዩ ግንዛቤ በማስጨበጣቸው ደስተኛ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፤ የአገሪቱ ብሔራዊ የጤና አገለግሎት (ኤንኤችኤስ) ድረ-ገፅ የፕሮስቴት ካንሰር ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ዘግቧል።

ጉዳዩ ፕሮስቴት ካንሰር እንዳልሆነ ቢነገርም፣ ንጉሡ ከመጠን በላይ ያደገ ፕሮስቴታቸውን ሊመረመሩ በሄዱበት ወቅት ነው ይህ የታወቀው።

ንጉሡ ኬሞቴራፒ ሕክምና የሚወስዱ ሲሆን፣ ካንሰሩ ከመስፋፋቱ በፊት እንደተገኘ ተነግሯል።