
5 የካቲት 2024, 19:51 EAT
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከአማራ ክልል ጋር በይገባኛል እያወዛገቡ ያሉትን አካባቢዎች ጉዳይ በሕዝብ ውሳኔ መፍትሄ ለመስጠት ከስምምነት ተደርሷል መባሉን አስተባበለ።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለፈው ሳምንት በመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን በኩል የአከራካሪ ቦታዎችን ሁኔታ በዘላቂነት ለመፍታት “ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ከአማራ እና ከትግራይ ክልሎች ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር” ማለቱን በመጥቀስ ነው፤ “ፍጹም የተሳሳተ [ነው]” ሲል አስተባብሏል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዛሬ ሰኞ ጥር 27/2016 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ ሕዝበ ውሳኔውን እና ሌሎች ጉዳዮችን በማንሳት ምላሽ ሰጥቷል።
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ጥር 23/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ በፌደራል መንግሥት በኩል ለትግራይ ክልል ተደረገ ያለውን የበጀት እና ሌሎች ድጋፎችን በዝርዝር አስፍሯል።
የተፈናቃዮች እና የይገባኛል ጥያቄ ስለሚነሳባቸው አካባቢዎች የጠቀሰው የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ “የአከራካሪ ቦታዎችን ሁኔታ በዘላቂነት ለመፍታትም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ጉዳዩ በዋናነት ከሚመለከታቸው ከአማራ እና ከትግራይ ክልሎች ጋር መግባባት ተደርሶ ነበር” ሲል አትቷል።
- ዩናይትድ ኪንግደም በኢትዮጵያ የተከሰተው የምግብ እጥረት አሳሳቢ መሆኑን አስጠነቀቀች5 የካቲት 2024
- አቶ ጌታቸው ረዳ ተፈናቃዮች ላሉበት ችግር የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተጠያቂ ነው አሉ24 ጥር 2024
- የአመራር ቀውስ እንደገጠመው የሚገልጸው ህወሓት ለምን መሪዎቹን መቀየር አልቻለም?1 የካቲት 2024
በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ ጉዳዩን “ፍጹም የተሳሳተ” ሲል በዛሬው መግለጫ አስተባብሎ፣ ጉዳዩን “ተቀባይነት የሌለው” ሲል ውድቅ አድርጎታል።
ጉዳዩን በሕዝብ ውሳኔ ለመፍታት ስምምነት ተደርሷል መባሉ፤ “ጊዜያዊ አስተዳደሩም ሆነ ፌደራል መንግሥቱ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ሕገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግ ጉዳዩን ለመፍታት ከደረሱበት ስምምነትም ሆነ ካላቸው ሥልጣን ውጪ የሆነ ተግባር” መሆኑን አስተዳደሩ አብራርቷል።
ከዚህ በተጨማሪም ከተፈናቃዮች ጋር በተያያዘ በመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን በኩል የወጣውን መግለጫም እንደማይቀበለው ይፋ አድርጓል።
የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቱ በመግለጫው ተፈናቃዮችን በተመለከተ የፌደራል መንግሥቱ ያከናወነውን ሥራ ጠቅሷል።
መግለጫው “በአንዳንድ አካባቢዎችም ትክክለኛ ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ አድርጓል” ሲልም አክሏል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ይህን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ “እጅግ አደገኛ” ሲል በመግለጽ፣ “‘ትክክለኛ ተፈናቃይ’ [እና] ‘ትክክለኛ ያልሆነ ተፈናቃይ’ በሚል መፈታት የነበረበትን ችግር የበለጠ የሚያባብስ አደገኛ ትንታኔ ስለሆነ አንቀበለውም” ሲል መግለጫውን ውድቅ አድርጎታል።
የአቶ ጌታቸው ረዳ አስተዳደር አክሎም፤ “እንደዚህ ዓይነት መግለጫ መውጣቱ የፌደራል መንግሥቱ የመፍትሄው አካል መሆን ሲገባው የችግሩ አካል ለመሆን የወሰነ የሚያስመስለው ስለሆነ በፍጹም ተቀባይነት የለውም” ብሏል።
የፌደራል መንግሥቱ ከፕሪቶሪያው ስምምነት ወዲህ ለትግራይ ክልል ያደረገውን የበጀት እና መሰል ድጋፎች በተመለከተ፤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት እንደሚቀርብ የጊዜያዊ አስተዳደሩ በዛሬው መግለጫው በመጥቀስ ምላሽ ሳይሰጥ ቀርቷል።
በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ለሁለቱም ክልሎች እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ሲሆን፣ ሁለቱንም ክልሎች የሚያስማማ መፍትሄ ሳይገኛ በእንጥልጥል ያለ ነገር ነው።
ይህ የአወዛጋቢዎቹ አካባቢ ጉዳይ ዘላቂ እና አስማሚ መፍትሄ ያልተገኘለት ከመሆኑ ባሻገር በፌደራል መንግሥቱ፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል ዋነኛ የራስ ምታት ሆኖ ዘልቋል።