አቡነ ጴጥሮስ
የምስሉ መግለጫ,አቡነ ጴጥሮስ

6 የካቲት 2024

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ያላቸው ኃላፊነት ከግምት ገብቶ ወደ አገር እንዲገቡ እንዲፈቀድ ጠየቀች።

ቤተክርስቲያኗ ይህን የጠየቀችው የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ እና የኒው ዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ ከውጭ አገር መልስ አገር እንዳይገቡ መከልከላቸው ከተገለጸ በኋላ ነው።

ቢቢሲ ከቤተክርስቲያኗ ሁለት አባቶች ጠይቆ አቡነ ጴጥሮስ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እንዳይወጡ መከልከላቸው እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ችሏል።

በተጨማሪም አቡኑን ለመቀበል ወደ አየር ማረፊያው የሄዱ የቤተክርስቲያኑቱ ተወካዮች ይገቡበታል ከተባለው ሰዓት አንስቶ እየተጠባበቋቸው እንደነበረ አመልክተዋል።

የቤተክርስቲያኗ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ አቡነ ጴጥሮስ በሰሜን አሜሪካ የነበራቸውን ጉዞ አጠናቀው ኢትዮጵያ ከደረሱ በኋላ ወደ አገር እንዳይገቡ መከልከላቸውን አስታውቆ፣ ይኸው ክልከላ እንዲነሳ ቤተክርስቲያኗ መጠየቋን ገልጿል።

የቤተክርስቲያኗ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ አቡነ ጴጥሮስ ከሳምንታት በፊት በቋሚ ሲኖዶስ እውቅና ወደ ሀገረ ስብከታቸው ለሥራ ተጉዙው እንደነበረ አስታውሷል።

አቡኑ ከሳምንታት ቆይታ በኋላ ዛሬ ማክሰኞ ጥር 28/2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ ቢመለሱም ማንነቱ ባልተገለጸ የመንግሥት አካል ከቦሌ አየር ማረፊያ እንዳይወጡ መከልከላቸውን ተገልጿል።

የሕዝብ ግንኙነቱ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ባውጣው መግለጫ ወደ አገር እንዳይገቡ የተከለከሉት አቡነ ጴጥሮስ ቦሌ አየር ማረፊያ እንደሚገኙ ቢገልጽም ለምን እንዳይወጡ እንደተደረጉ ያለው ነገር የለም።

ከጠዋት ጀምሮ አቡኑ ወደ አዲስ አበባ እንደሚመለሱ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተነገረ ሲሆን፣ ከእኩለ ቀን ጀምሮ ደግሞ ከቦሌ አየር ማረፊያ እንዳይወጡ መከልከላቸውን የሚገልጹ መረጃዎች ከፎቶግራፋው ጋር በስፋት እየተዘዋወረ ነው።

አቡነ ጴጥሮስ የቤተክርስቲያኗ አባት ኃላፊ እና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ መሆናቸውን ከግምት በማስገባት ወደ አገር እንዲገቡ ፍቃድ እንዲሰጣቸው ቤተክርስቲያኗ ጥሪ ማስተላለፏን የሕዝብ ግንኙነቱ ገልጿል።

“ብፁዕነታቸው በአሁኑ ሰዓት ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያው የሚገኙ መሆኑን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ በአየር መንገድ አቀባበል ለማድረግ በተገኘበት ወቅት አረጋግጧል” ብሏል።

የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ አቡነ ጴጥሮስ ወደ አገር እንዳይገቡ ለምን እንደተከለከሉ ከኢሚግሬሽን የዜግንት አገልግሎት ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚዘዋወሩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አቡነ ጴጥሮስ ከአዲስ አበባ ለመውጣት ወደ ሌላ አውሮፕላን መሳፈራቸውን እያመለከቱ ነው።

ቢቢሲ ይህንን መረጃ ለማጣራት ያደረገው ጥረት አልተሳካም። የቤተክርስቲያኗ ኃላፊዎችም ስለዚህ የሚያውቁት ጉዳይ እንደሌለ ተናግረዋል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት አቡነ ጴጥሮስ ወደ አሜሪካ ከተጓዙ በኋላ የሲኖዶሱ ዋና ፀሐፊ “ከአገር ኮበለሉ” የሚሉ ሐሰተኛ መረጃዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ሲሰራጩ ነበረ።

ይሁን እንጂ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ አቡነ ጴጥሮስ ወደ አሜሪካ የተጓዙት በሲኖዶሱ እውቅና ለዓመታዊ መንፈሳዊ ክብረ በዓላት እና የማዕረገ ዲቁና ለመስጠት መሆኑን ገልጸው ነበር።

አቡነ አብርሃምን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ከአገር እንደሸሹ ተደርጎ የተወራው የቤተ-ክርስቲያንን ክብር ለማኮሰስ ታስቦ የተደረገ ነው ብለው ነበር።