
ከ 8 ሰአት በፊት
የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶማሊያ ጋር ጦርነት ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንን ያሉት ዛሬ ማክሰኞ ጥር 28/2016 ዓ.ም ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ እና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ውሏቸው ከሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቤሂ ጋር ከአንድ ወር በፊት የተፈራረሙት የባሕር በር ለማግኘት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ እራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል።
ይህ ከሆነ ከ36 ቀናት በኋላ ለተወካዮች ምክር ቤት ገለጻ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አገራቸው ከሶማሊያ ጋር የመዋጋት ፍላጎት እንደሌላት ተናግረው፤ በስም ያልጠቀሷቸው “ኃይሎች” ኢትዮጵያን ከሶማሊያ ጋር ለማጋጨት እየሰሩ ነው ሲሉ ከሰዋል።
“የሶማሊያ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር የመጋጨት ፍላጎት ያለው አይመስለኝም – ስገምት። ግን ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች ሶማሊያን በእጅ አዙር መጠቀም ይፈልጋሉ። ለዚያ ደሞ’ እኛ አንመችም። ምንም አይነት የከፋ ነገር ለመናገርም፣ ለማደረግም ዝግጁ አይደለንም” ብለዋል።
አክለውም “ [ይህንን] የሚመኙ ኃይሎች ለአንዳንድ ዲያስፖራ ወንድሞቻችን ሚዲያ እንደከፈቱ ሁሉ ለአንዳንድ ሶማሌ ወንድሞቻችን የተወሰነ ነገር ሊያደርጉላቸው ይችላሉ፤ ሊያዋጉን ግን አይችሉም። ቢያንስ በእኛ በኩል አንዋጋም” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው ለሶማሊያ ሰላም እና አንድነት በመሥራት የሚወዳደረው አካልም እንደሌለም ጠቅሰዋል።
“ለሶማሊያ አንድነት እንደዚህ መንግሥት የሠራ የለም። ሶማሊላንድ እና ሶማሊያን ለማገናኘት ጥረት አድርገናል። ነገም ሶማሊያ እና ሶማሊላንድ ቢስማሙ የመጀመሪያ ተደሳች አገር ኢትዮጵያ ነች” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከማንም መቀማት አንፈልግም። የማንንም ሉዓላዊነት መንካት አንፈልግም” በማለትም የመንግሥታቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።
ሆኖም ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ የአገርነት እውቅና ስለመስጠት እና ስለቀጣዩ እርምጃ ምንም አይነት አስተያየት አልሰጡም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ማብራሪያ አገራቸው “ከወራሪ” ይልቅ “የሰፈር ጎረምሳ” እንዳስቸገራት አንስተው የውጪ ኃይልን ለመመከት የሚያስችል በቂ አቅም እንዳላት ተናግረዋል።
“ኢትዮጵያ ማንም ወርራ አታውቅም፣ [ሌላ አገር] ወርሯት ደግሞ አሸንፏት አያውቅም። ሦስት አይደለም አስር ቢደመር ኢትዮጵያን ማሸነፍ አይችልም። እኛ አንዋጋም። አንፈልግም። ወደዚህ ከመጣ ደግሞ አይችልም። በቂ የሆነ አቅም አለን . . . ወደማንም አንሄድም፣ ማንም ከመጣብን ግን ራሳችንን እንከላከላለን። በሱ ስጋት አይደርባችሁ” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሶማሌላንድ ከተፈራረሙት የባሕር በር ስምምነት በተጨማሪ ጨምሮ አገሪቷን እየናጧት እያሉ ግጭቶች እንዲሁም ድርቅ እና የኑሮ ውድነት እና የአገር ሀብት ምዝበራን አስመልክቶ ምላሾችን ሰጥተዋል።
- ዩናይትድ ኪንግደም በኢትዮጵያ የተከሰተው የምግብ እጥረት አሳሳቢ መሆኑን አስጠነቀቀች5 የካቲት 2024
- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምን ውጤት አመጣ? ወደፊትስ በምን ሊቋጭ ይችላል?3 የካቲት 2024
- የትግራይ አስተዳደር በአከራካሪ ቦታዎች ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ስምምነት ተደርሷል መባሉን አስተባበለ5 የካቲት 2024
የአማራ እና የትግራይ የግዛት ይገባኛል ጥያቄ
በዛሬው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሏቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው ምላሽ የሰጡት በአገሪቷ እየተነሱ ባሉ ግጭቶች ላይ ሲሆን፣ እነዚህም አንዳንድ ጅምሮችን አደናቅፏል ብለዋል።
