በጋዛ የደረሰው ውድመት

ከ 5 ሰአት በፊት

ሐማስ አዲስ ለቀረበው የተኩስ አቁም ስምምነት ምላሽ ሰጥቻለሁ አለ።

እስራኤል፣ አሜሪካ፣ ካታር እና ግብፅ አቀረቡት የተባለው የተኩስ አቁም ስምምነት ይዘት ለሕዝብ ይፋ አልሆነም።

ነገር ግን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለስድስት ሳምንታት እንደሚቆይና ሐማስ የታገቱ እስራኤላዊያንን የሚለቅ ከሆነ ፍልስጤማዊያን እስረኞች በምትኩ እንደሚለቀቁ ተነግሯል።

እስራኤል እና አሜሪካ የሐማስን ምላሽ እየመረመርን ነው ብለዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፤ ሐማስ ስለሰጠው ምላሽ ከእስራኤል ባለሥልጣናት ጋር ረቡዕ ዕለት እንደሚመክሩ ገልጠዋል።

ምንም እንኳ ብሊንከን የሐማስን ምላሽ አሜሪካ እንዴት እንደምትመለከተው ባይገልጡም ፕሬዝደንት ጆ ባይደን “ትንሽ ከበድ ያለ” ሲሉ ገልጠውታል።

ይህ ማለት የእስራኤል ባለሥልጣናት በሐማስ ምላሽ ላይስማሙ ይችላሉ ማለት ነው።

አንድ ነባር የሐማስ ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቡድኑ ለቀረበው ምክረ ሐሳብ “አዎንታዊ ዕይታ” ያለው ምላሽ ሰጥቷል።

ቢሆንም የጋዛ መልሶ ግንባታ፣ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው የመመለሳቸው ጉዳይና እና መልሶ ማቋቋምን በተለመከተ የተወሰኑ ማሻሻያዎች እንዲኖሩ መጠየቃቸውን ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ እንዳሉት ሐማስ ሌላ ያቀረበው ጥያቄ የተጎዱ ሰዎች ሕክምና ስለሚያገኙበት ሁኔታና እንዴት ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ ካለሆነም ወደ ውጭ ሀገር ሄደው ይታከማሉ ስለሚለው ጉዳይ ነው።

አዲሱ የተኩስ አቁም ስምምነት ዕቅድ ለሐማስ የተላከው ከአንድ ሳምንት በፊት ነው። ነገር ግን ሐማስ ለመመለስ ይህን ያህል ጊዜ የወሰደው “ግልፅ ያልሆኑና አሻሚ” አንቀፆች ስለነበሩት መሆኑን የቡድኑ ተወካይ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

የኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼኽ ሞሐመድ ቢን አብዱልራህማን አል ታኒ የሐማስን ምላሽ በጠቅላላው “አዎንታዊ” ብለውታል።

በጋዛ ያለው ግጭት በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7 ሐማስ እስራኤላዊያን ላይ ጥቃት አድርሶ 1300 ሰዎች ገድሎ 250 ካገተ በኋላ ነው የተጀመረው።

ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ 27500 ሰዎች ጋዛ ውስጥ መሞታቸውን የጋዛ ሰርጥ ጤና ሚኒስትር ይገልጣል። የጋዛ ሰርጥ በሐማስ የሚመራ ሲሆን በአውሮፓውያኑ ከ2007 ጀምሮ በእስራኤልና በግብፅ ገደብ የተጣለበት ሥፍራ ነው።

ሐማስ በበርካታ ሀገራት ሽብርተኛ ቡድን የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

ባለፈው ኅዳር አንድ ሳምንት በቆየው የተኩስ አቁም ስምምነት ታግተው የነበሩ 105 እስራኤላዊያንና የሌሎች ሀገራት ዜጎች ሲለቀቁ በእስራኤል እሥር ቤቶች የነበሩ 240 ፍልስጤማዊያን ተለቀዋል።

እስራኤል በያዝነው ሳምንት መባቻ የሐማሱን መሪ ያህያ ሲንዋር ውስጥ እያደነች መሆኑን አሳወቃ “ጥሩ እየገሰገስኩ ነው” ማለቷ ይታወሳል።

ይህ የእስራኤል እርምጃ ተስፋ የተጣለበትን የተኩስ አቁም እንዳያስተጓጉለው ስጋት አለ።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ የታገቱ ሰዎችን እንዲያስለቅቁ ከሀገር ቤት ከፍተኛ ጫና እየገጠማቸው ነው።

ስምምነቱ አንድ እርምጃ እንዲራመድ የሚሹት አንተኒ ብሊንከን ወደ መካከለኛው ምስራቅ የመጡት ቀጣናው በእስራኤል-ጋዛ ጦርነት ምክንያት እየተናወጠ መሆኑን በማሰብ ነው።

ዩናይትድስ ስቴትስ የእስራኤል-ጋዛ ጦርነት ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች እየወሰዱባት ላለው እርምጃ ምላሽ በመስጠት ላይ ትገኛለች።

በእስራኤል እና ሐማስ መካከል የሚደረግ የተኩስ አቁም ስምምነት የመካከለኛው ምስራቅን ውጥረት ለማርገብ አንዱ መፍትሔ እንደሆነ አሜሪካ ታምናለች።

ማክሰኞ ዕለት እስራኤል እንዳለቸው ከቀሩት 136 ታጋቾች መካከል 31 ሰዎች ተገድለዋል።