
ከ 1 ሰአት በፊት
የቀድሞው የፎክስ ኒውስ አቅራቢ ታከር ካርልሰን ከሩሲያው ፕሬዝደንት ጋር ቃለ-መጠይቅ ሊያደርግ ነው።
ጋዜጠኛው ከቭላድሚር ፑቲን ጋር “በቅርቡ” ሞስኮ ውስጥ ቃለ-መጠይቅ እንደሚያደርግ ይፋ አድርጓል።
ታከር በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ገፁ በለጠፈው ቪድዮ “አሜሪካዊያን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ስለሚሳተፉበት ጦርነት ማወቅ ይገባቸዋል” ብሏል።
ሩሲያ ከሁለት ዓመታት በፊት ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ፑቲን ከምዕራባዊ ጋዜጠኛ ጋር የሚያደርጉት የመጀመሪያው ቃለ-መጠይቅ ይሆናል።
ክሬምሊን ስለ ቃለ-መጠይቁ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
የ54 ዓመቱ ጋዜጠኛ ወደ ሞስኮ ማቅናት በሩሲያ መገናኛ ብዙኃን በስፋት የተዘገበ ሲሆን አንዳንድ ጣቢያዎች እያንዳንዱን እንቅስቃሴን ሲዘግቡ ተስተውለዋል።
“እርግጥ ነው ይህን መሰል ቃለ-መጠይቅ ማድረግ የራሱ አደጋ አለው። ለዚህ ነው ለወራት አስበን ተዘጋጅተን የመጣነው” ብሏል ታከር።
ጋዜጠኛው ወደ ሩሲያ ለመምጣት ሙሉ ወጭውን የሸፈነው ከኪሱ እንደሆነ ጠቁሞ ቃለ-መጠይቁን ማድረግ የፈለገው “በርካታ አሜሪካዊያን ዓለምን እየለወጠ ስላለው ጦርነት መረጃው ስሌላቸው ነው” ብሏል።
ታከር፤ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተነሳ በኋላ ምዕራባዊያን መገናኛ ብዙኃን የዩክሬኑን ፕሬዝደንት በተደጋጋሚ አነጋግረው ዘገባዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል ካለ በኋላ ዘገባዎቹ አሜሪካ ወደ ጦርነቱ የበለጠ እንድትገባ ለሚፈልጉት ዜሌንስኪ “መሣሪያ ለመሆን ነው” ብሏል።
“ይህ ጋዜጠኝነት አይደለም – የመንግሥት ፕሮፖጋንዳ እንጂ።”
አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ቮሎድሚር ዜሌንስኪን በተደጋጋሚ “አምባገነን” እያለ ይጠራቸዋል።
- ቴይለር ስዊፍት “የማደርጋቸውን በረራዎች የሚከታተለውን ተማሪ እሰካሳለሁ” ስትል አስፈራራችከ 2 ሰአት በፊት
- አዋሽ 40 ፡ “በቂ ምግብ ፣ ውሃ እና በቂ እንቅልፍ በስለትም ቢሆን የማይገኝበት ቦታ”ከ 6 ሰአት በፊት
- እስራኤል-ጋዛ፡ ሐማስ አዲስ ለቀረበው የተኩስ አቁም ስምምነት ምላሽ ሰጠከ 5 ሰአት በፊት
ነገር ግን ይላል ታከር፤ “አንድም ጋዜጠኛ ቭላድሚር ፑቲንን ለመጠየቅ አልደፈረም።”
የቢቢሲ ሩሲያ አርታዒ ስቲቭ ሮዘንበርግ ቢቢሲ “ባለፉት 18 ወራት ለክሬምሊን ጥያቄ ቢልክ ሁሌም ‘አይሆንም’ የሚል ምላሽ ነው ሚደርሰን” ይላል።
የተባበሩት መንግሥት እንደሚለው የሩሲያ ወታደሮች ዩክሬን ውስጥ የመድፈር፣ የማሰቃየት እና የግድያ ወንጀል ፈፅመዋል።
ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት [አይሲሲ] የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ የእሥር ማዘዣ አውጥቷል።
ፍርድ ቤቱ ፑቲን በጦር ወንጀል እና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሕፃናትን ከዩክሬን ወደ ሩሲያ በማጋዝ ይከሳቸዋል።
ሩሲያ ውስጥ ደግሞ ጋዜጠኞች በነፃነት መዘገብ አይችሉም። መገናኛ ብዙኃን “ጦርነት” ሳይሆን “ልዩ ወታደራዊ ኦፕሬሽን” እንዲሉ ይገደዳሉ።
ታከር ካርልሰን ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በግልፅ ፕሬዝደንት ፑቲንን በመደገፍ ይታወቃል። ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት “ፑቲንን መጥላት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መሠረት ሆኗል” ብሎ አሜሪካዊያን ለምን ብለው እንዲጠይቁ መክሮ ነበር።
ከሩሲያ ወረራ በኋላ ድምፀቱን ቀይሮ ለዩክሬን ጦርነት ቭላድሚር ፑቲን ተጠያቂ ናቸው ብሎ ነበር።
ታከር ካርልሰን ከፑቲን ጋር የሚያደርገው ቃለ-መጠይቅ መች እንደሚተላለፍ ግልፅ አይደለም። ነገር ግን ቃለ-መጠይቁ ሳይቀንስ ሳይጨመር የኤክስ ገፁ ላይ እንደሚለጠፍ ቃል ገብቷል።
የኤክስ ባለቤት የሆነው ኢላን መስክ ቃለ-መጠይቁን “ላለመጨቆን አሊያም ላለማገድ ቃል እገባለሁ” ብሏል።
በአሜሪካ እጅግ ታዋቂ ከሚባሉ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢዎች መካከል አንድ የነበረው ታከር ባለፈው ዓመት ነው ድንገት ፎክስ ኒውስን መልቀቁን ያሳወቀው።
አብዛኛውን ጊዜ ፕሮግራሞቹ ወግ አጥባቂ እና ለሪፐብሊካን ፓርቲ የሚያደሉ ተደርገው ይቆጠራሉ።
ከ2016 እስከ 2023 ድረስ የዘለቀውን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ካቋረጠ በኋላ በኤክስ ገፁ የሚተላለፍ ፕሮግራም ማሰናዳት ጀምሯል።