ፅጌ ደገፍ ከልጇ ጋር
የምስሉ መግለጫ,ፅጌ ደገፍ ከልጇ ጋር

5 የካቲት 2024, 16:27 EAT

በመቀለ የሚገኘው የአይደር ሆስፒታል ኮሪደሮች በታማሚዎች ተጨናንቀዋል። የሆስፒታሉ መተላለፊያዎች በሰዎች እንቅስቃሴ ወከባ ተወጥረዋል።

በሆስፒታሉ የሕፃናት ሕክምና ክፍል ያለው ሁኔታ ግን የተለያ ነው። ፀጥታ ሰፍኗል። በዚህ የመታከሚያ ክፍል የሚገኙት አብዛኞቹ ሕጻናት በምግብ እጥረት የተጎዱ ናቸው።

ሕፃናቱ ከተኙበት አልጋ ጎን በዝምታ እና በሐዘን የተዋጡ እናቶች የልጆቻቸውን ዐይኖች ይመለከታሉ። አንዳንዶቹ ከጡታቸው ጠብ የሚል ወተት ካለ በሚል ጡታቸውን እየጨመቁ ከልጆቻቸው ጋር አፍ አጣብቀው ይታያሉ።

እነዚህ እናቶች እና ሌሎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በሰሜን ኢትዮጵያ ያሉ የአገሪቱ ዜጎች ለዓመታት ከዘለቀ ጦርነት ጠባሳ ሳይላቀቁ የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል።

መንግሥት በመላው አገሪቱ 16 ሚሊዮን ሕዝብ የምግብ እጥረት አጋጥሞታል ይላል።

ከእዚህ መካከል ገሚሱ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት የገጠማቸው እና አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚሹ ናቸው። ይህ ማለት 8 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል ብቻ ሳይሆን ተርበዋል ማለት ነው።

የ23 ዓመቷ ፀጋ ጽጋቡ እና የአራት ወር ጨቅላ ልጇ በአይደር ሆስፒታል ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ናቸው።

የፀጋ ወላጆች አርሶ አደሮች ነበሩ። የዘሩት አልበቅል ቢል ሕይወታቸውን ለመታደግ ወደ መቀለ ተሰደዱ። እንደ ብዙዎቹ ስደተኞች መውደቂያቸው አዲስ በተቋቋም መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ሆኗል።

የፀጋ ባለቤት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ተሳታፊ ሆኖ እጁ ላይ በደረሰ ጉዳት ሥራ መሥራት አይችልም። ፀጋ ልጇን ለክትባት ወደ ጤና ማዕከል በወሰደችበት ወቅት ነበር ከፍተኛ ሁኔታ የምግብ እጥረት እንዳጋመው የተነገራት።

“ነፍሰ ጡር ሳለሁ በቂ ምግብ መብላት አልችልም ነበር። ከወለድኩ በኋላ በቂ የጡት ወተት የለኝም። ለዚያ ነው ልጄ የተጎዳው። ቤቴ ውስጥም ምንም የምበላው የለም” ስትል ትናገራለች።

የአይደር ሆስፒታል ሐኪሞች እንደሚሉት በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በምግብ እጥረት ሆስፒታል የሚገቡ ሕጻናት ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል።

ምንም እንኳ ጦርነቱ በድርድር ቢቋጭም አሁንም ድረስ ከ1 ሚሊዮን የማያንስ ሕዝብ ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው መመለስ አልቻሉም።

ፀጋ ጽጋቡ ከልጇ ጋር በአይደር ሆስፒታል
የምስሉ መግለጫ,ፀጋ ጽጋቡ ከልጇ ጋር በአይደር ሆስፒታል

ወደ ትግራይ የተጓዝነው ከዩናይትድ ኪንግደም የአፍሪካ ሚኒስትር አንድሩትግራ ሚሼል ጋር ነበር።

ሚኒስትሩ በትግራይ ጉዟቸው የተጎሳቆሉ ሕጻናት እና እናቶችን ተመልክተዋል። አሳዛኝ ታሪኮችን እና አሃዞችን ከሐኪሞች ሰምተዋል።

“አሁኑኑ እርምጃ የማንወስድ ከሆነ በግልጽ የረሃብ አደጋ ተደቅኗል” ሲሉ ሚሼል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“የረሃብ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል አስፈሪ የሆኑ ምልክቶች አሉ። ‘አሁን ላይ በኢትዮጵያ ረሃብ አለ?’ ብላችሁ ብትጠይቁኝ መልሴ ‘የለም’ ነው፤ እንዳይከሰት የመድረጉ አቅም አቅም አለን። ነገር ግን ተገቢውን እርምጃ ካልወሰድን በጦርነት የተጎሳቆለችውን አገር ረሃብ ክፉኛ ሊጎዳት ይችላል” ብለዋል።

የአፍሪካ ሚኒስትሩ አገራቸው ብሪታኒያ በኢትዮጵያ ያሉ ሴቶች እና ሕጻናት ተጨማሪ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት እንዲቻላቸው ተጨማሪ 100 ሚሊዮን ፓዎንድ (125 ሚሊዮን ዶላር) እንደምትለግስ ቃል ግብተዋል።

ረሃብ በኢትዮጵያ ሊከሰት ይችላል?