በአማራ እና በትግራይ ክልል ያለውን የግዛት ይገባኛል ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔ ለመመለስ የተጀመረው ጥረት በግጭቶች ምክንያት መደናቀፉን፣ በጉዳይ ላይ ሁለቱ ክልሎች መረጃ ከተሰጣቸው በኋላ ወደ ተግባር ለመግባት የተደረገው ጥረት አለመሳካቱን ጠቅሰዋል።
“በምሁራን፣ በሃይማኖት አባቶች፣ በሽማግሌዎች፣ በወጣቶች ወይይት እያደረግን በሕዝበ ውሳኔ፣ ሕዝቡ ወደ ፈለገበት እንዲመለስ እናድርግ ይህንን ካደረግን ዘላቂ ሰላም ልናመጣለን እንችላለን” ሲሉም ተደምጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከዚህ ውጪ ያለው አማራጭ ግን ጊዜያዊ ድል ዘላቂ ሰላም አያረጋግጥም የሚል አቋም ወስደን ለሁለቱም ክልሎች ነግረን ሥራ ልንጀምር ስንዘጋጅ ግጭቶች አጋጠሙን” ብለዋል።
በወሰን ይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ሕዝበ ውሳኔ እና ውይይት እስኪካሄድ ድረስ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደቀያቸው እንዲመለሱ፣ እንዲሁም የራሳቸውን ተወካዮች መርጠው እንዲተዳደሩም መንግሥታቸው ይሠራል ብለዋል።
በመጨረሻም በሕዝበ ውሳኔ ህዝቡ በሚፈልገው መንገድ በአንደኛው ክልል በሚጠቃለልበት ሁኔታ ላይም መንግሥታቸው እንደሚሠራ ጠቅሰዋል።
በትግራይ እና በአማራ ክልል የሚነሱ የግዛት ይገባኛል ጥያቄዎች ዘላቂ ሰላምን በሚያረጋግጥ መልኩ ሊፈታ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
“የወሰን ጥያቄዎችን በተመለከተ የፌዴራል መንግሥት ‘እከሌን ገፍተህ የኔን ጥያቄ መልስ’ የሚለውን መንገድ ሳይሆን ለሁሉም ክልሎች እኩል መፍትሔ የሚሰጠውን መንገድ ይከተላል” ብለዋል።
ቀጥለውም ከሕዝበ ውሳኔ ወጪ ያሉ ሌሎች አማራጮች ካሉ መንግሥት እንደሚቀበልም አንስተዋል።
“ከጦርነት መለስ ያለ ሌላ አማራጭ ካለ የፌደራል መንግስት ተባባሪ ነው” ሲሉም ተደምጧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ከማለታቸው አንድ ቀን ቀድም ብሎ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከአማራ ክልል ጋር በይገባኛል እያወዛገቡ ያሉትን አካባቢዎች ጉዳይ በሕዝብ ውሳኔ መፍትሄ ለመስጠት ከስምምነት ተደርሷል መባሉን አስተባብሎ ነበር።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለፈው ሳምንት በመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን የወጣወን መግለጫ መነሻ አድርጎ የአከራካሪ ቦታዎችን ሁኔታ በዘላቂነት ለመፍታት “ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ከአማራ እና ከትግራይ ክልሎች ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር” ማለቱን በመጥቀስ ነው፤ “ፍጹም የተሳሳተ [ነው]” ሲል አስተባብሏል።
ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለአገሪቱ ሕግ አውጪ አካል በሰጡት ማብራሪያ ላይ ጉዳዩ ለሁለቱም ክልሎች “መነገሩን” ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ችግሮች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐይን
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአማራ ክልል የተለያዩ ማኅበረሰቦች ጋር ባደረጓቸው ቀደምት ውይይቶች የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ከሦሰቱ መሠረታዊ ጥያቄዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከወሰን በተጨማሪም ሕዝቡ የሚያነሳቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ልማት፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እንደሆነ ጠቅሰው እነዚህንም ጥያቄዎች ለመመለስ መንግሥታቸው እየሠራም እንደሆነ ተናግረዋል።
መንግሥት የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በሚል ባለፉት አምስት ዓመታት ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ አመልክተው፣ ከእነዚህም ውስጥ 3200 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው፣ 53 የመንገድ ፕሮጀክቶች ሥራን በዋቢነት አንስተዋል። ከዚህም ውስጥ 1300 ኪሎ ሜትር መጠናቀቁን ጠቅሰዋል።
ሌላኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሱት በ2.4 ቢሊዮን ብር በባሕር ዳር እየተገነባ ያለውን የዓባይ ወንዝ ድልድይን በአባሪነት አንስተዋል።
ድልድዩ በኢትዮጵያ ደረጃም በጥራቱም ሆነ በወጪው ተወዳዳሪ የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም መንግሥታቸው እየሄደበት ያለውን ርቀት አመላካች ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌላው ያነሱት በቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ እመርታ አለው ያሉትን የጎርጎራ ፕሮጀክት ነው። ቀጥለውም የፋሲል ቤተ መንግሥት እድሳት ተደርጎለት በአዲስ አበባ እንዳሉ ፕሮጅክቶች ገቢ እንዲያመጣ ሥራ ለመጀመር ቢታቀደም አለመሳካቱን አንስተዋል።
በክልሉ ውስጥ ታሪካዊ የሆነውን የፋሲል ቤተ መንግሥት የፈረሰው አካል እድሳት ቢታሰብም በተለያዩ አሉባልታዎች እና ሴራዎች ሥራው መቆሙን ነው የተናገሩት።
“[የፋሲል ቤተ መንግሥት እድሳት] በተለያዩ አሉባልታዎች እና ሴራዎች ሥራው እንዳይከናወን አስቁመውታል” ካሉ በኋላ “ጦርነትም” ሌላው ምክንያት እንደሆነ አስቀምጠዋል።
ጥገናውን ለማካሄድ ያላስቻሉትን “አሉባልታዎች” ያልጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የመደመር መጽሐፍን ሽያጭ በመጠቀም ለመጠገን ታቅዶም እንደነበር አመልከተዋል።
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለማደስ ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር በመተባበር እየተሠሰራ መሆኑን እንደ አንድ የመንግሥታቸውን ቁርጠኝነት ማሳያነት ያወሱት ዐቢይ፣ በጦርነቱ ምክንያት መስተጓጎል እየገጠመው እንደሆነም አልደበቁም።
በተጨማሪም በቱሪዝም፣ በመንገድ፣ በግብርና እና ኢንደስትሪ ዘርፎች ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ዐቢይ በክልሉ ላሉ ታጣቂ ኃይሎች በድጋሚ የሰላም ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አማራ ክልልን ጨምሮ በክልሎች ድጋፍ ከተደረገለት “እገረ መንገዱን የአማራ ክልል [የሕገ መንግሥት] ጥያቄ ይመልሳል” ብለዋል።
መሠረታዊ ባሉት የሕገ መንግሥት የማሻሻያ ጥያቄም ከዚህ ቀደም ባልነበረ መልኩ መስተናገድ የሚችልበትን ማዕቀፍ በመፍጠር በሕዝቦች ውይይት እና ምክክር አገሪቷ ዘላቂ ሕገ መንግሥት እንዲኖራት የሚያስችል ሥራ የምክክር ኮሚሽኑ እየሠራ ነው ብለዋል።
“ሕገ መንግሥት ከነገሥታት ጋር የሚቀየር ሁኔታ መሆን የለበትም። በውይይት ዘላቂ ሕገ መንግሥትም ለመቅረጽ እየተሠራ ነው” ብለዋል።
በሌላ በኩል “ሕገ ማስከበር አጠናክረን እንቀጥላለን። እጃችሁን አጣጥፋችሁ ተቀመጡ የሚለንን አንስማም፣ አንቀበልም፣ አናደርግም። መንግሥት ነን አቅም በፈቀደ መጠን እንሠራለን። ሕግ ለማስከበር ሰንሠራ በእያንዳንዷ ሰከንድ ለሰላም ዝግጁ የሆነ ኃይል ካለ ለሰላም ዝግጁ ነን” ብለዋል።
ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ስለተገደገው ድርድር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥታቸው ሸኔ እያለ ከሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር በቅርቡ ለሁለተኛ ጊዜ በታንዛንያ ተደርጎ ስላልተሳካው የሰላም ድርድር ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር የተደረገው የሰላም ውይይት ግልጽነት የጎደለው ነው የሚሉ ኃይሎች እንዳሉ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ንግግር ሲጀመር ለሕዝቡ መንግሥታችው ቀድሞ ማሳወቁን ጠቅሰዋል።
ንግግሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ይህ ነው የሚባል ፍሬ ሃሳብ ላይ ባለመደረሱ መናገር ባይቻልም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የአገሪቱን ሕግ እና ሥርዓት ባከበረ መልኩ ውይይት አድርጎ ተጨባጭ ነገር ላይ መድረስ ከተቻለ ለሕዝቡ ይፋ ይሆናል ሲሉ የመንግሥታቸውን አቋም አስታውቀዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን ጨምሮ በርካታ ተፋላሚ ወገኖች ወደ አገሪቱ ገብተው በሰላም እንዲታገሉ መንግሥታቸው ጥሪ ማድረጉን ያስታወሱት ዐቢይ፣ ኦብነግ፣ ኦነግ፣ ግንቦት ሰባት፣ ኢህአፓ በአገሪቱ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ብለዋል።