ዓለም አቀፍ የእርዳት ተቋማት ‘ረሃብ’ የሚለውን ቃል በጥንቃቄ ነው የሚጠቀሙት።

ረሃብ ተከሰተ የሚባለው 20 በመቶ የሚሆነው የቤተሰብ አባል ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት ሲያጋጥመው፣ 30 በመቶ የሚሆኑ ዕደሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ከፍተኛ የምግብ እጥረት ሲያጋጥማቸው እና ከ10 ሺህ ሰዎች ሁለቱ በየዕለቱ በምግብ እጥረት ሲሞቱ ብቻ ነው።

ይሁን እንጂ ረሃብ ተከስቷል ለማለት ጥቅም ላይ የሚውሉ መመዘኛዎች ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ጌታቸው ረዳ ትርጉም አልባ ናቸው።

ጌታቸው ረዳ በትግራይ ረሃብ እየተስፋፋ ነው ይላሉ። በየጊዜው “ከሞት ጋር የሚጋፈጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው” የሚሉት አቶ ጌታቸው፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ እያመነቱ ነው በማለት ይወቅሳሉ።

“አንድ ነገር በትክክል የማውቀው እራሳቸውን መመገብ የሚችሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እራሳቸውን መመገብ አቅቷቸው በረሃ ለመሞት እያጣጣሩ መሆኑን ነው” ይላሉ።

“ረሃብም አልነው፣ የረሃብ አደጋ ትርጓሜው ለእኔ ቴክኒካዊ ነው” ካሉ በኋላ አፋጣኝ እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ “በ1977 የተከሰተው ዓይነተ ረሃብ ሊያጋጥም ይችላል” ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

የ1977ቱ ድርቅ በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ዜጎች ላይ እጅግ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ከማድረሱ በላይ አሁንም ድረስ አገሪቱን የረሃብ መገለጫ አድርጎ በምዕራባውያን ዘንድ እንድትታወስ አድርጓል።

በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበረው መንግሥት በአገሪቱ የከፋ ረሃብ መኖሩን አምኖ ለመቀበል በተገደደበት ረሃብ 1 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወታቸው አንዳለፈ ይነገራል።

ቢቢሲ የድርቁን ስፋት ለዓለም ያሳየ ዘገባ ካወጣ በኋላ ተጎጂዎችን ለመርዳታ ዓለም አቀፍ ርብርብ እንዲደረግ አስችሎ ነበር።

የዩኬ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር አንድሩ ሚሼል በመቀለ
የምስሉ መግለጫ,የዩኬ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር አንድሩ ሚሼል በመቀለ

የትግራይ ክልል አመራሮች አሁን ላይ በክልሉ ያለውን ሁኔታ ከ1977ቱ ድርቅ ጋር ማነጻጸራቸው የፌደራል መንግሥቱን ያበሳጨ ነበር።

የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ሽፈራው ተክለማርያም “የክልል መንግሥታት ጉዳዩን ፖለቲካዊ ከማድረግ መቆጠብ አለባቸው” በማለት ዓለም አቀፍ ተቋማት የበለጠ መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የገጠማት በአየር ንብረት ለውጥ የመጣ ድርቅ ነው የሚሉት ኮሚሽነር ሽፈራው፤ “ያለው ድርቅ ነው። ረሃብ አይደለም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“መንግሥት በስፋት ትኩረት ሰጥቶ ምላሽ እየሰጠ ነው፤ በተመሳሳይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ እያቀርብን ነው” ብለዋል።

በኢትዮጵያ ረሃብ ከፖለቲካ ጋር ይያያዛል።

ከዚህ ቀደም ከረሃብ ጋር ተያይዞ መንግሥታት ከሥልጣን ተወግደዋል። ተንታኞች የቃላት አጠቃቀም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕምድ መንግሥትን ያሳስባል ነው የሚሉት።

መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ተባብሮ የተከሰተውን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ ቢሞክርም የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ደካማ በመሆኑ እና የበጀት እጥረት የመንግሥትን ጥረት አክብደውታል።

በትግራይ መረጃ ማግኘት በጣም ከባድ በመሆኑ በትክክል እየተከሰተ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ማወቅ አዳጋች ነው።