እነዚህ ወገኖች በተለያዩ ደረጃዎች በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ከ“ሸኔ ጋር” ምን ዓይነት መግባባት ተደርሶ ነበር? ምንስ ቃል ተገብቶላቸው ነው የሚሉ ጥያቄዎችን አጣጥለዋል።
ኦነግን ወክለው በአመራ ደረጃ አስመራ ላይ ከመንግሥት ጋር የተደራደሩ ሰዎች አብዛኛዎቹ አዲስ አበባ መሆናቸውን የተወሰኑትም በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ናቸው ብለዋል።
“የተለየ የሰላም ውይይት ካለ ግማሹ እዚህ ገብተው የሚሠሩበት ከፊሎቹ ደግሞ ጫካ ገብተው ሕዝብ የሚያሰቃዩበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ለሁሉም የቀረቡት ጥሪዎች ተመሳሳይ ናቸው” ብለዋል።
ሸኔ ሲሉ የጠሩት ኃይል በአሥመራ በተደረገው ድርድር ከመንግሥት የተገባለት ቃል ሳይሳካ ከሆነ ጫካ የገባው “ሕዝብን እየገደሉ፣ እየዘረፉ፣ እታገላለሁ ማለት ተቀባይነት የለውም” ሲሉም ተደምጠዋል።
የፕሪቶሪያ ስምምነት እና የትግራይ ክልል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት የቋጨውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተደዳር በትብብር ትላልቅ ድሎችን ማስመዝገብ የቻሉበት ነው ብለዋል።
አክለውም ለእነዚህ ሥራዎች የፌዴራል መንግሥት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በጋራ መሥራታቸውን ተናግረው ጊዜያዊ አስተዳደሩን አሞካሽተዋል።
እነዚህን ውጤቶች በአየር መንገድ፣ በቴሌኮም፣ በኢንደስትሪ፣ ትምህርት እና ጤና ዘርፎች በማብራራት፤ በመቀለ፣ በሽረ እና በአክሱም አየር መንገድ ሥራ መጀመራቸው የሰላም ስምምነቱ ውጤት ነው ብለዋል።
በቴሌኮም ከ20 ሺህ በላይ የቤት ስልክ መስመሮች መጠገናቸው፤ በትግራይ 600 የባንክ ቅርንጫፎች በብሔራዊ ባንክ 10 ቢሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ መለቀቁን፣ በኢንዱስትሪ 217 ፋብሪካ ሥራ መጀመራቸው እንዲሁም በግብርና 630 ሺህ ሄክታር መሬት መታረሱ ትልቅ ውጤት ነው ሲሉ አንስተዋል።
በክልሉ ያለውን የግብርና ዘርፍ ለማገዝ እንዲሁ 500 የሚሆኑ ትራክተሮች ለክልሉ ተገዝተው ጂቡቲ ወደብ መድረሳቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ ቢደረግም በቂ እንዳልሆነም ነው የጠቀሱት።
ሆኖም ይህ ውጤት “በቂ አይደለም። የኢትዮጵያ አቅም ውስን ስለሆነ ነው እንጂ ከዚህ በላይ መታገዝ አለባቸው” ብለዋል።
ተፈናቃዮችን በመመለስ እንዲሁም የይገባኛል የግዛት ጥያቄዎች ሊመለሱ እንደሚገባ ጠቅሰው፣ መንግሥታቸው ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ሥራዎችን አብሮ ያከናውናል ብለዋል።
ድርቁን በተመለከተ
በርካታ የረድዔት ተቋማት ኢትዮጵያ የከፋ ረሃብ ሊያጋጥማት እንደሚችል እያስጠነቀቁ ባለበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርቁን እንደ ፖለቲካ መሳሪያ መጠቀም አግባብ አይደለም ሲሉ በዛሬው ውሏቸው ተደምጠዋል፡፡
በዘንድሮው ዓመት በትግራይ፣ በአማራ አና በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ድርቅ መከሰቱን ገልጸው የዚህንም ታሪካዊ ዳራ ጠቅሰዋል።
“ድርቅ መንግሥት አላመጣውም፣ ችግኝ እንተከል ሲባል ምን ያደርጋል ስንል፣ ስንዴ እናምርት ስንል ምን ያደርጋል ብለን ድርቅ መጣ ብለን ብንጮህ ትርጉም የለውም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“በረሃብ ምክንያት የሚሞት ሰው የለም” ብለውም የተከሰተው ድርቅ የሰው ሕይወት እንዳይቀጥፍ መተባበር እንደሚገባ አሳስበዋል።
አንዱ ክልል ተርቦ አንዱ በልቶ ሊያድር አይችልም ሲሉም ገልጸው ባለፉት ጥቂት ወራት በትግራይ ክልል 5 መቶ ሺህ ኩንታል እህል በመንግሥት እና በሌሎች አካላት ትብብር ወደ ክልሉ ማድረስ መቻሉን አስረድተዋል።
መንግሥታቸው አንድም ቦታ በረሃብ የሚሞት ሰው አይቶ ዝም አይልም በማለትም በመተባበር ይህንንም ጊዜ እንዲሻገር እንደሚሠሩም አስረድተዋል።