በሰሜን ኢትዮጵያ፤ በተለይ ደግሞ በአማራ ክልል ባለው ወታደራዊ ግጭት ሰብዓዊ ድርጅቶች እንዳሻቸው ተንቀሳቅሰው መረጃ መሰብሰብ እና እርዳታ ማቅረብ አልተቻላቸውም።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ
የምስሉ መግለጫ,የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ

በተጨማሪም በአፋር ክልል ያለው የምግብ እጥረት ከትግራይ ክልል የላቀ ችግር እንዳያስከትል ስጋት አለ።

በሰሜን ኢትዮጵያ ያሉ ከተሞች እና መንደሮች ያለው የምግብ እጥረት ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ እንደመጣ ከሥፍራው የሚወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ እየወሰደ ያለው እርምጃ በቂ እንዳልሆነ ይነገራል።

ባፈለው ዓመት የአሜሪካው ተራድዖ ድርጅት ዩኤስኤአይዲ እና የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ፕሮግራም ያደርጉት የነበረውን ሰብዓዊ እርዳታ ለአምስት ወራት ማቋረጣቸው ይታወሳል።

የተራድዖ ድርጅቶቹ ይህን ያደረጉት በሥፍራው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች ለእርዳታ የቀረበ ምግብ ሰርቀዋል የሚል ሪፖርት በመውጣቱ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በዩክሬን የተከሰተው ግጭት ዓለም ትኩረቱን ወደዚያ እንዲያዞር አድርጎታል።

የተባበሩት መንግሥታት ተወካይ የሆኑት ራሚዝ አልክባሮቭ ይህ የተረሳ ቀውስ ነው “ዓለም ትኩረት ተነፍጓል” ይላሉ።

“በሌላው ዓለም እየተከሰተ ያለውን ችግር እያየን ሳለ በዚህኛው ዓለም ያለውን ቀውስ ሁሉም ዘንግቶታል። አሁን መደራጀት አለብን፤ ተራድዖ ማሰባሰብ አለብን።”

መቀለ የሚገኝ አንድ የምግብ እርዳታ የሚሰጥበት ማዕከል የዓለም ምግብ ፕሮግራም ስንዴ፣ ምስር እና ዘይት ያድላል።

እርዳታ ለመቀበል የተሰለፉ ሰዎች ኪውአር ኮድ በተሰኘው ቴክኖሎጂ ማንነታቸውን እያሳዩ የምግብ እርዳታ ይቀበላሉ። ነገር ግን በእርዳታ የሚያገኙት ምግብ ከበቂ በታች ነው።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባልደረባ የሆኑት ክሌር ኔቪል የሚያስፈልገው የምግብ እርዳታ ብቻ ሳይሆን ተፈናቃዮች ወደ እርሻቸው ተመልሰው የሚቋቋሙበት በጀት ጭምር ነው ይላሉ።

በዚህ ጊዜ ትልቅ ደንቃራ የሆነው ጉዳይ አሁንም በርካታ ታጣቂዎች እና የኤርትራ ወታደሮች በክልሉ መገኘታቸው ነው።

“ኢትዮጵያ የተለያዩ ችግሮች የተደራረቡባት አገር ናት” ይላሉ።

“ድርቅ አለ፤ ሰዎች ሁለት ዓመት ከፈጀ ጦርነት እያገገሙ ነው፤ የኑሮ ግሽበት እያሻቀበ ነው፤ በሽታ እየተንሰራፋ ይገኛል። ስለዚህ የምግብ እርዳታ አሁን ማድረስ ካልቻልን ሁኔታዎች ይባባሳሉ።”

የ28 ዓመቷን ፅጌ ደገፍ ያገኘናት አይደር ሆስፒታል ነው። የ15 ወራት ዕድሜ ያለው ልጇ በምግብ እጥረት ተጎሳቁላለች።

የፅጌ ቤተሰቦች በጦርነት ወቅት ቤተሰባቸውን ለመመገብ ሲሉ የነበራቸውን ከብት ሸጠው ምግብ መግዛት ነበረባቸው።

በሥፍራው ሰላም ሲሰፍን ገበሬው ያረሰውን ማጨድ አልቻለም። የሚበላ የሚቀማስ አልነበረም።

ልጇ በሽታው ሲጠናባት ፅጌ ትጨነቃለች። ነገር ግን አሁን ጨቅላ ልጇ እያገገመች ነው። ፅጌ በቅርቡ ወደመጣችበት ቀየ እንደምትመለስ ተስፋ አላት።

“ሻይ ቤት ከፍቼ በማገኘው ገንዘብ ልጄን መጠበቅ እፈልጋለሁ። ወደፊት ሌላ ችግር እንዳያጋጥማት የተቻለኝን ሁሉ ከማድረግ ወደኋላ አልልም።”